ፈልግ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በቅዱስ ማርቲኖ የተመላላሽ ታካሚዎች የሕክምና ማዕከል ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በቅዱስ ማርቲኖ የተመላላሽ ታካሚዎች የሕክምና ማዕከል  (@Vatican Media)

ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ፥ በቫቲካን የቅዱስ ማርቲኖ የተመላላሽ ታካሚዎች ማዕከልን መርቀው ከፈቱ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ አምዶች ዙሪያ አዲስ የተከፈተውን የሕክምና ማዕከልን በመመረቅ አገልግሎቱን እንዲጀምር አድርገዋል። ማዕከሉ ለድሆች የሚሰጡ የጤና እንክብካቤ አገልግሎቶችን የሚያሰፋ እና የጎዳና ላይ ነዋሪዎችን የሚያጠቁ የተለመዱ በሽታዎችን በፍጥነት ለመመርመር የሚያግዝ የራዲዮሎጂ ክፍልን የሚያካትት እንደሆነ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ዓርብ ኅዳር 5/2018 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ አምዶች ሥር የሚገኘውን የቅዱስ ማርቲኖ የተመላላሽ ታካሚዎች ክሊኒክን መርቀዋል። ዓለም አቀፍ የድሆች ቀን ከሚከበርበት ማለትም ከእሑድ ኅዳር 7/2018 ዓ. ም. በፊት በሮቹን ለድሆች የከፈተው አዲሱ የሕክምና መስጫ ማዕከሉ ከዚህ በፊት “የምሕረት እናት” በሚል ስያሜ የተከፈተው እና ከቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ አጠገብ የሚገኝ ክሊኒክ ከተመረቀ ከአሥር ዓመታት በኋላ እንደሆነ ታውቋል።


ድሆች እንክብካቤን ለማግኘት ወደ ቤተ ክርስቲያን የሚመጡበት ቦታ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ዓርብ ኅዳር 5/2018 ዓ. ም. ጠዋት በሮም የሚገኝ የላቴራን ጳጳሳዊ ዩኒቨርሲቲ የትምህርት ዓመት መጀመሪያ ሥነ-ሥርዓትን ከተካፈሉ በኋላ እኩለ ቀን አካባቢ ወደ ቫቲካን ተመልሰው፥ በቅዱስ ማርቲኖ መንደር በሚገኙ የበርኒኒ አምዶች ዙሪያ ለረጅም ጊዜ ድሆችን በመቀበል ወደሚታወቅ አካባቢ ደርሰዋል።

ቦታው መጠለያ ለሌላቸው የጎዳና ላይ ተዳዳሪዎች የገላ መታጠቢያ፣ ጸጉር መስተካከያ እና የ “ምሕረት እናት ክሊኒክ” የሚገኝበት ሲሆን፥ ነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የመኖሪያ ፈቃድ፣ የገንዘብ ድጋፍ እና የጤና አጠባበቅ ዕርዳታ የማግኘት ዕድል ለሌላቸው ድጋፍን ለመስጠት ብለው ያቋቋሙት እንደሆነ ይታወቃል።

ወደ ሥፍራው ሲደርሱ በቅድሚያ ክሊኒኩን የጎበኙት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳስ ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ በሐዋርያዊ ጽሕፈት ቤት የምጽዋት ሰብሳቢ ክፍል አስተባባሪ እና የር. ሊ. ጳ. የበጎ አድራጎት ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ ከብጹዕ ካርዲናል ኮንራድ ክራየስኪ ጋር በመሆን የተመላላሽ ታካሚዎች ክሊኒክ ዳይሬክተር ዶ/ር ማሲሞ ራሊን እና በቫቲካን ከተማ ግዛት የጤና እና የንፅህና ዳይሬክተር ዶ/ር ሉዊጂ ካርቦኔ ጋር ተገናኝተዋል።

ብጹዕ ካርዲናል ኮንራድ ለቫቲካን የዜና አገልግሎት እንደገለጹት፥ የቅዱስነታቸው ጉብኝት የግል ጉብኝት በመሆኑ እና ለማንም ያልተነገረ በመሆኑ በሥራ ላይ የነበሩ ዶክተሮች ብቻ በሥፍራው እንደ ነበሩ አስረድተው፥ ዓርብ ኅዳር 5/2018 ዓ. ም. ጠዋት ቅዱስነታቸው ወደ ቦታው ሲደርሱ ለ65 ሰዎች የሕክምና ዕርዳታ ሰጠው የሸኙት 8 ዶክተሮች፣ 4 ነርሶች እና 2 በጎ ፈቃደኞች የነበሩ ሲሆን፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ሰላምታቸውን ከሰጡ በኋላ ስለ ክሊኒኩ እንቅስቃሴዎች ጠይቀዋቸዋል።

የአእምሮ ጤና እንክብካቤ

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት የበጎ አድራጎት ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ኮንራድ ክራየስኪ በገለጻቸው፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ከዶክተሮቹ መካከል የአእምሮ ሐኪሞችም መኖራቸው ሲያውቁ በመገረም፥ “ድሆቻችን እንዲህ ዓይነት እንክብካቤ ያስፈልጋቸዋል” ማለታቸውን አስታውሰው፥ ዶክተሮቹ ሮም ውስጥ ከሚገኝ ጄሜሊ ካቶሊክ ሆስፒታል የመጡ መሆናቸውን እና አገልግሎታቸውን በትዕግስት የሚሰጡት ብዙ ስለሚሠሩ እና ሰዎች ስለሚያምኑባቸው ነው” ሲሉ አክለዋል።

