ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ “ሰላምን እንደ ግብ ብቻ ሳይሆን እንደ መንገድ መምረጥ አለብን” ሲሉ አሳሰቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በቱርክ እና በሊባኖስ የሚያደረጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት አጠናቅቀው ወደ ሮም ከመጓዛቸው በፊት በቤሩት አየር ማረፊያ በተዘጋጀ የሽኝት ሥነ-ሥርዓት ላይ ንግግር አድርገዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ቅዱስነታቸው በንግግራቸው ለመካከለኛው ምሥራቅ የውይይት፣ የወንድማማችነት እና የእርቅ ጥሪን በማቅረ በአሁኑ ጊዜ እራሳቸውን አንዱ ለሌላው ጠላት አድርገው የሚቆጥሩ ሰዎች የወንድማማችነት እና የሰላም ቁርጠኝነት መንፈስ እንደሚላበሱ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ማክሰኞ ኅዳር 23/2018 ዓ. ም. በቤሩት ራፊክ ሃሪሪ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ በተዘጋጀው ይፋዊ የስንብት ሥነ-ሥርዓት ላይ በቱርክ እና በሊባኖስ ያደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ለክልሉ በሙሉ የወንድማማችነት እና የሰላም ራዕይን አጉልቶ እንደሚሳይ በመግለጽ የ6 ቀናት ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን አጠናቀዋል።

በሊባኖስ ያሳለፏቸውን ሦስቱን ቀናት መለስ ብለው ተመልክተው በሰጡት አስተያየት፥ የአገሪቱን የበለጸገ መንፈሳዊ ቅርስ እና የሕዝቦቿን ጽናት በማስታወስ፥ ክርስቲያኖችም ሆኑ ሙስሊሞች በጋራ ለቅድስት ድንግል ማርያም ያላቸውን ጥልቅ አክብሮት አድንቀዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ የቅዱስ ቻርቤልን መቃብር መጎብኘታቸውን በማስታወስ እንደተናገሩትም፥ የሊባኖስን ታሪክ ወደ ሰላማዊ የወደፊት ጉዞ የሚያደርስ እንደሆነ ተናግረዋል።

አገሪቱን እያጋጠሟት ያሉ ቀጣይነት ያላቸው ችግሮችን ችላ ሳይሉ፥ ከቤሩት የወደብ ፍንዳታ ሰለባዎች ጋር ያላቸውን አጋርነት በመግለጽ “በመላው ሊባኖስ የሚገኙ የብዙ ቤተሰቦች የእውነት እና የፍትህ ጥማትን እሸከማለሁ” ብለዋል።

ሰላምን እንደ ግብ ብቻ ሳይሆን እንደ መንገድ መምረጥ

ሊጎበኟቸው ያልቻሏቸው ቦታዎችን ጨምሮ ለሁሉም የሊባኖስ ክልሎች ሕዝቦች ሰላምታ አቅርበው፥ ትሪፖሊን እና ሰሜናዊውን ክልል፣ ቤቃን እና በአሁኑ ጊዜ በግጭት እና በጥርጣሬ ሁኔታ ውስጥ የሚገኘውን ደቡባዊውን ክልል አስታውሰዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ጦርነት እንዲቆም ጥሪ በማቅረብ፥ “የትጥቅ ትግል ምንም ጥቅም እንደማያመጣ፣ የጦር መሣሪያዎች ገዳይ እንደሆኑ፤ ድርድር፣ ሽምግልና እና ውይይት ገንቢ መሆናቸውን መገንዘብ እና ሁላችንም ሰላምን እንደ ግብ ብቻ ሳይሆን እንደ መንገድ መምረጥ አለብን!” ብለዋል።

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ቃላትን በመጥቀስ፥ “ሊባኖስ ከአገርነት በላይ መልዕክትም ጭምር ናት!” ካሉ በኋላ በመጨረሻም “ይህ እውን እንዲሆን አብረን መሥራትን እና ተስፋ ማድረግን እንማር” ብለዋል።

ለር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ በቤሩት አየር ማረፊያ የተዘጋጀ የሽኝት ሥነ-ሥርዓት

 

02 Dec 2025, 17:36