ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ‘ጡረታ ለመውጣት አስቤ ነበር፣ ግን በምትኩ ለእግዚአብሔር እጅ ሰጠሁ’ አሉ!
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን
ስለ ዩክሬን በተመለከተ፣ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ የአውሮፓን ተሳትፎ እና ጣሊያን ልትጫወተው የምትችለውን አስፈላጊ ሚና አፅንዖት ሰጥተዋል፣ እንዲሁም ሲመተ ርዕሰ ሊቃነ ጵጵስና ያጎናጸፋቸውን ምርጫ እንዴት ምላሽ እንደሰጡ ለሚለው ጥያቄ መልስ ሰጥተዋል፣ የአንድን ሰው ሕይወት ለእግዚአብሔር መስጠት እና “መንገዱን እንዲመራ” መፍቀድ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ አፅንዖት ሰጥተው ቅዱስነታቸው ተናግረዋል።
“በመጀመሪያ፣ ይህን ያህል ጠንክረው ለሠሩ ሁሉ አመሰግናለሁ ማለት እፈልጋለሁ፤ ይህንን መልእክት በቱርክ ሆነ በሊባኖስ ላሉ ሌሎች ጋዜጠኞች፣ የዚህን ጉዞ አስፈላጊ መልእክቶች ለማስተላለፍ ለሠሩት ጭምር እንድታስተላልፉ እፈልጋለሁ። ለዚህ ጉብኝት ሁላችሁም ትልቅ ጭብጨባ ይገባችኋል” ሲሉ ቅዱስነታቸው ንግግራቸውን ጀምረዋል።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ከቤሩት ወደ ሮም በበረራ ላይ የነበሩትን 81 ጋዜጠኞች በእነዚህ ቃላት ተቀብለው በርካታ ጥያቄዎችን በመመለስ በእንግሊዝኛ፣ በጣሊያንኛ እና በስፓኒሽ ቋንቋዎች ተናግረዋል።
ስለተጠናቀቀው ሐዋርያዊ ጉዞአቸው፣ ስለ መካከለኛው ምስራቅ፣ በዩክሬን ስላለው ጦርነት፣ ስለ አውሮፓ በሰላም ድርድር መገኘት እና ስለ ቬንዙዌላ ሁኔታ ተናግረዋል።
ከሊባኖስ ዘጋቢም ስጦታ ተቀብለዋል፡ በቅርብ ቀናት በቴሌቪዥን በቀጥታ የተፈጠረ በእጅ የተሰራ ሥዕል፣ እሱን እና በሴዳር ምድር የጎበኟቸውን ተምሳሌታዊ ቦታዎች ያሳያል።
ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በወቅቱ ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ የሰጡትን ምላሽ እንደ የሚከተለው አሰናድተንዋል ተከታተሉን።
ጥያቄ፡ ከጋዜጠኛ ጆ ፋርቻክ (LBC International): የሰላም ሂደትን የሚመሩ የአሜሪካዊ ጳጳስ ነዎት። ጥያቄዬ ከፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና ከጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ ጋር ያለዎትን ግንኙነት ይጠቀማሉ ወይ የሚለው ነው። በአውሮፕላን ላይ ቫቲካን የእስራኤል ወዳጅ እንደሆነች ተናግረዋል። እስራኤል በሊባኖስ ላይ የምታደርሰውን ጥቃት የማስቆም ጉዳይ አንስተዋልን? እናም በክልሉ ውስጥ ዘላቂ ሰላም ሊኖር ይችላል?
