ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ፥ ወደ ተቸገሩት በልግስና መቅረብ የቤተ ክርስቲያንን ተዓማኒነት ያረጋግጣል ሲሉ ገለጹ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ ዓርብ ኅዳር 12/2018 ዓ. ም. በቫቲካን ለተቀበሉት የካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ዓለም አቀፍ የበጎ አድራጎት ምክር ቤት አባላት ባደረጉት ንግግር፥ የበጎ አድራጎት ድርጅት ለመላዋ ቤተ ክርስቲያን እያቀረበ ላለው ጽኑ አገልግሎት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ለምክር ቤቱ ባደረጉት ንግግር፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ለድሆች፣ ለተናቁት፣ ለተዘነጉት እና ለተገለሉት ያሳየውን ርኅራሄን ቤተ ክርስቲያን በዓለም አቀፍ የበጎ አድራጎት ድርጅት በኩል ሁልጊዜ በተጨባጭ ማወጇን አስታውሰዋል።
ለድሆች የሚደረግ ርኅራሄ ኢየሱስ ክርስቶስ በዓለም ውስጥ የነበሩ ወገኖቹን እስከ መጨረሻው ድረስ እንደወደዳቸው በቅዱስ ቁርባን ውስጥ መግለጹን አስታውሰዋል።
ለድሆች የሚሰጥ ፍቅርን በማስመልከት፥ “እኔ ወድጄሃለሁ” “Dilexi te” በሚል ርዕሥ ይፋ ባደረጉት ሐዋርያዊ ምክራቸው ላይ ያሰላሰሉት ቅዱስነታቸው፥ ይኸውም ከክርስቶስ የምንቀበለው ፍቅር የግል ሃብት ሳይሆን የተሰጠን ተልዕኮ እንደሆነ በማስገንዘብ፥ ፍቅር ወደ ፊት እንደሚለከን፣ አገልጋዮች እንድንሆን እና የሌሎችን ሕመም እንድንመለከት የሚያደርገን መሆኑን አስረድተዋል።
የሚያበራ የቤተ ክርስቲያን እናታዊ ፍቅር ምልክት
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ ዓለም አቀፍ የበጎ አድራጎ ድርጅት “ካሪታስ ኢንተርናሽናሊስ” ለረጅም ጊዜ የሚያበራ የቤተ ክርስቲያን የእናትነት ፍቅር ምልክት ሆኖ መቆየቱን ፥ አባላቱ እያንዳንዱን ሰው በክብር ለማገልገል ከሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ተተኪ ጋር ለመራመድ ዝግጁ ሆነው መቆማቸውን በማስታወስ ምስጋናቸውን ገልጸዋል።
ቅዱስነታቸው ለዲፕሎማሲ አካላት ባደረጉት የመጀመሪያ ንግግራቸው የተናገሯቸውን እና ቤተ ክርስቲያኗ በዓለም ዙሪያ የምታከናውናቸውን ተግባራት የሚደግፉ ሦስት ምሰሶዎችን እነርሱም ሰላም፣ ፍትህ እና እውነት እንደሆኑ መናገራቸውን አስታውሰዋል።
“ተልዕኮአችሁ ያንን ራዕይ ያስተጋባል” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ ይህንን የምታደርጉት በረቂቅ መንገድ ሳይሆን ዕለት በዕለት በምታደርጉት ተጨባጭ ሥራ አማካይነት ነው” ሲሉ አስረድተዋል።
ፍቅራችሁ ረቂ ሳይሆን ተጨባጭ ይሁን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ለበጎ አድራጎት ድርጅት ምክር ቤት አባላት ባደረጉት ንግግር፥ “የተፈናቀለ ቤተሰብ ብትደግፉ፣ ለድሆች መብት ብትቆሙ ወይም የተረሱ ሰዎችን የሚያዳምጥ ልብ ቢኖራችሁ የቤተ ክርስቲያ ምስክርነት የበለጠ ተዓማኒ ይሆናል” ብለዋል።
በዚህ መንፈስ ወደ አገራቱ አብያተ ክርስቲያናት በመሄድ የምእመናን መሪዎችን መመሥረት እንዲያጠናክሩ እና በልዩ ልዩ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች መካከል ያለውን አንድነትን እንዲጠብቁ ብርታትን በመመኘት፥ “የቤተ ክርስቲያኗ ተልዕኮ የሚገለጠው በወዳጅነት አብረን ስንጓዝ እና መንፈስ ቅዱስ የምሕረት ሥራችንን እንዲቀርጽ ስንፈቅድ ብቻ ነው” ብለዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በመጨረሻም፥ የድሆች እናት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ዓለም አቀፍ የበጎ አድራጎት አባላት አማላጅ እንድትሆናቸው፣ የተስፋ ነጋዲያን እና የሰላም መሣሪያዎች እንዲሆኑ፣ በድፍረት፣ በጽናት እና በደስታ ስጦታው እግዚአብሔር እንዲባርካቸው በመለመን ንግግራቸውን ደምድመዋል።
