ፈልግ

በቱርክዬ የተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ አያስከተለው አደጋ በቱርክዬ የተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ አያስከተለው አደጋ 

የር. ሊ. ጳ. ሊዮ የቱርክዬ ሐዋርያዊ ጉብኝት ሁለተኛውን የቫቲካን ጉባኤ መንፈስ ለማነቃቃት ዕድል የሚሰጥ መሆኑ ተነገረ

የቀድሞው የአናቶሊያ ሐዋርያዊ ተወካይ የነበሩት ብጹዕ አቡነ ፓውሎ ቢዜቲ፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ወደ ቱርክዬ የሚያደርጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት በተመለከተ ከቫቲካን ዜና ጋር ቃለ ምልልስ አስድርገዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ብጹዕ አቡነ ፓውሎ ቢዜቲ ለቫቲካን የዜና አገልግሎት እንደገለጹት፥ “አገሪቱን በጎዳው የመሬት መንቀጥቀጥ በኋላ ካሉት ወራት ጎን ለጎን የድሮውን የመለያየት ግድግዳን ለማፍረስ እና ነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እንደሚሉት፥ በሃይማኖቶች መካከል የሚደረግ ጥልቅ ውይይት በተለይም ድሆችን ማገልገል መሆኑን ለማሳየት በርትተን ሠርተናል” ሲሉ ተናግረዋል።

እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከ2019 ዓ. ም. ጀምሮ እስከ ጥቂት ቀናት ድረስ የካሪታስ ቱርክዬ ካቶሊካዊ የዕርዳታ ድርጅት ፕሬዝዳንት ሆነው ያገለገሉት ብጹዕ አቡነ ፓውሎ ቢዜቲ፥ በአገሪቱ ውስጥ በሃይማኖቶች መካከል ያለው ትብብር ለብዙ ዓመታት ካጋጠሟቸው እጅግ ትርጉም ካላቸው ልምዶች መካከል አንዱ አድርገው እንደሚመለከቱት ገልጸዋል።

እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከ2015 እስከ 2024 ዓ. ም. ድረስ የአናቶሊያ የላቲን ሐዋርያዊ ተወካይ የነበሩት እና አካባቢውን በሚገባ የሚያውቁት ብጹዕ አቡነ ፓውሎ ቢዜቲ፥ ከቫቲካን ዜና ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በቱርክዬ ከሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት በፊት አስተያየታቸውን እና ተስፋቸውን አጋርተዋል።

የቅዱስነታቸው ሐዋርያዊ ጉብኝት ዋና ዓላማ የመጀመሪያውን የኒቂያ ጉባኤ 1700ኛ ዓመት ክብረ በዓል ላይ ለመገኘት ሲሆን፥ ቅዱስነታቸው በተጨማሪም አንካራን፣ ኢስታንቡልን እና በአንድ ወቅት ኒቂያ በመባል ይታወቅ የነበረውን ኢዝኒክን እንደሚጎበኙ ታውቋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በቱርክዬ የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ዋና ዓላማ መንጋውን በአካል መጎብኘት እና የመልካሙን እረኛ ቅርበት ማምጣት እንደሆነ ብጹዕ አቡነ ፓኦሎ ቢዜቲ ገልጸው፥ የቱርክዬ እጅግ አስፈላጊነት የሚታወቀው ባለፈው የአንጾኪያ እና የኦሮንቴስ የክርስትና ታሪክ ብቻ ሳይሆን በዘመናዊው ቱርክዬ የክርስትና ሕይወት ሕያውነት ጭምር እንደሆነ አስረድተዋል።

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ሐዋርያዊ ጉብኝት ለክርስቲያኖች አንድነት ትልቅ ዕድል እንደሆነ የኒቂያ በዓል ጉባኤ አባቶች ያነቃቃውን መንፈስ ለማደስ እንደሚረዳ፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ 23ኛ እንዳሳሰቡት፥ “እምነትን በአዲስ ቃላት መግለጽ፣ አንድ የሚያደርግ መንገድ መፈለግ እና ይህ ሁልጊዜ እንደገና መጀመር ያለብን ተግባር ነው” ሲሉ ብጹዕ አቡነ ፓውሎ ቢዜቲ ተናግረዋል።