መልስ፡ [ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፣ በእንግሊዝኛ ቋንቋ]፡- በመጀመሪያ ደረጃ፣ አዎ፣ ዘላቂ ሰላም ሊደረስበት የሚችል ነው ብዬ አምናለሁ። ስለ ተስፋ ስንነጋገር፣ ስለ ሰላም ስንነጋገር፣ የወደፊቱን ስንመለከት፣ ሰላም እንደገና ወደ ክልሉ መጥቶ ወደ ሀገርህ፣ ወደ ሊባኖስ መምጣት እንደሚቻል ስለማምን ነው ብዬ አስባለሁ።
እንደ እውነቱ ከሆነ፣ በጣም በትንሹ መንገድ፣ ከጠቀስካቸው የአገራት መሪዎች ጋር ጥቂት ውይይቶችን ጀምሬያለሁ፣ እና ያንን በግል ወይም በቅድስት መንበር በኩል ማድረግን ለመቀጠል አስቤ ነበር፣ ምክንያቱም እውነታው ግን ከአብዛኛዎቹ የክልሉ አገሮች ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ስላለን፣ እናም ዛሬ በመስዋዕተ ቅዳሴው ማብቂያ ላይ የተናገርኩትን የሰላም ጥሪ ማቅረባችንን መቀጠል በእርግጥ ተስፋችን ይሆናል።
ጥያቄ፡ ኢማድ አትራች (ስካይ ኒውስ አረቢያ)፡- በመጨረሻው ንግግሮ ላይ ለሊባኖስ ባለስልጣናት ግልጽ መልእክት ተላልፏል። ለመደራደር፣ ለመነጋገር፣ ለመገንባት ውይይት ያስፈልጋል ሲሉ ተናግረዋል። ቫቲካን በዚህ ረገድ ተጨባጭ ነገር ታደርጋለች ወይ? ትላንት ማታ ከእስልምና የሺዓ እምነት ተወካይ ጋር ተገናኝተዋል። ከጉብኝቶ በፊት ሂዝቦላህ መልእክት ልኮውሎት ነበር፤ አንብበው እንደሆነ ግን አላውቅም። ስለዚህ ምን ልትነግሩን ይችላሉ? ሊባኖስን ስለጎበኙ በጣም አመሰግናለሁ፤ ይህም ለእኛ ህልም ነበር።
መልስ፡ [ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት በጣሊያንኛ]፡- የዚህ ጉዞ አንድ ገጽታ፣ ዋናው ምክንያት ያልሆነው - ጉብኝቱ የተፀነሰው የኒቂያ ጉባኤ ጭብጥን፣ ከካቶሊክ እና ከኦርቶዶክስ ፓትርያርኮች ጋር የተደረገውን ስብሰባ እና በቤተክርስቲያን ውስጥ አንድነትን ለማምጣት ነው - ነገር ግን እንደ እውነቱ ከሆነ፣ በዚህ ጉዞ ወቅት፣ የፖለቲካ ባለስልጣናትን፣ ከውስጣዊ ግጭቶች ወይም ከክልሉ ዓለም አቀፍ ግጭቶች ጋር ግንኙነት ያላቸውን ሰዎች ወይም ቡድኖችን የሚወክሉ የተለያዩ ቡድኖች ተወካዮችን አግኝቻለሁ።
ሥራችን በዋናነት በጎዳናዎች ላይ የምናውጀው የህዝብ ነገር አይደለም፤ ከትዕይንቱ በስተጀርባ ነው። ተፋላሚ ወገኖቹ የጦር መሣሪያዎችን እንዲያስቀምጡ፣ ዓመፅን እንዲተው እና ወደ ውይይት ጠረጴዛ እንዲመጡ ለማሳመን አስቀድመን ያደረግነው እና የምናደርገው ነገር ነው፡- ጠበኛ ያልሆኑ ነገር ግን የበለጠ ውጤታማ ሊሆኑ የሚችሉ መልሶችን እና መፍትሄዎችን መፈለግ ነው ተግባራችን።
ጥያቄ፡ ኢማድ አትራች፡ ከሂዝቦላህ የተላከውን መልእክት ተመልክተውታል ወይ?
መልስ፡ አዎ፣ አይቼዋለሁ። በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው፣ በቤተክርስቲያኗ በኩል የጦር መሣሪያዎቻቸውን እንዲያስቀምጡ እና ውይይት ለማድረግ ሀሳብ አለ። ከዚህ ባሻገር ግን በዚህ ጊዜ አስተያየት መስጠት አልፈልግም።
ጥያቄ፡ ሲንዲ ውደን፣ ከሲኤንኤስ (CNS)፡ ቅዱስ አባታችን፣ ከጥቂት ወራት በፊት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት መሆን የመማሪያ አቅጣጫ እንዳለው ተናግረዋል። ትላንት ሃሪሳ ሲደርሱ፣ ሞቅ ያለ አቀባበል ሲደረግሎት፣ 'ዋው' እንዳሉ ይመስል ነበር። ምን እየተማሩ እንደሆነ ሊነግሩኝ ይችላሉን? ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት በመሆኖ ለመማር በጣም አስቸጋሪው ነገር ምንድን ነው? እና በኮንክሌቪ (የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ምርጫ ሂደት) ውስጥ ምን እየተከናወነ እንዳለ ግልጽ ሲሆን ምን እንደተሰማዎ ምንም ነገር አልተናገሩም። ስለዚያ ትንሽ ሊነግሩን ይችላልን?
