ፈልግ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ታዋቂውን የፊልም ተዋናይ ሮበርት ደ ኒሮን በቫቲካን ሲቀበሉ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ታዋቂውን የፊልም ተዋናይ ሮበርት ደ ኒሮን በቫቲካን ሲቀበሉ 

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ከታዋቂው የፊልም ተዋናይ ሮበርት ዴ ኒሮ ጋር በቫቲካን ተገናኙ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ በመቶዎች በሚቆጠሩ ፊልሞች ላይ በታዋቂነት የተሳተፈውን እና ከሮም ከተማ ከንቲባ ሮቤርቶ ጓልቲየሪ ከፍተኛ ሽልማት የተቀበለውን ታዋቂ የፊልም ተዋናይ ሮበርት ደ ኒሮን በቫቲካን ተቀብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ታዋቂው የፊልም ተዋናይ ሮበርት ዴ ኒሮ በሮም ባደረገው የአርባ ስምንት ሰዓታት ቆይታው ዓርብ ጥቅምት 28/2018 ዓ. ም. ጠዋት በቫቲካን አጭር ጉብኝት በማድረግ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ጋር የተገናኘ ሲሆን፥ ቅዱስነታቸው እውቁን የፊልም ተዋናይ ሮበርት ዴ ኒሮን በቫቲካን በሚገኘው የትሮኔቶ ሐዋርያዊ ሕንጻ ውስጥ አጭር አቀባበል በማድረግ የመቁጠሪያ ስጦታን አበርክተውለታል።

በቫቲካን ውስጥ የተደረገ አቀባበል

ሁለት ጊዜ የኦስካር ሽልማት አሸናፊ የነበረው ታዋቂው የ82 ዓመት ዕድሜ ባለጸጋ ሮበርት ዴ ኒሮ በዜግነት አሜሪካዊ ቢሆንም ወላጆቹ በጣሊያን ውስጥ ከሞሊሴ ከተማ የወጡ መሆናቸው ታውቋል። በሮም የ48 ሰዓት ጉብኝት ያደረገው ሮበርት ዴ ኒሮ በአሜሪካ ቺካጎ ከተማ የአንድ አካባቢ ተወላጅ የሆኑትን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛን በቫቲካን ከጎበኟቸው በኋላ የሮም ጉብኝቱን ማጠናቀቁ ታውቋል።

የቺካጎ በርካታ የረጅም ጊዜ ጓደኞቻቸው እንደሚያደርጉት ሁሉ ብዙውን ጊዜ ወደ ፊልም ቤት መሄድ የሚወዱ መሆናቸውን ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ ከተዋናዩ ጋር በትሮኔቶ ሐዋርያዊ ሕንጻ ውስጥ በነበራቸው አጭር ቆይታ የኅብረት ፎቶግራፍ ከተነሱ በኋላ በመጨረሻም አብረውት ለመጡትም ጭምር የመቁጠሪያ ስጦታን አበርክተውላቸዋል።

በሮም በስጦታነት የተጠው ሜዳሊያ

ታዋቂው የፊልም ተዋናይ ሮበርት ዴ ኒሮ በቫቲካን ያደረገው ጉብኝት በሐዋርያዊ ሕንጻ ውስጥ የሚገኘውን ጥበባዊ ውበት በጥልቀት እንዲመለከት ያደረገ ሲሆን፥ በሮም በነበረው ተሞክሮ ፍጻሜ ከሮም ከተማ ከንቲባ አቶ ሮቤርቶ ጓልቲየሪ ጋር በማዘጋጃ ቤቱ ደረጃ ላይ ቆሞ በተመለከተው የጥበብ ሥራ ተማርኮ እንደ ነበር ተገልጿል።

ታዋቂው የፊልም ተዋናይ ሮበርት ዴ ኒሮ ለሮም ከተማ ከንቲባ አቶ ሮቤርቶ ጓልቲየሪ ባደረገው ንግግር፥ “የሮም ከተማ ከከተማነት በላይ ሕያው የጥበብ ሥራ ናት” ሲል ተናግሯል። ከንቲባ አቶ ሮቤርቶ ጓልቲየሪ በበኩላቸው የከተማዋ ከፍተኛ ክብር የሆነውን የተኩላ ምስልን በስጦታነት አበርክተውለታል። ተዋናይ ሮበርት ዴ ኒሮ በታዋቂ ፊልሞች ዋና ገፀ ባህሪ ሆኖ የተሳተፈበትን “ዘ ጎድፋዘርን” ጨምሮ የሲሲሊያን አፍ የተማረበትን በማስታወስ ሽልማቱን በደስታ ተቀብሏል።

“ለባሕል፣ ለሲኒማ ዕድገት እና ለውበት ብዙ አስተዋጽዖን ካበረከተ ቦታ እውቅናን ማግኘት በእውነት ልብን የሚነካ ነው” ሲል ተዋናዩ ተናግሮ አክሎም፥ “ቤተሰቤ ከጣሊያን የመጣ በመሆኑ እውቅናው ለእኔ እጅግ ልዩ ትርጉም ያለው ነው” ሲል ገልጿል።

 

08 Nov 2025, 15:02