ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የስደተኞች መንፈሳዊ መብት ሊከበር እንደሚገባ አሳሰቡ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
በሮም አቅራቢያ ወደሚገኝ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ማረፊያ ሰኞ አመሻሽ ላይ የሄዱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ በሰሜን አሜሪካ ውስጥ ለሚገኙ ስደተኞች ተገቢ እንክብካቤ እና ድጋፍ እንዲደረግላቸው ጥሪ አቅርበዋል። ቅዱስነታቸው በካስቴል ጋንዶልፎ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት፥ “በአሜሪካ ውስጥ ለዓመታት የኖሩ ብዙ ሰዎች ችግሮችን በሚያስከትሉ የመንግሥት የጅምላ ማፈናቀል ፖሊሲ በጥልቅ ተጎድተዋል” ብለው፥ በርካታ ስደተኛ እስረኞች ከቤተሰቦቻቸው መለያየታቸውን እና ምን እየተከናወነ እንዳለ ማንም እንደማያውቅ ተናግረዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ቺካጎ ውስጥ የታሰሩት ካቶሊክ ስደተኞች ቅዱስ ቁርባንን እንዳይቀበሉ መከልከላቸውን በተመለከተ ከጋዜጠኛ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡ፥ “የቤተ ክርስቲያኒቱ ሚና ወንጌልን መስበክ ነው” ሲሉ ተናግረው፥ ወንጌላዊው ማቴዎስ ስለ መጨረሻው ፍርድ የጻፈውን በመጥቀስ፥ “ኢየሱስ ክርስቶስ በዓለም መጨረሻ “እንግዳ ሆኜ ተቀብላችሁኛል” በማለት በግልጽ መናገሩን በማስታወስ በስደተኞች መንፈሳዊ መብቶች መጠበቅ አስፈላጊነት አፅንዖት ሰጥተዋል።
“የመንግሥት ባለሥልጣናት የቤተ ክርስቲያኒቱ አገልጋዮች የስደተኞችን ፍላጎት ማስተናገድ እንዲፈቅዱላቸው ጠይቀው፥ ስደተኞቹ ለብዙ ጊዜ ከቤተሰቦቻቸው መለያየታቸውን በመግለጽ ምን እየተፈጠረ እንዳለ ማንም ሰው የማያውቅ መሆኑን ተናግረዋል።
በአሜሪካ እና በቬንዙዌላ መካከል የተፈጠሩ ውጥረቶች
በአሜሪካ እና በቬንዙዌላ መካከል እየጨመረ የመጣው ውጥረት ያሰጋቸው መሆኑን የገለጹት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ የአሜሪካ የአደንዛዥ ዕፅ ሱሰኝነትን ለመከላከል ስትል በቬንዙዌላ ውሃ አቅራቢያ የባሕር ኃይሏን አሰማርታለች ቢባልም ነገር ግን የቬንዙዌላው ፕሬዝዳንት ኒኮላስ ማዱሮ፥ አሜሪካ የቬንዙዌላን ነዳጅን ለመያዝ የአገዛዝ ለውጥ ማድረግን እንደ ሰበብ አድርጋለች” ማለታቸውን ገልጸዋል።
“ዓመፅ ፈጽሞ ድል እንደማያመጣ አምናለሁ” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ የጦር መርከቦች ወደ ቬንዙዌላ የባህር ዳርቻ እየተቃረቡ መሆናቸውን የሚገልጹ ዘገባዎችን ማንበባቸውን ገልጸው፥ “ዋናው ነገር በውይይት በአገሮች መካከል ሊኖሩ የሚችሉ ችግሮችን ለመፍታት ፍትሃዊ መንገዶችን መፈለግ ነው” ሲሉ አሳስበዋል።
በመካከለኛው ምሥራቅ ያለው አስጊ ሁኔታ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በመቀጠልም፥ በመካከለኛው ምሥራቅ ስላለው ሁኔታን በማስመልከት ለተጠየቁት ጥያቄ ምላሽ ሰጥተዋል። የተኩስ አቁም ስምምነቱ በአዳዲስ የእስራኤል ጥቃቶች እና በዌስት ባንክ በሚገኙ መንደሮች ላይ ከሠፋሪዎች በሚሰነዘሩ ጥቃቶች ስጋት ላይ መውደቁን ገልጸዋል።
