ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ቅድስት ድንግል ማርያም የሰውን ልጆች እንድትጠብቅ በጸሎት ጠየቁ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የአዳም ኃጢአት ያልነካት መሆኗ በካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ሕገ ቀኖና ከታወጀበት ከ100 ዓመታት ወዲህ በሮም በሚገኝ የጽንሰተ ማርያም ሐውልት ሥር አበባ የማስቀመጥ ልማድ የተጀመረው በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፒዮስ 12ኛ ሐዋርያዊ የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ጊዜ መሆኑ ይታወሳል።
ከጥቂት ዓመታት በኋላ ማለትም እንደ ጎርጎሮሳያኑ በ1958 ዓ. ም. ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ 23ኛ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሐውልት ወደሚገኝበት ሥፍራ ሄደው በግርጌው ነጭ የጽጌረዳ አበባን ማኖራቸውም ይታወሳል።
በቀደሙት ርዕሣነ ሊቃነ ጳጳሳት የተጀመረውን ይህን የበርካታ ዓመታት ልማድ ተከትለው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የጽንሰተ ማርያም በዓል በተከበረበት ኅዳር 29/2018 ዓ. ም. በ “ፒያሳ ዲ ስፓኛ” በሚገኝ የጽንሰተ ማርያም ሐውልት ሥር ነጭ የጽጌረዳ አበባን አኑረዋል።
ለእመቤታች ቅድስት ድንግል ማርያም ጊዜን መስጠት
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ወደ ቦታው ሲደርሱ መዘምራን እና ምዕመናን በኅብረት፥ “ከንጋት ብርሃን ይበልጥ ውብ ሆነሽ ታይተሻል” የሚል የእመቤታችን ማርያም ዝማሬን አሰምተዋል። የሮም ሰበካ ረዳት ጳጳስ ብጹዕ ካርዲናል ባልዳዛሬ ሬይና እና የሮም ከንቲባ አቶ ሮቤርቶ ጓልቲየሪ ለቅዱስነታቸው አቀባበል አድርገውላቸዋል።
ከሥነ-ሥርዓቱ የመክፈቻ ጸሎት በኋላ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ 12 ሜትር ርዝመት ካለው የጽንሰተ ማርያም ሐውልት ግርጌ የአበባ እቅፍ ካስቀመጡ በኋላ ከመዘምራን እና ምዕመናን ጋር ሆነው ወደ ቅድስት ድንግል ማርያም ዘንድ የሚቀርብ ጸሎት “ሊጣኒያ” ካደረሱ በኋላ የሚከተለውን ጸሎት አድርሰዋል፥
“ጸጋን የተሞላሽ ማርያም ሆይ! እግዚአብሔር በውስጣቸው መኖሩን እንደሚያሳይ ገር ብርሃን በጸጋ የተሞላሽ ቅድስት ድንግል ማርያም ሆይ ደስ ይበልሽ! ይህ ምስጢር ከመጀመሪያው ጀምሮ ባንቺ ውስጥ ሆኖ ከእናትሽ ማኅፀን ጀምሮ ታላላቅ ነገሮችን ማከናወን ጀምሯል። ብዙም ሳይቆይ ላንቺ የቀረበልሽ የአዎንታዊነት ጥያቄ ሌሎች በርካቶችን አዎንታዊነታቸውን እንዲገልጹ አድርጓቸዋል።
