ፈልግ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ “በሊባኖስ ፍትህን ለማምጣት ልብን ማዘጋጀት አለብን” ሲሉ አሳሰቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በሊባኖስ መዲና ቤሩት የውሃ ዳርቻ የተዘጋጀውን የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ሥነ-ሥርዓት መርተዋል። ቅዱስነታቸው በመስዋዕተ ቅዳሴው ሥነ-ሥርዓት ላይ ባሰሙት ቃለ ምዕዳን፥ “ሊባኖሳውያን ሰላም እና ፍትህ የሰፈነባት አዲሷን ሊባኖስ ማየት ከፈለጉ ልባቸውን ማዘጋጀት ያስፈልጋል” ሲሉ አሳስበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በሊባኖስ ባደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት የመጨረሻ ቀን፥ ጉብኝታቸውን ለረጅም ጊዜ ሲጠብቁ ከነበሩ በሺዎች ለሚቆጠሩ የሊባኖስ ምእመናን የተዘጋጀውን የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት መርተዋል።

በቅዳሴው ሥነ-ሥርዓት መጀመሪያ ላይ የግሪክ መልቃይት ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የአንጾኪያ ፓትርያርክ ብጹዕ ወቅዱስ ዩሱፍ አብሲ አብዛኛዎቹ የሊባኖስ ካቶሊካዊ ምዕመናን የምስራቅ አብያተ ክርስቲያናት አባላት መሆናቸውን አስታውሰዋል።

ብጹዕ ወቅዱስ ዩሱፍ አብሲ በሥነ-ሥርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ የምሥራቅ ሥርዓተ አምልኮን ለሚከተሉ ካቶሊካዊ ምዕመናን ላደረጉት እንክብካቤ እና ወደ ሊባኖስ ላመጡት የደስታ እና የሰላም መልዕክት ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በቃለ ምዕዳናቸው፥ በሊባኖስ ለተደረገላቸው ደማቅ አቀባበል ምስጋናቸውን ገልጸው፥ አገሪቱን እንዲጎበኟት የፈቀደላቸውን እግዚአብሔር አመስግነዋል።

ብዙ ሰዎች በዕለት ተዕለት ሕይወታቸው ውስጥ የሚያጋጥሟቸው አስቸጋሪ ሁኔታዎች ቢኖሩም ክርስቲያኖች ዘወትር ለእግዚአብሔር ምስጋና እና ውዳሴ የማቅረብ ፍላጎትን ማዳበር እንዳለባቸው አሳስበዋል።

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለተዘመረለት የሊባኖስ ውበት አድናቆታቸውን የገለጹት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ ነገር ግን ይህ ውበት በድህነት እና በስቃይ ምክንያት በአገሪቱ ታሪክ ላይ የቁስል ምልክቶችን በማስቀመጡ የተሰማቸውን ሐዘን ገልጸዋል።

“አገራችሁ ውበት በሚያሰቃዩ በርካታ ችግሮች፣ በደካማ እና ያልተረጋጋ የፖለቲካ ሁኔታ፣ በከባድ የኢኮኖሚ ቀውስ እና ፍርሃትን እንደገና በቀሰቀሱ ዓመጾች እና ግጭቶች ተሸፍኗል” ሲሉ አክለዋል።

“በእነዚህ ጭንቀቶች መካከል ወደ ፊት መልካም ጊዜ እንደሚመጣ እርግጠኞች አለመሆን እና ተስፋ መቁረጥ ለእግዚአብሔር የምናቀርበውን ምስጋና እንዲቀንስ ሊያደርግ ይችላል” ብለዋል።

