ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ሊዮ፥ ምዕመናን እንደ ማርያም በእምነት ለእግዚአብሔር የአዎንታ ምላሽ እንዲሰጡ አሳሰቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ የላቲን ሥርዓተ አምልኮን በሚከተሉ ካቶሊካዊ ምዕመናን ዘንድ የጽንሰተ ማርያም ዓመታዊ በዓል በተከበረበት ሰኞ ኅዳር 29/2018 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከተሰበሰቡት ምዕመናን ጋር እኩለ ቀን ላይ የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት አድርሰዋል። ቅዱስነታቸው በዕለቱ ባሰሙት ቃለ ምዕዳን፥ ምዕመናን እንደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በእምነት ለእግዚአብሔር አዎንታዊ ምላሽ እንዲሰጡ አሳስበዋል። ክቡራት እና ክቡራን የዝግጅታችን ተከታታዮች፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በዕለቱ ያሰሙትን ቃለ-ምዕዳን ትርጉም ሙሉ ይዘቱን እንደሚከተለው እናቀርብላችኋለን።

ክቡራት እና ክቡራን የዝግጅታችን ተከታታዮች፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በዕለቱ ያሰሙትን ቃለ-ምዕዳን ትርጉም ሙሉ ይዘቱን እንደሚከተለው እናቀርብላችኋለን።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

"ውድ ወንድሞች እና እህቶች፣ መልካም በዓል እንዲሆንላችሁ እመኛለሁ! ዛሬ የጽንሰተ ማርያም ዓመታዊ በዓል በማክበር ላይ እንገኛለን። የሰማይ አባት እግዚአብሔር ከመጀመሪያው ጀምሮ ማርያምን ኃጢአት እንዳይነካት ስለፈለገ ደስታችንን እንገልጻለን። “በንጽሕና እና በቅድስና ለተሞላች ቅድስት ድንግል ማርያም እግዚአብሔር አብ ከልቡ የሚወደውን አንድያ ልጁን ለእርሷ በአደራ ለመስጠት ፈለገ”። (የር. ሊ. ጳ. ፒዮስ 11ኛ “Ineffabilis Deus” የተሰኘ ሐዋርያዊ ድንጋጌ፥ ታህሳስ 8/1854 ዓ. ም. እ.አ.አ)፣

ጌታ እግዚአብሔር ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እጅግ ጥሩ የሆነውን የፍጹም ንጹህ ልብ ጸጋ ሰጥቷታል። በበለጠ ደግሞ አዳኙ ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ዓለም እንደ ሰው እንዲመጣ ያደረገው ተዓምር ነው (ሉቃ. 1፡31-33)። ቅድስት ድንግል ማርያም ይህንን ያውቀችው ትኅትና ከተመላበት ተዓምራዊ የመልአኩ ሰላምታ ነው። “ጸጋ የሞላብሽ ሆይ! እግዚአብሔር ከአንቺ ጋር ነው” (ሉቃ. 1፡28)። እርሷም፥ “እነሆ እኔ የጌታ ባሪያ ነኝ፤ እንደ ቃልሽ ይሁንልኝ” በማለት በእምነት መለሰችለት (ሉቃ. 1፡38)።

ቅዱስ አጎስጢኖስ እነዚህን ቃላት ሲገልጽ፥ “ማርያም አመነች፣ ያመነችውም በእሷ ተፈጸመ” ይላል (ስብከት 215፣ 4)። የጸጋ ሙላት ስጦታ ፍሬ በናዝሬቷ ወጣት ውስጥ ማፍራት የቻለው የእግዚአብሔርን ዕቅድ በነጻነት ስለተቀበለች ነው። እግዚአብሔር ዘወትር በዚህ መንገድ ይሠራል። እግዚአብሔር ታላላቅ ስጦታዎችን ይሰጠናል። ነገር ግን እንድንቀበላቸው ወይም እንዳንቀበላቸው በነፃነት ይተወናል። በዚህ ምክንያት ቅዱስ አጎስጢኖስ “እኛም እናምናለን፣ ምክንያቱም [በእሷ] የሆነው ነገር እኛንም ሊጠቅመን ይችላልና”። ስለዚህ በእግዚአብሔር እናት ያልተበከለ ውበት እንድንደሰት የሚያደርገን ይህ በዓል፥ እርሷ ያመነችውን እና እግዚአብሔር የጠራንን ተልዕኮ በልግስና እንድንቀበል የሚያደርገንን እንድናምን ይጋብዘናል።

ማርያም በተፀነሰችበት ጊዜ የተከናወነው ተዓምር በጥምቀት ታድሶልናል። ከአዳም ኃጢአት ነጻ አድርጎናል። የእግዚአብሔር ልጆች፣ ማደሪያው እና የመንፈሱ ቤተ መቅደስ ሆነናል። ማርያምም በልዩ ጸጋ ኢየሱስን በራሷ ተቀብላ ለሁሉም ሰው ልትሰጥ እንደቻለች ሁሉ፥ “ጥምቀት ክርስቶስ በእኛ እንዲኖር እና ከእርሱ ጋር አንድ ሆነን እንድንኖር፣ እያንዳንዳችን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንድንተባበር እና ለዓለም ለውጥ እንድንተባበር ያስችለናል” (ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ የጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምንሮ ሚያዝያ 11/2018 ዓ. ም. እ.አ.አ)።

የተወደዳችሁ ምዕመናን፥ ከኃጢአት ነጻ ሆኖ የመጸነስ ስጦታ ምንኛ ታላቅ ነው? የተቀበልነው የጥምቀት ስጦታም እንዲሁ ነው! የጌታ እናት አዎንታዊ ምላሽ ድንቅ ነው። የእኛም ይሁንታ በምስጋና፣ በትህትና እና በጽናት፣ በጸሎት እና በተጨባጭ የፍቅር ተግባራት፣ ከእጅግ ያልተለመዱ ምልክቶች እስከ ተራ ጥረቶች እና የአገልግሎት ተግባራት በየቀኑ በታማኝነት እየታደሰ እንደዚህ ሊሆን ይችላል። በዚህ መንገድ ኢየሱስ ክርስቶስ በሁሉም ዘንድ እና በሁሉም ሥፍራ ሊታወቅ፣ ተቀባይነት ሊኖረው እና ሊወደድ ይችላል፤ ድነት ለሁሉም ሊደርስ ይችላል።

በንጽሕት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት፥ እርሷ ለመጀመሪያ ጊዜ ያመነችበትን ተመሳሳይ ቃላት በመድገም ይህን ጸጋ እግዚአብሔርን እንዲሰጠን ዛሬ እንለምነው።” በማለት ቃለ ምዕዳናቸውን አጠቃልለዋል።

09 Dec 2025, 17:06