ፈልግ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በጦርነት ቀጣናዎች የሚኖሩ ክርስቲያኖችን በጸሎት መደገፍ እንደሚገባ አሳሰቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ ለታኅሳሰ ወር እንዲሆን ያዘጋጁትን የጸሎት ሃሳብ ይፋ አድርገዋል። ቅዱስነታቸው በጸሎት ሃሳባቸው ጦርነት በሚካሄድባቸው አገራት ውስጥ የሚኖሩ ክርስቲያኖች የሰላም መሣሪያዎች እንዲሆኑ በጸሎት መደገፍ አለብን ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በጸሎት ጥሪ አውታረ-መረብ በኩል የጸሎት ሃሳባቸውን ለካቶሊካዊ ምዕመናን ይፋ ያደረጉት በቱርክ እና ሊባኖስ የሚያደርጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት ለመጀመር በሚዘጋጁበት ወቅት እንደ ነበር እና ዓላማውም ጦርነት በሚካሄድባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ ክርስቲያኖችን በጸሎት ለማገዝ እንደሆነ ተገልጿል።

ቅዱስነታቸው በጸሎት ሃሳብ መልዕክታቸው፥ “በተለይም በመካከለኛው ምሥራቅ በጦርነት እና በሁከት ውስጥ የሚገኙ ክርስቲያኖች የሰላም፣ የእርቅ እና የተስፋ መሣሪያዎች እንዲሆኑ በኅብረት እንጸልይ” ሲሉ አሳስበዋል።

በማከልም በጦርነት የተከበቡ ክርስቲያኖች የወንድሞቻቸውን እና የእህቶቻቸውን የእምነት አጋርነት እና ደግነት እዲሰማቸው፥ የወንድማማችነት ትስስራቸውን እንዲያጠናክሩ እና ተስፋን የሚገነቡ የእርቅ ፍሬዎች እንዲሆኑ በማለት ጸሎት አቅርበዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በመልዕክታቸው፥ ክርስቲያኖች በሙሉ ለሌሎች ክርስቲያኖች ስቃይ ግድየለሾች እንዳይሆኑ ጥሪ አቅርበው ይልቁንም አንድነትን የሚያጠናክሩ እንዲሆኑ አሳስበዋል።

በጥፋት ውስጥ የማይናወጥ ጠንካራ እምነት

ዓለም አቀፍ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ወርሃዊ የጸሎት ጥሪ አውታረ-መረብ ከቫቲካን ሚዲያ ጋር በመተባበር ያዘጋጀውን የጸሎት ሃሳብ፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በቱርክ እና ሊባኖስ ከሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ጋር ማዛመዱ ታውቋል።

በመካከለኛው ምሥራቅ አለመረጋጋት ቢኖርም የክርስቲያን ማኅበረሰቦች እምነታቸውን በመጠበቅ፣ ድሆችን በማገልገል እና ከሌሎች አብያተ ክርስቲያናት እና ልዩ ልዩ እምነቶች ጋር በመተባበር በጋራ የሚኖሩበትን ሁኔታ ማመቻቸትን ቀጥለዋል።

በመከራ ውስጥ ለምትገኝ ቤተ ክርስቲያን ድጋፍ የሚያደርግ ጳጳሳዊ ፋውንዴሽን በ 2025 ዓ. ም. (እ.አ.አ) ይፋ ባደረገው ሪፖርቱ፥ “በመካከለኛው ምሥራቅ አገራት ውስጥ የሚፈጠሩ ግጭቶች እና በዚያ ያሉ ማኅበራዊ እና ኤኮኖሚያዊ ሁኔታዎች በቁጥር ዝቅተኛ የሆኑትን በተለይም ክርስቲያኖችን ለከፍተኛ መከራ የሚያጋልጡ ናቸው” ሲል አስታውቋል።

ጦርነት ባሉባቸው አገራት ውስጥ የሚገኙ የክርስቲያን ማኅበረሰቦች በማይናወጥ እምነታቸው ከጦርነቶች በኋላ ወደ ሕይወት ተመልሰው ለሌሎች በጎን በማድረግ እና መንፈሳዊ ዕርዳታ እያቀረቡ እንደሚገኙ ታውቋል።

ቅዱስነታቸው በወርሃዊ የጸሎት ሃሳባቸው፥ “እነዚህ በሙሉ የመንፈስ ቅዱስን መኖር የሚገልጹ ምልክቶች እና በጨለማ ጊዜያት የተስፋ ምንጮች ናቸው” ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በጦርነት ቀጣናዎች ውስጥ የሚኖሩ ክርስቲያኖችን በማስታወስ የሚከተለውን ጸሎት አቅርበዋል።

“በልጅህ ደም ዓለምን ከራስህ ጋር ያስታርቅህ የሰላም አምላክ ሆይ! ዛሬ በጦርነት እና በዓመፅ ውስጥ ስለሚኖሩ ክርስቲያኖች እንጸልያለን።

እነዚህ ክርስቲያኖች በሥቃይ ውስጥ ቢኖሩም የአንተን ደግነት እና የወንድሞቻቸውን እና የእህቶቻቸውን ጸሎት በእምነት ከማዳመጥ ወደ ኋላ አላሉም። ከአንተ ብቻ ከሚገኝ የወንድማማችነት ትስስር ተጠናክረው የእርቅ ፍሬ፣ በትንሽም በትልቅ የተስፋ ገንቢዎች፣ በይቅርታ ወደፊት የመራመድ ችሎታ ያላቸው፣ መለያየትን በማጥበብ እና ምሕረትን በመፈለግ ፍትህን የማምጣት ችሎታ አላቸው።

‘ሰላምን የሚያወርዱ የተባረኩ ናቸው’ ያልካቸው ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ! ስምምነት የማይቻል በሚመስልበት ወቅት እንኳ የሰላም መሣሪያዎች አድርገን።

በጨለማ ጊዜያት የተስፋ ምንጭ የሆንክ መንፈስ ቅዱስ ሆይ! የሚሰቃዩትን ሰዎች እምነት ጠብቅ፤ ተስፋቸውን አጠንክር፤ በግድየለሽነት ውስጥ እንዳንወድቅ ጠብቀን፤ እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ የአንድነት ፈጣሪዎች አድርገን።    አሜን!”

10 Dec 2025, 15:24