ፈልግ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ “ሊባኖስ በሃይማኖቶች መካከል ለሚደረግ ውይይት ምስክር ናት” ሲሉ ገለጹ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በሊባኖስ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ወቅት በልዩ ልዩ የሃይማኖት መሪዎች መካከል በተካሄደው ስብሰባ ላይ ተገኝተው ንግግር አድርገዋል። ቅዱስነታቸው ለሃይማኖት መሪዎች ባደረጉት ንግግር፥ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን የእያንዳንዱን ሰው ክብር ለማረጋገጥ የሚያግዝ በመለኮታዊ ፍቅር የታገዘ ውይይትን ለማበረታታት የምትፈልግ መሆኗን አረጋግጠዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በሊባኖስ ባደረጉት የሁለተኛ ቀን ሐዋርያዊ ጉብኝት ማለትም ሰኞ ኅዳር 22/2018 ዓ. ም. በቤይሩት በሚገኘው የሰማዕታት አደባባይ ከክርስቲያን እና ከልዩ ልዩ የሃይማኖት መሪዎች ጋር ተገናኝተዋል።  

ቅዱስነታቸው ለመሪዎቹ ባደረጉት ንግግር፥ ሊባኖስ በሰማይ የማያቋርጥ ዕይታ ሥር የሚበቅል የዝግባ ዛፍ ዓርማን በሚመለከቱ የብሉይ ኪዳን ነቢያት የተከበረች ምድር ናት” በማለት ጠርተውታል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤኔዲክቶስ 16ኛ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2012 ዓ. ም. “Ecclesia in Medio Oriente” “በመካከለኛው ምሥራቅ የምትገኝ ቤተ ክርስቲያን” በማለት በቤሩት ይፋ ያደረጉትን ሐዋርያዊ ምክር በማስታወስ፥ ይህም ቤተ ክርስቲያኗ ከሌሎች ሃይማኖቶች ተከታዮች ጋር ለመወያየት ያላትን ፍላጎት የሚገልጽ መሆኑን አስረድተዋል።

በሀገሪቱ ውስጥ ከመስጊዶች ጋር የተገነቡ ረጃጅም ግንቦች ከቤተ ክርስቲያን የደወል ማማዎች ጎን ለጎን መቆማቸው በዚህች የተወደደች ምድር የሊባኖስ ሕዝብ ለአንድ አምላክ ያለውን ዘላቂ እምነት እና ታማኝነት ይመሰክራል” ብለው፥ “እያንዳንዱ የደወል እና የ ‘አድሃን’ ድምፅ አንድ ከፍ ያለ የጸሎት ጥሪን የሚያስተጋባ፣ የሰማይ እና የምድርን መሐሪ ፈጣሪ ለማክበር ብቻ ሳይሆን ለመለኮታዊ የሰላም ስጦታ ከልብ የመነጨ ጸሎት ለማቅረብ ጭምር” ነው ብለዋል።

ባለፉት በርካታ ዓመታት የመካከለኛው ምሥራቅ አስቸጋሪ ጉዞ ማድረጉን እና ውድ የሆነውን የሰላም ስጦታ ሳያቋርጥ የሚፈልግ መሆኑን ዓለም እንደሚያውቅ ጠቁመው፥ “በእነዚህ የክልሉ ውስብስብ ግጭቶች መካከል የሊባኖስ ሕዝብ ያለመተማመን እና የጭፍን ጥላቻ ዕድል እንደሌለው ገልጸው፥ ይህም “ሰላም የሚቻል መሆኑን የሚያሳይ ነው” ሲሉ አስረድተዋል።

በእነዚህ የሰላም ጥረቶች ውስጥ አንድ በሚያደርገን ነገር ላይ ስናተኩር ተስፋ እና ብርታት ሊገኝ የሚችለው በጋራ ሰብዓዊነታችን፣ በፍቅር እና በምሕረት አምላክ ባለን እምነት ላይ ነው” ብለው፥ ክርስቲያኖች፣ ሙስሊሞች፣ ድሩዝ እና ሥፍር ቁጥር የሌላቸው ሌሎች ሕዝቦች አብረው በመኖር፣ በመከባበር እና በመወያየት የተዋሃደች አገር ለመገንባት የሚፈልጉ መሆናቸውን አስረድተዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ የቤተ ክርስቲያንን ሚና በማስመልከት እንደተናገሩት፥ ሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ መላው ካቶሊካዊ ምዕመናን ለሁሉም እምነት ተከታዮች በፍቅር ላይ የተመሠረተ አክብሮት እንዲያሳዩ ጥሪ ማቅረቡን አስታውሰዋል።

“በመለኮታዊ ፍቅር የታገዘ የእርስ በርስ ውይይት በመልካም ፈቃድ ላይ የተመሠረቱ ሰዎችን በሙሉ በማስተባበር፣ ጭፍን ጥላቻን፣ መድልዎን እና ስደትን በማስወገድ የእያንዳንዱን ሰው እኩል ክብር ማረጋገጥ እንዳለበት አሳስበዋል።

ቅዱስነታቸው አክለውም፥ የልዩ ልዩ ሃይማኖት ተከታዮች በመካከላቸው የሚያደርጓቸው ውይይቶች ከምንም በላይ እግዚአብሔርን በማስቀደም የሚያድግ እና እርሱን በማክበር በትህትና አብረው እንዲፈልጉት የሚጋብዙ መሆናቸውን አስታውሰዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በሊባኖስን ውስጥ የበቀሉ ሥፍር ቁጥር የሌላቸው የዝግባ እና የወይራ ዛፎችን በማስታወስ “የማያቋርጡ የእርቅ እና የሰላም ምልክቶች ናቸው” ብለዋል።

“የዛፎቹ ረጅም ዕድሜ እና እጅግ አስቸጋሪ በሆኑ አካባቢዎችም ጭምር የመብቀል አስደናቂ ችሎታቸው ጽናትን እና ተስፋን የሚያመለክት፣ በሰላም አብሮ የመኖርን ፍላጎትን ለማሳደግ የሚያግዙ ጽኑ ቁርጠኝነቶችን ያንፀባርቃል” ብለው፥ “ከዚህ ዛፍ የሚፈሰው ዘይት በአካላዊ እና መንፈሳዊ ቁስሎች ለሚሰቃዩት በሙሉ የእግዚአብሔርን ወሰን የሌለው ርኅራኄ ይገልጻል” ብለዋል

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በንግግራቸው ማጠቃለያ፥ በዓለም ዙሪያ ያሉ የሊባኖስ ስደተኞች እና እምነታቸው ሰላምን ለመገንባት፣ አለመቻቻልን ለመጋፈጥ፣ ዓመፅን ለማሸነፍ እና ለሁሉም ሰው ፍትሃዊ መንገድን ለማሳየት የቀረበ ጥሪ እንደሆነ አስረድተዋል።

“የሰላም ንግሥት እና የኢየሱስ ክርስቶስ እናት ቅድስት ድንግል ማርያም እናታዊ ፍቅር ሁላችንንም ይምራን” ብለው፥ የትውልድ አካባቢያቸው በሆነው መካከለኛው ምሥራቅ እና በመላው ዓለም የእርቅ እና በሰላም አብሮ የመኖር ስጦታን እንደ ሊባኖስ ጅረቶች እንዲፈስ፣ ተስፋ እና አንድነት ለሁሉ ሰው እንዲኖር በመጸለይ ንግግራቸውን ደምድመዋል።

 

02 Dec 2025, 13:56