መልስ፡ [ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት፣ በእንግሊዝኛ ቋንቋ]፡- የመጀመሪያ አስተያየቴ ከአንድ ወይም ከሁለት ዓመት በፊት እኔም አንድ ቀን ጡረታ ለመውጣት አስቤ ነበር የሚል ነው። ያንን ስጦታ እንደተቀበልኩ በግልጽ ያሳያል፤ አንዳንዶቻችን መስራታችንን እንቀጥላለን።
ኮንክላቪ (የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ምርጫ ሂደት) ራሱ፣ እኔ እንደማምነው፣ የኮንክላቩን ምስጢር በተመለከተ በጣም ጥብቅ ነው፣ ምንም እንኳን አንዳንድ ነገሮች የተገለጡባቸው የሕዝብ ቃለመጠይቆች እንደነበሩ አውቃለሁ። ከመመረጤ አንድ ቀን በፊት ለአንድ ዘጋቢ እንዲህ ነገርኩት፣ በመንገድ ላይ ያዘችኝ፣ ከቅዱስ አጎስጢኖስ ማሕበር አባላት ጋር (አውጉስቲኒያውያን) ጋር ምሳ ለመብላት እየሄድኩ ነበር፣ እና እሷም “ምን ይመስሎታል? ከተወዳዳሪዎቹ አንዱ ሆነዋል!” ስትል ተየቀችኝ፣ እኔም “ሁሉም ነገር በእግዚአብሔር እጅ ነው” አልኳት። ይህንንም በጥልቅ አምናለሁ።
ከእናንተ አንዱ፣ እዚህ ውስጥ አንድ የጀርመን ጋዜጠኛ አለ፣ በሌላ ቀን፣ ፕሬቮስት (ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ተብለው ከመጠራታቸው በፊት ካርዲናል ሉዊስ ማሪየስ ፕሬቮስት ተብለው ይጠሩ ነበር) ማን እንደሆነ ለመረዳት ማንበብ የምንችለውን አንድ ቅዱስ አጎስጢኖስ የተመለከተ መጽሐፍ ንገረኝ ብሎኝ ነበር።
እናም ብዙ አስቤ ነበር፣ ነገር ግን ከእነዚህ ውስጥ አንዱ “የእግዚአብሔር መገኘት ልምምድ” የሚባል መጽሐፍ ነው። ከብዙ ዓመታት በፊት የተጻፈው የአያቱን ሥም እንኳን የማይጠቅሰው በወንድም ላውረንስን የተጻፈ በጣም ቀለል መጽሐፍ ነው።
ነገር ግን፣ ከፈለጉ፣ አንድ ሰው ሕይወቱን ለጌታ የሚሰጥበት እና ጌታ እንዲመራ የሚፈቅድበትን የጸሎት እና የመንፈሳዊነት ዓይነት ይገልጻል። ስለ እኔ የሆነ ነገር ማወቅ ከፈለጉ፣ ለብዙ ዓመታት መንፈሳዊነቴ ሆኖ ቆይቷል።
በታላቅ ፈተናዎች መካከል፣ በፔሩ ለዓመታት በሽብርተኝነት ዘመን መኖር፣ ለማገልገል እጠራለሁ ብዬ ባላሰብኩባቸው ቦታዎች ለማገልገል መጠራቴ ያስደንቀኛል። በእግዚአብሔር እታመናለሁ፣ እና ያ መልእክት ከሁሉም ሰዎች ጋር የማካፍለው ነገር ነው።
ታዲያ ምን ይመስል ነበር? ነገሮች እንዴት እየሄዱ እንደሆነ ሳየው ለእውነታው ራሴን አቀረብኩ፣ እናም ይህ እውን ሊሆን እንደሚችል ተናገርኩ። በጥልቀት ተነፈስኩ፣ 'እነኾኝ ጌታ ሆይ እዚህ አለሁኝ፣ አንተ ኃላፊነቱን ውሰድ፣ አንተ በመንገዴ ምራኝ' ብዬ ጸለይኩኝ።
ትላንት ማታ 'ዋው' እንዳልኩ አላስታውስም። የፊቴ ገጽታ የሁኔታዎች ገላጭ በጣም ይመስላል፣ ነገር ግን ጋዜጠኞቹ የፊቴን ገጽታ እንዴት እንደሚተረጉሙት ባላውቅም ብዙ ጊዜ ግን እደሰታለሁ። ማለቴ አስደሳች ነው፤ አንዳንድ ጊዜ ከሁላችሁም በጣም ጥሩ ሀሳቦችን እቀበላለሁ፣ ምክንያቱም አእምሮዬን ወይም የፊቴን ገጽታ ማንበብ እንደምትችሉ አድርጋችሁ ታስባላችሁ። እናም ይህ ግን ሁል ጊዘ እውነት አይደለም - ሁልጊዜ ትክክል አይደላችሁም።