“የእግዚአብሔር ቃል፥ በጨለማ ውስጥ ትናንሽ ብርሃኖችን ማግኘት እንዳለብን ይጋብዘናል” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ ለምስጋና ራሳችንን እንድንከፍት እና ለዚህች ምድር ጥቅም ሲባል የጋራ ቁርጠኝነት እንድናነሳሳ ይጋብዘናል” ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በመቀጠልም፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ለአብ ምስጋናውን የሚያቀርበው ለልዩ ሥራዎቹ ሳይሆን ራሱን ለትንንሾች እና ለትሑታን በመግለጡ ነው” ሲሉ አስረድተዋል።

በትንቢተ ኢሳይያስ እንደተገለጸው፥ የእግዚአብሔር መንግሥት ከግንድ ላይ እንደሚበቅል ትንሽ ቅርንጫፍ እንደሆነ አስታውሰው፥ “ይህም በሞት መካከል ዳግም መወለድን የሚያረጋግጥ ትንሽ የተስፋ ምልክት ነው” ብለዋል።

“ይህ ለእኛም አመላካች ነው” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ በመሆኑም በመከራ ጊዜ እንኳ የሚወጣውን እና የሚበቅለውን ቅርንጫፍ ትንሽነት የመለየት ችሎታ ያላቸው ዓይኖች እንዲኖሩን ያደርጋል” ብለዋል።

“አሁንም ቢሆን በሊባኖስ ምሽት ትናንሽ መብራቶች መብራት ጀምረዋል” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ በተለይም በሊባኖስ ሕዝብ መካከል የሰረጸ ቅን እና እውነተኛ እምነት በቤተሰቦች እና በክርስቲያን ትምህርት ቤቶች ውስጥ ይታያል” ብለዋል።

የሰዎችን ቁሳዊ እና መንፈሳዊ ፍላጎቶች ለማሟላት የሚጥሩ ቁምስናዎች እና መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች እንዲሁም የበጎ አድራጎት ሥራዎችን የሚያከናውኑ እና ወንጌልን ለሊባኖስ ማኅበረሰብ የሚመሰክሩ በርካታ ካህናት፣ ገዳማውያን እና ገዳማውያት መኖራቸውን ጠቁመዋል።

“ምስጋና ወደ ግል የሚያተኩር መጽናኛ ሆኖ ሊቀጥል እንደማይችል ገልጸው፥ ይልቁንም እንድንለወጥ እና በተስፋ እና በበጎ አድራጎት ቃል ኪዳን እንድንኖር ሊያደርገን ይገባል” ብለዋል።

“ሁላችንም ተስፋን እንዳንቆርጥ፣ ለዓመፅ አመክንዮ እና ለገንዘብ እንዳንሸነፍ፣ ተስፋፋው ክፉ ነገር ራሳችንን አስልፈን እንዳንሰጥ ተጠርተናል” ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ የሊባኖስ ሕዝብ አገሪቱን ወደ ቀድሞ ክብሯ እንድትመልስ የበኩሉን ጥረት እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።

“ልብን ለዚህ ማዘጋጀት ብቸኛው መንገድ ነው” ብለው፥ “የዘር እና የፖለቲካ ክፍፍሎችን በማስወገድ፣ የሃይማኖት ተቋማት እርስ በርስ የሚገንኙበትን መንገድ በማመቻቸት ሰላም እና ፍትህ የሚነግሥባት እና ሁሉም እንደ ወንድም እና እህት የሚታወቁባት የተባበረች ሊባኖስን በልባችን ውስጥ እንደገና እንገባ” ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በቃለ ምዕዳናቸው ማጠቃለያ፥ የሊባኖስ ሕዝብ እግዚአብሔር በእጃቸው ያስቀመጠውን ሕልም እንዲያሳድግ፣ ስቃዩን እንዲሸከምና በተስፋ እንዲጸና፣ “ሊባኖስም የፍትህ እና የወንድማማችነት አገር እንድትሆን፣ ለመላው ሌዋውያን የሰላም ትንቢታዊ ምልክት ትሆን ዘንድ!” በማለት ጸሎታቸውን አቅርበዋል።

 

 

03 Dec 2025, 16:40