ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ፥ “እኛ የፍጥረት ተንከባካቢዎች እንጂ አውዳሚዎች አይደለንም” ሲሉ ገለጹ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
አብዛኛውን የውይይት ጊዜ ለደቡባዊ የዓለም ክፍል በሰጠው የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ጉባኤ ላይ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ከእስያ፣ ከአፍሪካ፣ ከላቲን አሜሪካ እና ከካሪቢያን አኅጉራት በመጡ ካርዲናሎች ተወክላ ስብሰባዎችን እና ሲምፖዚየሞችን ተካፍላለች። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛም፥ ከደቡባዊው የዓለም ሕዝቦች ጋር ያላቸውን ቅርበት በማሳየት በየተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ሰላሳኛ ጉባኤ ለሚሳተፉት ብጹዓን ጳጳሳት የቪዲዮ መልዕክት ልከዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ የጉባኤው ሁለተኛው ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ኅዳር 8/2018 ዓ. ም. ሊጠናቀቅ ሲል በላኩት መልዕክት፥ “የአማዞን ክልል አስቸኳይ እንክብካቤ የሚፈልግ የፍጥረት ሕያው ምልክት ነው” በማለት ለዓለም በቃላት እና በምልክት ትንቢታዊ ድምጻቸውን ሲያሰሙ ከነበሩት ካርዲናሎች ጋር ተቀላቅለዋል።
ቅዱስነታቸው በአማዞኒያ ሙዚዬም ውስጥ ለተሰበሰቡት ጳጳሳት ባስተላለፉት የቪዲዮ መልዕክት፥ “በተስፋ እና በተጨባጭ እርምጃ አብሮ የሚሠራ ዓለም አቀፍ ማኅበረሰብን መገንባት ምረጡ” ብለው፥ “ምድሪቱን በመንከባከም ረገድ ዕድገት ቢታይም በቂ እንዳልሆነ፣ ተስፋ እና ቁርጠኝነት በቃላት እና በምኞት ብቻ ሳይሆን በተጨባጭ ድርጊቶች መታደስ አለባቸው” ሲሉ አፅንዖት ሰጥተዋል።
“ፍጥረት በጎርፍ፣ በድርቅ፣ በአውሎ ነፋሶች እና በማያቋርጥ ሙቀት በመጎዳቱ እየጮኸ ይገኛል” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ “ከሦስት ሰዎች መካከል አንዱ በእነዚህ የአየር ንብረት ለውጦች ምክንያት በከፍተኛ ተጋላጭነት ይኖራል” ብለዋል። ለእነዚህ ሰዎች የአየር ንብረት ለውጥ የሩቅ ስጋት እንዳልሆነ ገልጸው፥ ችላ ማለቱ የጋራ ሰብዓዊነታችንን መካድ እንደሆነ አስረድተዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ “የዓለም የሙቀት መጠንን ከ1.5°ሴ በታች ለማድረግ አሁንም ጊዜ ቢኖርም ዕድሉ እያለቀ ነው” ሲሉ አፅንዖት ሰጥተዋል። “የእግዚአብሔር ፍጥረት ተንከባካቢዎች እንደመሆናችን መጠን በእምነት እና በትንቢታዊነት በፍጥነት ለመንቀሳቀስ የተሰጡንን ስጦታዎች ለመጠቀም ተጠርተናል” ብለዋል።
በመቀጠልም የፓሪስ ስምምነት እውነተኛ ዕድገት እንዳሳየ አፅንዖት ሰጥተው፥ “ሰዎችን እና ምድሪቱን ከጉዳት ለመጠበቅ እጅግ ጠንካራ መሣሪያችን ነው” ሲሉ ገልጸውታል። “እውነቱን መናገር አለብን” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ “ስምምነቱ የማይሳካ ሳይሆን ነገር ግን ምላሽ በመስጠት ላይ ስህተት አለ” ሲሉ ተናግረዋል። የአንዳንድ ሰዎች የፖለቲካ ፍላጎት የሚጎድል መሆኑን የገለጹት ቅዱስነታቸው፥ እውነተኛ አመራር ማለት አገልግሎት እና በተወሰነ ደረጃ ድጋፍ ማድረግ ማለት እንደሆነ በማስረዳት፥ ጠንካራ የአየር ንብረት እርምጃዎች ጠንካራ እና ፍትሃዊ የኢኮኖሚ ሥርዓቶችን እንደሚፈጥሩ፥ ጠንካራ የአየር ንብረት እርምጃዎች እና ፖሊሲዎች ሁለቱም ይበልጥ ፍትሃዊ እና የተረጋጋ ዓለም ውስጥ መዋዕለ ነዋይ ናቸው” ሲሉ አስረድተዋል
ቅዱስነታቸው በመልዕክታቸው ማጠቃለያ፥ በኅብረት የሚጓዙ የእያንዳንዱ አገር ሃይማኖታዊ እምነቶች፣ የሳይንስ ጠበብት፣ የመንግሥት መሪዎች እና የሃይማኖት አባቶች ሥራን በማስታወስ፥ “እኛ የፍጥረት ጠባቂዎች እንጂ የውድመት ተፎካካሪዎች አይደለንም” ብለዋል።
የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ የቪዲዮ መልዕክት
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ይህን በእምሮአቸው ልባቸው በመያዝ በጉባኤው ላይ የተገኙት በሙሉ ከፓሪሱ ስምምነት እና ከአየር ንብረት ትብብር ጀርባ በማይናወጥ አንድነት ግልጽ ዓለም አቀፍ ምልክት እንዲያሳዩ ጠይቀው፥ በመጨረሻም “ይህ ጉባኤ የሚካሄድበት የአማዞኒያ ሙዚዬም የሰው ልጅ ከመከፋፈል እና ከክህደት ይልቅ ትብብርን የመረጠበት ቦታ መሆኑ ይታወስ” ብለዋል።
ከቅዱስነታቸው የቪዲዮ መልዕክት በኋላ በጉባኤው ላይ ከደቡባዊው የዓለም ክፍል የመጡ ብጹዓን ካርዲናሎች የዓሣ ማጥመጃ መረብን አቅርበዋል። መረቡ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2019 ዓ. ም. በፓን-አማዞን ክልል አገራት የሲኖዶስ ጉባኤ ወቅት ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳስ ፍራንችስኮስ በስጦታነት የተበረከተ ቅጂ ሲሆን ይህም በአማዞን ደን ውስጥ በሚኖሩ በርካታ ነባር ተወላጅ ማኅበረሰቦች የተሸመነ የአንድነት እና የሰላም ምልክት እንደሆነ ታውቋል።