ማለቴ፣ እዚያ ከ1 ሚሊዮን በላይ ወጣቶች በነበሩበት በኢዩቤሊዩ ላይ ተሳትፌ ነበር። ትላንት ማታ ጥቂት ሰዎች ነበሩ። ለእኔ ሁልጊዜ ድንቅ ነው፤ ‘እነዚህ ሰዎች እዚህ ያሉት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱን ለማየት ስለሚፈልጉ ነው’ ብዬ ለራሴ አስባለሁ፤ ነገር ግን በተለይ በዚህ ጉዳይ ‘እዚህ ያሉት ኢየሱስ ክርስቶስን ለማየት ስለሚፈልጉና የሰላም መልእክተኛ ማየት ስለሚፈልጉ ነው’ እላለሁ።
ስለዚህ ጉጉታቸውን ማዳመጥ እና ለዚያ መልእክት የሚሰጡትን ምላሽ መስማት እኔ እንደማስበው - ያ ጉጉት አስደናቂ ነው። እነዚህ ሁሉ ወጣቶች የሚያሳዩትን ሁሉ ከማድነቅ ፈጽሞ እንደማልሰለች ተስፋ አደርጋለሁ።
ጥያቄ፡ ጂያን ጊዶ ቬቺ (ኮሪዬሬ ዴላ ሴራ): በአሁኑ ጊዜ በኔቶ እና በሩሲያ መካከል ከፍተኛ ውጥረት ያለበት ጊዜያት ናቸው፤ ስለ ድብቅ ጦርነት፣ የሳይበር ጥቃቶች ተስፋዎች እና እንደዚህ ዓይነት ነገሮች ወሬ አለ። የኔቶ መሪዎች እንደዘገቡት ግጭት የመባባስ አደጋ፣ በአዲስ መንገድ ወደፊት የመሄድ አደጋን ይታዮታል ወይ? እናም በዚህ የአየር ሁኔታ፣ በቅርብ ወራት ውስጥ በአሜሪካ ፕሬዝዳንትነት በስርዓት የተገለለው የአውሮፓ አህጉር ከሌለ ፍትሃዊ ሰላም ለማግኘት ድርድር ሊኖር ይችላል?
መልስ፡ [ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት፣ በጣሊያንኛ ቋንቋ]፡ ይህ በግልጽ ለዓለም ሰላም አስፈላጊ ጉዳይ ነው፣ ነገር ግን የቅድስት መንበር ቀጥተኛ ተሳትፎ የላትም፣ ምክንያቱም እስካሁን ድረስ የኔቶ አባላትም ሆኑ የማንኛውም ውይይት አባላት ስላልሆንን፣ እና ብዙ ጊዜ ለጦርነት ሳይሆን ለውይይት የተኩስ አቁም ጥሪ ብናቀርብም።
እናም አሁን በብዙ ገጽታዎች የተሞላ ጦርነት ነው፡ የጦር መሳሪያዎች መጨመር፣ ሁሉም የጦር መሳሪያዎች ማምረት፣ የሳይበር ጥቃቶች፣ ጉልበት መጠቀም። አሁን ክረምት እየመጣ ነው፣ እዚያም ከባድ ችግር አለ።
በአንድ በኩል፣ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ሊያራምዱት የሚፈልገውን የሰላም እቅድ ማስተዋወቅ እንደሚችሉ እና ቢያንስ መጀመሪያ ላይ የአውሮፓ አህጉር የማይሳተፍበት መሆኑን እያሰቡ እንደሆነ ግልጽ ነው።
ነገር ግን የአውሮፓ መገኘት አስፈላጊ ነው፣ እና ያ የመጀመሪያ ሀሳብ አውሮፓ በምትለው ምክንያትም ተሻሽሏል።
በተለይ፣ የጣሊያን ሚና በጣም አስፈላጊ ሊሆን ይችላል ብዬ አስባለሁ። በባህልና በታሪክ፣ ጣሊያን በተለያዩ ወገኖች መካከል በሚፈጠር ግጭት መካከል እንደ አማላጅ የመሥራት አቅም አላት፤ ዩክሬን፣ ሩሲያ፣ አሜሪካ…
በዚህ መልኩ፣ ቅድስት መንበር እንዲህ ዓይነቱን ሽምግልና ሊበረታታ እንደሚችል እና አንድ ሰው በዚህ ጉዳይ ላይ በዩክሬን ውስጥ በእውነት ሰላምን፣ ፍትሃዊ ሰላምን የሚያመጣ መፍትሄ መፈለግ እንዳለበት እና አብረን መፈለግ እንዳለብን ልጠቁም እችላለሁ።