ብጹዕ አቡነ ፓውሎ ቢዜቲ፣ በቫቲካን የዜና አገልግሎት ጣቢያ
ብጹዕ አቡነ ፓውሎ ቢዜቲ፣ በቫቲካን የዜና አገልግሎት ጣቢያ

ቱርኪዬ በፖለቲካ ላይ የተመሠረተ የእስልምና እምነት፣ ባሕላዊ የእስልምና ሃይማኖት፣ የሱፊ እና የአሌቪ እንቅስቃሴዎች ያሉባት እና በቁጥር አናሳ የክርስትና እምነት ተከታዮች ያሉባት አገር መሆኗን ገልጸው፥ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ አገልግሎት በሕግ እና በልማድ በእጅጉ የተገደበ እንደሆነ እና ይህም ጸሎት ቤቶችን፣ የወጣቶች እና የባሕል ማዕከላትን ለመገንባት አስቸጋሪ ማድረጉን እና ሁሉም ነገር የሚከናወነው ከመቶ ዓመት በፊት በሎዛን ስምምነት መሠረት በተቋቋሙ ጥቂት ቁምስናዎች ውስጥ መሆኑን አስረድተዋል።

በሶርያ እና በቱርኪዬ የድንበር አካባቢዎች መካከል እንደ ጎርጎሮሳውያኑ የካቲት 6/2023 ዓ. ም. በሬክተር መለኪያ 7.8 የሚደርስ የመሬት መንቀጥቀጥ በመከሰቱ ከ50,000 በላይ ሰዎች መሞታቸውን በማስመልከት እንደተናገሩት፥ እውነተኛው የሟቾች ቁጥር ከተጠቀሰው በላይ እንደሆነ እና በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መፈናቀላቸውን ገልጸዋል። ውጤቶቹ አሁንም በድሃው ማኅበረሰቦች ዘንድ ከፍተኛ ጫና መፍጠሩን አስረድተዋል። በካሪታስ ካቶሊካዊ የዕርዳታ ድርጅት በኩል አስቸኳይ ጥረቶችን እንዲያደርጉ ያስገደዳቸው ችግር እንደ ነበር ገልጸው፥ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ለማድረግ ከአካባቢው እና ከሀገር አቀፍ የዕርዳታ ድርጅቶች ጋር በመተባበር ላደረጉት ዕርዳታ ወደ አንካራ ተጠርተው በይፋ ምስጋና ማግኘታቸው እንዳስደሰታቸው ገልጸዋል። “ይህ ከዚህ በፊት ያልተከሰተ እና ሰዎችን ያለ ምንም ልዩነት የሚረዳ ድርጅት እንደመሆናችን እውቅና ተሰጥቶናል” ሲሉ ተናግረው፥ “እንደ ካቶሊካዊነታችን ከአራቱም የምድር ማዕዘኖች በልግስና የደረሰውን ዕርዳታ በአግባቡ በመጠቀም አነስተኛ አስተዋፅዖ በማድረጋችን ኩራት ይሰማናል” ብለዋል።

ከመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ በኋላ ካሉት ወራት ጎን ለጎን፥ የነበረውን የልዩነት ግድግዳን ለማፍረስ እና ነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እንደሚሉት፥ በሃይማኖቶች መካከል የሚደረግ ጥልቅ ውይይት በተለይም ድሆችን ማገልገል መሆኑን ለማሳየት በኅብረት በርትተን ሠርተናል” ሲሉ ተናግረዋል።

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ሐዋርያዊ ጉብኝት ለቱርኪዬ የካሪታስ ሠራተኞች የእግዚአብሔር ሕዝብ አካል ሆኖ የመሰማት አስደሳች አጋጣሚ እንደሚሆን ገልጸው፥ ክርስቲያኖች ዘወትር በአገልግሎት በመተባበር ተጋላጭ የሆኑት ሰዎችን በማገልገል እና በመንከባከብ የሁሉም አገልጋይ የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን የሚከተሉ መሆናቸውን የቀድሞው የአናቶሊያ ሐዋርያዊ ተወካይ የነበሩት ብጹዕ አቡነ ፓኦሎ ቢዜቲ ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር በነበራቸው ቆይታ አስረድተዋል።

የቅድስት መንበር መግለጫ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በቱርክዬ እና በሊባኖስ ከህዳር 18-23/2018 ዓ. ም. ድረስ ሐዋርያዊ ጉብኝት እንደሚያደርጉ ማስታወቁ ይታወሳል።

 

11 Nov 2025, 16:52