ንጽሕት ሆይ! የታማኝ ሕዝብ እናት ሆይ! ያንቺ ንጽሕና የሮም ከተማን በዘላለማዊ ብርሃን አሸብርቆታል፤ አንቺ የሄድሽበት መንገድ ዛሬ እኛ ከምናቀርብልሽ አበቦች ይበልጥ የሮም ጎዳናዎችን በመልካም መዓዛ ሞልቶታል። ንጽሕት ድንግል ሆይ! ከመላው ዓለም የመጡ በርካታ ነጋዲያን ለዘመናት እና በዚህ የኢዮቤልዩ ዓመት ውስጥ በሮም ከተማ ጎዳናዎች ተራምደዋል። እግዚአብሔር በትህትናው ሕይወት ሰጪ መንፈሱን መላክ በማያቆምበት በዚህ የጥፋት ዓለም የሰው ልጅ ፈተና ውስጥ ይገኛል።
ማርያም ሆይ! ተስፋቸው ያልጠፋባቸው በርካታ ልጆችሽን ተመልከቺያቸው፤ እርሱ ሕያው ቃል የሆነው ልጅሽ ኢየሱስ ክርስቶስ በልባቸው ውስጥ የዘራው ዘር ይበልጥ ሥር እንዲሰድድ እና እንዲያድግ፤ በእያንዳንዱ ሰው ውስጥ ሥጋን፣ መልክን እና ድምጽን እንዲለብስ ይጠይቃል። እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሆይ! የኢዮቤልዩ ተስፋ በሮም እና በምድር ሁሉ ላይ፣ እግዚአብሔር በሚያዘጋጀው አዲስ ዓለም ውስጥ አንቺ እንደ ቡቃያ በማበብ የንጋት ብርሃን ሁኝለት። ከቅዱስ በር መከፈት በኋላ ሌሎች በሮችም እንዲከፈቱ፣ ክብር እንደገና የሚያብብበት፣ ሰዎች በሙሉ ሰላምን እና የእርቅ ጥበብን የሚማሩበት የሰላም ቤት በሮች እንዲሆኑ እንለምናለን።
በሕጻንነት እና በወጣትነት ዕድሜሽ እንደ ቤተ ክርስቲያን እናትነት ራስሽን ለእግዚአብሔር ፈቃድ ሙሉ በሙሉ ከፍተሽ በጥልቀት የናፈቀሽው የእግዚአብሔር መንግሥት ይምጣ! የዘመናችን ደስታ እና ተስፋ፣ ሐዘን እና ጭንቀት በሚንጸባርቅባቸው አካባቢዎች፣ በሮም እና በልዩ ልዩ ቦታዎች በሚገኙ ቤተ ክርስቲያናት ውስጥ በተለይም በድሆች እና በሚሰቃዩ ሰዎች መካከል አዳዲስ ሃሳቦች እንዲፈልቁ እርጂን።
ምስጢረ ጥምቀት የኢየሱስ ክርስቶስ አካል ሕያው አባላት የሆኑ ወንዶች እና ሴቶች ቅዱሳን እና ንጹሐን እንዲሆኑ፣ የእግዚአብሔርን ከተማ የሚገነቡ ምድራዊ አካላት እንዲሆኑ ያዘጋጃቸው። ያልተዘጋጁ እና አቅመ ቢሶች ለሚያደርጉ ለውጦች ለተጋፈጥን ለእኛ አማልጂን! ሕልሞቻችንን፣ ራእዮቻችንን እና ድፍረቶቻችንን አነሳሽልን! ለእግዚአብሔር የማይቻል ነገር እንደሌለ እና ይህንንም ብቻውን እንደማያደርግ ከማንም በላይ ታውቂዋለሽ።
በአንድ ወቅት አክስትሽን ኤልሳቤጥን ለመጎብኘት ቸኩለሽ ለስደት እና ለንግደት በነበረሽ ጉጉት የተባረክሽ ማርያም ሆይ! አንቺ ከሴቶች ሁሉ የተባረክሽ የልጅሽ የኢየሱስ ክርስቶስ የመጀመሪያ ደቀ መዝሙር የሆንሽ የእግዚአብሔር እናት ሆይ እኛም በዚህ እንድንባረክ ከእኛ ጋር ሁኚ!
ዘወትር ከሕዝብ እና በሕዝብ መካከል የምትገኝ ቤተ ክርስቲያን እንድንሆን እርጂን! ለፍትህ እና ለተስፋ በሚጮህ የሰው ልጅ መካከል እርሾዎች እንድንሆን እርጂን! ንጽሕት እና ማለቂያ የሌለው ውበት ያለሽ ማርያም ሆይ! በዚህች ከተማ ውስጥ የሚገኙ የሰው ልጆችን በሙሉ ጥብቂ! ወደ ልጅሽ ኢየሱስ ክርስቶስ አመልክቺያቸው፣ ምሪያቸው፣ አቅርቢያቸው። የሰላም ንግሥት እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሆይ ስለ እኛ ጸልዪልን!” በማለት ጸሎታቸውን አቅርበዋል።