ጥያቄ፡ ኤሊሳቤታ ፒኬ (La Nación): የሊባኖስ ባንዲራ ከፔሩ ባንዲራ ጋር ተመሳሳይ ቀለሞች አሉት። ይህ በሚቀጥለው ዓመት ሁለተኛ አጋማሽ ላይ ላቲን አሜሪካን እንደሚጎበኙ የሚያሳይ ምልክት ነው፣ ከአርጀንቲና እና ከኡራጓይ ጋር በማጣመር? ቀልዱን ወደ ጎን ብንተወው፣ ለሚመጣው ዓመት ምን ጉብኝቶችን እያዘጋጁ ነው? በተጨማሪም፣ ስለ ላቲን አሜሪካ ስንናገር፣ በቬንዙዌላ ውስጥ በሚሆነው ነገር ምክንያት ከፍተኛ ውጥረት አለ። ከፕሬዚዳንት ትራምፕ እስከ ማዱሮ ድረስ ሥልጣናቸውን ለማስለቀቅ እና በወታደራዊ ዘመቻ እሱን ለማስወገድ የሚያስፈራራ የመጨረሻ ጊዜ ላይ ደርሰናል። ስለዚህ ምን ያስባሉ?
መልስ፡ [ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት፣ በስፓኒሽ ቋንቋ]፡- ስለ መጪ ሐዋርያዊ ጉብኝቶች ምንም እርግጠኛ ነገር የለም፤ አፍሪካን ለመጎብኘት ተስፋ አደርጋለሁ። ያ ምናልባት ቀጣዩ ጉዞ ሊሆን ይችላል።
ጥያቄ፡ ወ/ሮ ፒኬ፡ የት አገር?
አፍሪካ፣ አፍሪካ። በግሌ፣ የቅዱስ አውጉስጢኖስ የትውልድ ቦታዎችን ለመጎብኘት ወደ አልጄሪያ ለመሄድ ተስፋ አደርጋለሁ፣ ነገር ግን በክርስቲያን ዓለም እና በሙስሊሙ ዓለም መካከል ድልድዮችን ስለመገንባት የሚደርገውን ውይይት እና ንግግር ለመቀጠል ወደ እዚያ ለመሄድ አቅጃለሁ። ቀደም ሲል፣ በሌላ ቦታ፣ ስለዚህ ርዕስ የመናገር እድል አግኝቼ ነበር። አስደሳች ነው፡ የቅዱስ አውጉስጢኖስን ምስል እንደ ድልድይ መመልከቱ ብዙ ይረዳል፣ ምክንያቱም በአልጄሪያ እንደ ትውልድ አገሩ ልጅ በጣም የተከበረ ነው። ያ አንድ ነገር ነው።
ከዚያም ሌሎች አገሮች አሉ፣ ግን በእሱ ላይ እየሰራን ነው። በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው፣ የሊቀ ጳጳሱን ጉብኝት የሚጠብቁትን ላቲን አሜሪካ፣ አርጀንቲና እና ኡራጓይን መጎብኘት በጣም እፈልጋለሁ። ፔሩም እንደምትቀበለኝ አስባለሁ፣ እና ወደ ፔሩ ከሄድኩ ብዙ ጎረቤት አገሮችም ይኖራሉ፣ ነገር ግን እቅዱ ገና አልተገለጸም።
ስለ ቬንዙዌላ፣ በጳጳሳት ጉባኤ ደረጃ እና ከቅድስት መንበር ልዑክ ጋር፣ ሁኔታውን ለማረጋጋት መንገድ ለማግኘት እየሞከርን ነው፣ ከሁሉም በላይ የሕዝቡን ጥቅም እንፈልጋለን፣ ምክንያቱም በእነዚህ ሁኔታዎች ውስጥ የሚሰቃዩት ሰዎች ናቸው፣ ባለሥልጣናት አይደሉም።
ከዩናይትድ ስቴትስ የሚመጡት ምልክቶች ይለወጣሉ? ስለዚህ ማየት አለብን… በአንድ በኩል፣ በሁለቱ ፕሬዚዳንቶች መካከል የስልክ ውይይት የተደረገ ይመስላል፤ በሌላ በኩል፣ ይህ አደጋ፣ ይህ እድል፣ እርምጃ፣ የቬንዙዌላ ግዛትን ወረራ ጨምሮ ሊሆን ይችላል።
በዚህ ጫና ውስጥ ውይይት መፈለግ የተሻለ ነው ብዬ አምናለሁ፣ የኢኮኖሚ ጫናን ጨምሮ፣ ነገር ግን ዩናይትድ ስቴትስ ለማድረግ የወሰነችው ለውጥ ለማምጣት ሌላ መንገድ መፈለግ ተገቢ ነው።
ጥያቄ፡ ሚካኤል ኮሬ (La Croix ፕሬስ)፣ ሰላም ቅዱስነዎ፣ ለዚህ በጣም አስደሳች ጉዞ አመሰግናለሁ። በተለያዩ ዓለማት መካከል ድልድይ መገንባትን ስለመቀጠል ተነጋግረዋል። መጠየቅ እፈልጋለሁ፡ በአውሮፓ ያሉ አንዳንድ ካቶሊኮች እስልምና ለምዕራቡ ዓለም የክርስትና ማንነት ስጋት ነው ብለው ያምናሉ። ትክክል ናቸው ወይ? እናም ለእነርሱ ምን መላሽ ይሰጧቸዋል?