አዲስ አገልግሎትን መጀመር

“ጥሩ ሥራ በመሆኑ አመሰግናችኋለሁ” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ የቅዱስ ማርቲኖ የተመላላሽ ታካሚዎች ክሊኒክን ወደነበረበት ለመመለስ የሠሩትን በሙሉ አመስግነው፥ የበጎ አድራጎት ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ባወጣው መግለጫ መሠረት ማዕከሉ ዘመናዊ የሕክምና ቴክኖሎጂ እና የራዲዮሎጂ ክፍል የተገጠመላቸው ሁለት ክፍሎች እንዳሉት ታውቋል።

የኤክስሬይ ማሽኖች ቀጣዩ ትውልድ የሳንባ ምች፣ የአጥንት ስብራት፣ ዕጢዎች፣ የኩላሊት ጠጠር፣ የአንጀት ችግሮችን እና ብዙውን ጊዜ በድህነት ውስጥ በሚኖሩ ሰዎች መካከል ችላ የሚባሉትን በሽታዎችን በፍጥነት እና በትክክለኛው መንገድ ለመመርመር የሚያስችሉ እንደሆኑ ተመልክቷል። እነዚህ ምርመራዎች ዶክተሮች በተቻለ ፍጥነት ተገቢውን ሕክምና እንዲጀምሩ የሚያስችላቸው እና ድሆች የተሻለ የኑሮ ጥራት እንዲኖራቸው የሚያደርጉ መሆናቸው ታውቋል።

የቅዱስ ማርቲኖ የተመላላሽ ታካሚዎች ማዕከል ውስጥ ከሚሠሩ በጎ ፈቃደኞች መካከል
የቅዱስ ማርቲኖ የተመላላሽ ታካሚዎች ማዕከል ውስጥ ከሚሠሩ በጎ ፈቃደኞች መካከል

በድሆች ውስጥ ኢየሱስን ማየት

አዲሱ ክሊኒክ ከቫቲካን ከተማ ግዛት የጤና እና የንፅህና ዳይሬክቶሬት ጋር በመተባበር የተቋቋመ ሲሆን የሕክምና እርዳታ ለሚፈልጉ በሙሉ ሁሉን አቀፍ እንክብካቤን እንደሚሰጥ ታውቋል። ሁለቱ ክሊኒኮች ለተቸገሩት መልካም አቀባበልን የሚያደርጉ የፈውስ ቦታዎች መሆናቸውን ብጹዕ ካርዲናል ኮንራድ ገልጸው፥ “ዕርዳታን የሚሹ ቤት የሌላቸውን ሰዎች ኢየሱስ ክርስቶስን የምናይባቸው ሰዎች ናቸው” ሲሉ አፅንዖት ሰጥተዋል።

በወር ወደ 2,000 የሚጠጉ ሰዎች እንክብካቤን እንደሚያገኙ የገለጹት ብጹዕ ካርዲናል ኮንራድ፥ ሁሉም ዓይነት እንክብካቤዎች ሙሉ በሙሉ ከክፍያ ነፃ መሆናቸውን እና የመድኃኒት ማዘዣም እንደሚሰጣቸው፥ በስዊዘርላንድ ዘቦች እና በቫቲካን የጸጥታ አስከባሪዎች ሰላምታ ተሰጥቷቸው ወደ ቫቲካን ከገቡ በኋላ የመድኃኒት ማዘዣቸውን ወደ ቫቲካን ፋርማሲ በማቅረብ ያለ ክፍያ መድሃኒቶችን እንደሚቀበሉ በማስረዳት ይህ አገልግሎታቸው ድሆች ከሌሎች የተገለሉ አለመሆናቸውን ወይም የበታችነት እንዳይሰማቸው ለመከላከል እንደሚረዳ አፅንዖት ሰጥተዋል።

በቅዱስ ማርቲኖ የተመላላሽ ታካሚዎች ማዕከል ውስጥ ልዩ ልዩ ሕክምናን የሚሰጡ ክፍሎች
በቅዱስ ማርቲኖ የተመላላሽ ታካሚዎች ማዕከል ውስጥ ልዩ ልዩ ሕክምናን የሚሰጡ ክፍሎች

በሐዋርያዊ ጽሕፈት ቤት የምጽዋት ሰብሳቢ ክፍል አስተባባሪ እና የር. ሊ. ጳ. የበጎ አድራጎት ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ ብጹዕ ካርዲናል ኮንራድ ክራየስኪ፥ ዓለም አቀፍ የድሆች ቀን ከሚከበርበት ህዳር 7/2018 ዓ. ም.  ቀደም ብለው ባስተላለፉት መልዕክት፥ “እኔ አማኝ፣ የካቶሊክ እምነት ተከታይ እና አመክኖዬም ቅዱስ ወንጌልን መመስከር ነው” ብለው፥ ኢየሱስ ክርስቶስ እርቃኑን የነበረ፣ ታስሮ፣ ታሞ እና ተደድዶ እንደነበር መናገር እንችላለን ብለው፥ ለድሆች የምናደርገው በሙሉ በዓለም በተለያዩ ገጽታዎች ራሱን ለሚያሳይ ለእርሱ ለኢየሱስ ክርስቶስ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ የሕክምና መስጫ ማዕከልን መርቀው ሲክፍቱ
ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ የሕክምና መስጫ ማዕከልን መርቀው ሲክፍቱ   (@Vatican Media)

 

15 Nov 2025, 20:00