ር. ሊ. ጳ. ሊዮ በቅድስት ማርያም ባዚሊካ ውስጥ ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስን በጸሎት አስታወሱ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ለሳምንታዊ የዕረፍት ጊዜ ወደ ካስቴል ጋንዶልፎ ማረፊያቸው ከመጓዛቸው በፊት ሰኞ ማታ ከምሽቱ ሁለት ሰዓት ገደማ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም “ባዚሊካ”ን ወይም ጳጳሳዊ ቤተ ክርስቲያንን ከተሳለሙ በኋላ በውስጡ በሚገኝ የነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መካነ መቃብር ፊት ጸሎታቸውን አቅርበዋል።
የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መንፈሳዊነት በሚያሳይ እና ነጭ የጽጌረዳ አበባ ዘወትር በማይጠፋበት የሊሲው ቅድስት ተሬዛ መታሰቢያ ሐውልት ባለበት ቦታ በሚገኝበት መካነ መቃብር ላይ ነጭ የጽጌረዳ አበባን አስቀምጠዋል። በሁለት ጸሎት ቤቶች መካከል የሚገኘው የነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መካነ መቃብር፥ ከጸሎት ቤቶቹ አንዱ የሮም ከተማ ነዋሪዎች ጠባቂ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቅዱስ ምስል በክብር የተቀመጠበት ሲሆን፥ ይህም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከእያንዳንዱ ዓለም አቀፍ ሐዋርያዊ ጉብኝት በፊት እና በኋላ እንዲሁም ከሆስፒታል ከወጡ በኋላ ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አደራን የሰጡበት እና ምስጋናን የሚያቀርቡበት ጸሎት ቤት መሆኑ ይታወቃል።
የቅድስት መንበር መግለጫ እንደ ገለጸው፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛም ሰኞ ጥቅምት 24/2018 ዓ. ም. ማምሻውን ወደ ካስቴል ጋንዶልፎ ከማቅናቸው በፊት በእመቤታችን ቅድስት ማርያም ቅዱስ ምስል ፊት ቀርበው ጸሎታቸውን ካቀረቡ በኋላ ጉዞአቸውን መቀጠላቸውን አስታውቋል።
ለር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ መታሰቢያነት የተዘጋጀ የመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓት
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ቀደም ሲል፥ ባለፈው ዓመት ላረፉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ለብጹዓን ካርዲናሎች እና ጳጳሳት መታሰቢያነት የተዘጋጀውን መስዋዕተ ቅዳሴ በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ አሳርገዋል።
የመስዋዕተ ቅዳሴውን ሥነ-ሥርዓት በታላቅ ፍቅር የፈጸሙት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በስብከታቸው ላይ እንደተናገሩት፥ ነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ቅዱስ በርን ከፍተው ለሮም እና ለመላው ዓለም የብርሃነ ትንሳኤውን ቡራኬ መስጠታቸውን አስታውሰዋል። ዘንድሮ እየተከበረ ለሚገኘው የኢዮቤልዩ በዓል ምስጋና ይግባው” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ በሐዋርያዊ የመሪነት ስልጣን ወቅት የሚያከብሩት የመጀመሪያ በዓል በመሆኑ የክርስቲያን ተስፋ ልዩ ጣዕም እና ትርጉም ያለው መሆኑን አስረድተዋል።
“ይህ ተስፋ ከቅርብ ወራት በፊት ያረፉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እና ሌሎች ብጹዓን ጳጳሳት በተጨባጭ የኖሩት፣ የመሰከሩት እና ያስተማሩት ነው” ብለው፥ ቀደም ሲል ባገኟቸው አጋጣሚዎች በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ባዚሊካ ወደሚገኘው መካነ መቃብር ያደረጓቸውን ጉብኝቶች አስታውሰዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ለሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ መንበር ከተመረጡበት ከሁለት ቀናት በኋላ ማለትም ቅዳሜ ግንቦት 2/2017 ዓ. ም. የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን መካነ መቃብር መጎብኘታቸው ይታወሳል። መካነ መቃብሩ በየቀኑ በርካታ ምዕመናን እና መንፈሳዊ ነጋዲያን የሚጎበኙት ሲሆን፥ በወቅቱ አዲስ የተመረጡት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ወደ ባዚሊካው ሄደው በመካነ መቃብሩ ላይ አበባ በማስቀመጥ ጸሎት ማቅረባቸው ይታወሳል። እሑድ ሰኔ 15/2017 ዓ. ም. ከቅዱስ ዮሐንስ ዘላተራን ጳጳሳዊ ባዚሊካ እስከ ቅድስት ማርያም ጳጳሳዊ ባዚሊካ ድረስ ከተደረገው የኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ሥጋ እና ደም ዑደት በኋላ በመቃብሩ ላይ አበባን በማስቀመጥ ጸሎት ማቅረባቸው ይታወሳል።