መልስ፡ [ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት፣ በእንግሊዝኛ ቋንቋ]፡ በቱርክ ሆነ በሊባኖስ በነበርኩበት ጊዜ ያደረግኳቸው ውይይቶች በሙሉ፣ ከብዙ ሙስሊሞች ጋር ጨምሮ፣ በትክክል ስለ ሰላምና ለተለያዩ ሃይማኖቶች ሰዎች አክብሮት በሚመለከት ርዕስ ላይ ያተኮሩ ነበሩ።
እንደ እውነቱ ከሆነ፣ ሁልጊዜ እንደዚያ እንዳልሆነ አውቃለሁ። በአውሮፓ ውስጥ ብዙ ጊዜ የሚፈጠሩ ፍርሃቶች እንዳሉ አውቃለሁ፣ ነገር ግን ብዙ ጊዜ የሚፈጠሩት ከስደት ጋር በተቃረኑ እና ከሌላ ሀገር፣ ከሌላ ሃይማኖት፣ ከሌላ ዘር የመጡ ሰዎችን ለማራቅ በሚሞክሩ ሰዎች ነው።
በዚህ መልኩ፣ ሁላችንም አብረን መሥራት እንዳለብን እላለሁ፣ የዚህ ጉዞ እሴቶች አንዱ በሙስሊሞችና በክርስቲያኖች መካከል ውይይትና ጓደኝነት ሊኖር እንደሚችል የዓለምን ትኩረት በትክክል ማሳደግ ነው።
ሊባኖስ ለዓለም ልታስተምር የምትችላቸው ታላላቅ ትምህርቶች አንዱ እስልምናና ክርስትና ሁለቱም የሚገኙበትን እና የሚከበሩበትን እና ጓደኛ ለመሆን አብረው የመኖር እድል እንዳለ በትክክል ማሳየት ነው ብዬ አስባለሁ።
ባለፉት ሁለት ቀናት ውስጥ እንኳን ሰዎች እርስ በርስ ሲረዳዱ የሰማናቸው ታሪኮች፣ ምስክርነቶች፤ ለምሳሌ፣ ሁለቱም መንደሮቻቸው የወደሙባቸው ሙስሊሞች ከክርስቲያኖች አንድ ላይ ተሰባስበን አብረን መስራት እንደምንችል ይናገሩ ነበር።
እነዚህ ትምህርቶች በአውሮፓ ወይም በሰሜን አሜሪካም ጭምር መሰማታቸው አስፈላጊ ናቸው ብዬ አስባለሁ። ምናልባት ትንሽ ፍርሃት ሊኖረን እና እውነተኛ ውይይት እና አክብሮትን የማሳደግ መንገዶችን መፈለግ አለብን።
ጥያቄ፡ አና ጆርዳኖ (ከArd Radio)፡- በሊባኖስ የምትገኘው ቤተክርስቲያን በጀርመን ቤተክርስቲያንም ትደግፋለች። ለምሳሌ፣ በሊባኖስ ውስጥ በጣም ንቁ የሆኑ አንዳንድ የጀርመን የእርዳታ ድርጅቶች አሉ። ስለዚህ ከዚህ አንፃር የጀርመን ቤተክርስቲያን ጠንካራ ቤተክርስቲያን ሆና መቀጠሏ አስፈላጊ ነው። ስለዚህ ምናልባት ይህ በጀርመን ቋንቋ (ሲኖዳለር ዌግ)፣ ሲኖዶሳዊ መንገድ፣ በጀርመን ቤተክርስቲያን ውስጥ የለውጥ ሂደት እንዳለ ይታወቃል። ይህ ሂደት ቤተክርስቲያንን ለማጠናከር መንገድ ሊሆን ይችላል ብለው ያስባሉ? ወይስ በተቃራኒው ነው? እና ከሆነስ ለምን?