“ቢያንስ የሰላም ስምምነቱ የመጀመሪያ ምዕራፍ አሁንም እንደቀጠለ ነው” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ የተኩስ አቁም ስምምነቱ ደካማ መሆኑን ከመናገራቸው በፊት በመስከረም 30/2018 ዓ. ም. በእስራኤል እና በሃማስ መካከል የተደረሰውን ስምምነት በመጥቀስ ተናግረዋል።
የሁሉም ሕዝቦች መብቶች በማረጋገጥ ወደ ሁለተኛው ምዕራፍ መሻገር አስፈላጊ መሆኑን አፅንዖት ሰጥተው፥ በዌስት ባንክ ውስጥ ያለው የእስራኤል ሠፈራዎች ጉዳይ በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት ሕገ-ወጥ መሆኑን እና ጉዳዩ ውስብስብ መሆኑን በመናገር ለሁሉም ሕዝቦች ፍትህ በጋራ መሥራት እንደሚገባ አፅንዖት ሰጥተዋል።
የሥራ ክቡርነት
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በተጨማሪም፥ በሮም ውስጥ የሚገኝ ጥንታዊ የኮንቲ ሕንጻ በከፊል በመደርመሱ ምክንያት የሞተውን የ66 ዓመት አዛውንት በማስታወስ በሰጡት አስተያየት የሠራተኞችን የመብት ጉዳይ አንስተዋል። “አንድ ሰው ለቤተሰቡ የሚያስፈልገውን ሁሉ ለማቅረብ የሚያስችለውን የተከበረ ሥራ ማግኘት የሰው ልጅ መብት ነው” ሲሉም አስተያየታቸውን ገልጸዋል።
“ቤተ ክርስቲያን ብዙ ማድረግ ትችላለች” ሲሉ ገልጸው፥ ሆኖም ግን መጪው የሠራተኞች ኢዮቤልዩ ተስፋን ለመስጠት እና በችግሮች ላይ አስተያየት ለመስጠት ብቻ ሳይሆን መፍትሄን ለማግኘት እና ጥረቶችን ለማስተባበር ዕድል እንደሚሆን አክለው ገልጸዋል።
የቀጠለው የሩፕኒክ ጉዳይ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ወደ ቫቲካን ከመመለሳቸው በፊት፣ የቀድሞው የኢየሱሳውያን ማኅበር ካኅን እና አርቲስት ማርኮ ሩፕኒክ ጉዳይ በአሁኑ ጊዜ በቅድስት መንበር የእምነተ አንቀጽ ጳጳሳዊ ጽሕፈት በኩል እየታየ መሆኑን ገልጸዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ አሁንም በዓለም ዙሪያ በብዙ አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ በመታየት ላይ የሚገኙ የሩፕኒክ የጥበብ ሥራዎች በማስመልከት ለሚነሱ ጥያቄዎች ምላሽ ሲሰጡ፥ “በብዙ ቦታዎች የጥበብ ሥራዎቹ ከዕይታ መታገዳቸውን እና ከድረ-ገጾችም መወገዳቸውን በእርግጠኝነት የምናውቀው ነገር ነው” ሲሉ ተናግረው፥ የቫቲካን ችሎት ጉዳዩን በቅርቡ መመልከት መጀመሩን አረጋግጠዋል።
“ዳኞች መሾማቸን እና ሂደቶቹ ጊዜ ይወስዳሉ” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ ተጎጂዎች ትዕግስት እንዲያደርጉ መጠየቅ በጣም ከባድ ቢሆንም ነገር ግን ቤተ ክርስቲያኗ የሁሉንም ሰው መብት ማክበር አለባት” ሲሉ ተናግረው፥ ጥፋተኛ መሆኑ እስኪረጋገጥ ድረስ ንፁህ መሆን በቤተ ክርስቲያኑ ውስጥም እንደሚሠራ ገልጸው፥ “ሂደቱ በጉዳዩ ላይ ለተሳተፉት በሙሉ ግልጽነትን እና ፍትህን እንደሚያመጣ ተስፋ እናደርጋለን” ብለዋል።