መልስ፡ [ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት፣ በእንግሊዝኛ ቋንቋ]፡- የሲኖዶሳዊ መንገድ ለጀርመን ብቻ አይደለም፤ መላው ቤተክርስቲያን ባለፉት በርካታ ዓመታት ሲኖዶስ እና ሲኖዶሳዊነትን አክብራለች።
አንዳንድ ታላላቅ ተመሳሳይነቶች አሉ፣ ነገር ግን በጀርመን የሲኖዶሳዊ መንገድ እንዴት ወደ ፊት እንደሄደ እና በአለም አቀፍ ቤተክርስቲያን ውስጥ እንዴት እንደሚቀጥል... በነዚህ መካከል ጉልህ ልዩነቶችም አሉ። በአንድ በኩል፣ ለባህል አክብሮት በእርግጥ ቦታ አለ እላለሁ።
በአንድ ቦታ ሲኖዶሳዊነት በተወሰነ መንገድ የሚኖር መሆኑ እና በሌላ ቦታ ደግሞ በተለየ መንገድ የሚኖር መሆኑ ስብራት ወይም መፈረካከስ አለ ማለት አይደለም። ይህን ማስታወስ በጣም አስፈላጊ ይመስለኛል።
በተመሳሳይ ጊዜ፣ በጀርመን ውስጥ ብዙ ካቶሊኮች እስካሁን ድረስ በጀርመን ሲከበሩ የቆዩት አንዳንድ የሲኖዶሳዊነት መንገድ ገጽታዎች ለቤተክርስቲያኗ ወይም ለራሳቸው የቤተክርስቲያኗ የአኗኗር ዘይቤ የራሳቸውን ተስፋ እንደማይወክሉ እንደሚያምኑ አውቃለሁ።
ስለዚህ የማንም ድምጽ እንዳይገለል፣ በጀርመን ውስጥ ተጨማሪ ውይይት እና ማዳመጥ ያስፈልጋል፣ ስለዚህ የበለጠ ኃያላን የሆኑት ሰዎች ድምጽ በጣም ብዙ ሊሆኑ የሚችሉ፣ ነገር ግን ለመናገር ቦታ የሌላቸውን እና የራሳቸውን ድምጽ እና የቤተክርስቲያን ተሳትፎ መግለጫዎች እንዲሰሙ መፍቀድ።
በተመሳሳይ ጊዜ፣ እንደምታውቁት፣ የጀርመን ጳጳሳት ቡድን ባለፉት ሁለት ዓመታት ከሮማ ኩሪያ የመጡ ካርዲናሎች ቡድን ጋር ሲገናኝ ቆይቷል። የጀርመን ሲኖዶሳዊ መንገድ እንደ ዓለም አቀፋዊው ቤተክርስቲያን መንገድ ተደርጎ ሊወሰድ ከሚገባው ነገር እንዳይላቀቅ ለማድረግም ቀጣይ ሂደት አለ።
ይህ እንደሚቀጥል እርግጠኛ ነኝ። በጀርመን በሁለቱም ወገኖች አንዳንድ ማስተካከያዎች እንደሚደረጉ እገምታለሁ፣ ነገር ግን ነገሮች በአዎንታዊ መልኩ እንደሚሰሩ ተስፋ አደርጋለሁ።
ጥያቄ፡ ሪታ ኤል-ሙናየር (Sat-7 International)፡- በመካከለኛው ምስራቅ እና በሰሜን አፍሪካ የሚተላለፉ አራት የተለያዩ የክርስቲያን ቻናሎች ነን፣ ሁለቱ በአረብኛ፣ አንዱ በፋርሲ እና አንዱ በቱርክ ቋንቋ። በመጀመሪያ ደረጃ፣ ለሊባኖስ ሕዝብ ጊዜ ስለሰጡን አመሰግናለሁ። እኔ ራሴ የጦርነት ዘመን ልጅ ነኝ፣ እናም ከቅዱስነትዎ እቅፍ በማድረግ፣ ትክሻዬን መታ መታ በማድረግ እና ሁሉም ነገር ደህና ይሆናል በማለት መናገርዎ ምን ያህል ትርጉም እንዳለው አውቃለሁ። እናም 'በአንዱ ሁላችንም አንድ ነን' የሚለው አርማዎ ያስገረመኛል፣ ይህ አርማ በተለያዩ የክርስትና እምነቶች፣ በሃይማኖቶች እና በባልንጀራዎቻችን መካከል ድልድይ ስለመገንባት ይናገራል፣ ይህም አንዳንድ ጊዜ ትንሽ አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል። ስለዚህ ጥያቄዬ፣ ከእርሶ እይታ አንጻር፣ በመካከለኛው ምስራቅ የምትገኘው ቤተክርስቲያን - እንባዋን፣ ቁስሏን፣ ተግዳሮቶቿን እና ያለፈውን ታሪክዋን ጨምሮ - ለምዕራቡ ዓለም ቤተክርስቲያን ምን ልዩ ስጦታ ልትሰጥ ትችላለች?
መልስ፡ [ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት፣ በእንግሊዝኛ ቋንቋ]፡ ዛሬ በጣም ግለሰባዊ በሆነ ማህበረሰብ ውስጥ ያደጉ - በወረርሽኙ ወቅት ብዙ ጊዜ ያሳለፉ ወጣቶች - እና የግል ግንኙነታቸው ብዙውን ጊዜ በጣም የተገለለ፣ በእውነቱ በኮምፒውተር ስክሪኖች ወይም በስማርትፎኖች በኩል ብቻ ስለሆነ - አንዳንድ ጊዜ 'አንድ መሆን ለምን እንፈልጋለን? እኔ ግለሰብ ነኝ፣ እና ለሌሎች ግድ የለኝም' ብለው ይጠይቃሉ።
እና እዚህ ለሁሉም ሰዎች አንድነት፣ ጓደኝነት፣ የሰው ልጅ ግንኙነቶች፣ ኅብረት እጅግ በጣም አስፈላጊ እና እጅግ በጣም ጠቃሚ እንደሆኑ የሚገልጽ በጣም አስፈላጊ መልእክት እንዳለ አስባለሁ። በሌላ ምክንያት ካልሆነ፣ በጦርነት ውስጥ የኖረ ወይም የተሰቃየ እና በህመም ላይ ያለ ሰውን በተመለከተ የጠቀሽው ምሳሌ፣ እቅፍ ለእነሱ ምን ማለት ሊሆን እንደሚችል በመግለጽ ልጀምር።
ያ በጣም ሰብዓዊ፣ እውነተኛ፣ ጤናማ የግል እንክብካቤ መግለጫ የሌላ ሰውን ልብ ለመፈወስ ምን ሊያደርግ ይችላል። በግል ደረጃ፣ ይህ የጋራ ደረጃ ሊሆን ይችላል፣ ሁላችንንም አንድ የሚያደርግ፣ እንድንረዳ የሚያግዘን፣ እና እርስ በርስ መከባበር ‘ርቀታችሁን ጠብቁ፤ እኔ እዚህ እቆያለሁ፣ እናንተም እዚያ ትቆያላችሁ፣ ምንም ዓይነት መስተጋብር አይኖረንም’ ማለት ሳይሆን ነገር ግን ሁሉንም ሰዎች የሚያበለጽጉ ግንኙነቶችን መገንባት ማለት ነው።
በዚህ መልእክት፣ በእርግጥ፣ የእኔ መፈክር በዋናነት በክርስቶስ ምክንያት ‘አንድ በሆነው በክርስቶስ ሁላችንም አንድ ነን’ የሚል ነው።
ነገር ግን፣ ከፈለጉ ለክርስቲያኖች ብቻ የተገለጸ አይደለም። እንደ እውነቱ ከሆነ፣ ለሁላችንም ሆነ ለሌሎች የምንጋብዘው ነው፡- በዓለም ላይ እውነተኛ አንድነትንና መግባባትን፣ አክብሮትንና ሰብዓዊ የወዳጅነት እና የውይይት ግንኙነቶችን በምናሳድግበት መጠን፣ የጦር መሳሪያዎችን ወደ ጎን የመተው፣ ብዙ ጊዜ የተገነባውን አለመተማመንን፣ ጥላቻን፣ ጥልን ወደ ጎን የመተው እና በዓለም ዙሪያ እውነተኛ ሰላምንና ፍትህን የማስፈን መንገዶችን የምናገኝበት ዕድል ሰፊ ነው።
