ፈልግ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ከዜማ ሊቅ ሪካርዶ ሙቲ ጋር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ከዜማ ሊቅ ሪካርዶ ሙቲ ጋር  (@Vatican Media)

ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ፥ የእግዚአብሔር ውበት በዜማ እንዲገለጽ ያደረገ እውቅ ሰው ሪካርዶ ሙቲን አመሰገኑ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ መጭውን የብርሃነ ልደቱን በዓል ምክንያት በማድረግ በቅዱስ ጳውሎስ 6ኛ አዳራሽ በተዘጋጀው ኮንሰርት ላይ ተገኝተዋል። እንደ ጎርጎሮሳውያኑ የ2025 ዓ. ም. “የራትዚንገር ሽልማት” አሸናፊ እና የኮንሰርቱ መሪ የሆነውን የዜማ ሊቅ ሪካርዶ ሙቲን አመስግነዋል። ኮንሰርቱን በኅብረት ያዘጋጁት በቅድስት መንበር የባሕል እና የትምህርት ጉዳዮች ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት እና “ግራቪሲሙም ኤጁኬሽኒስ” የተሰኘ ጳጳሳዊ ፋውንዴሽን መሆናቸው ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በዜማ ሊቅ በሪካርዶ ሙቲ መሪነት በቅዱስ ጳውሎስ 6ኛ አዳራሽ ውስጥ ዓርብ ታኅሳስ 3/2018 ዓ. ም. ምሽት በቀረበው ኮንሰርት ላይ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ጋር ከፍተኛ የቫቲካን ባለስልጣናት የታደሙት ሲሆን፥ ኮንሰርቱን ያቀረቡት “ሉዊጂ ኬሩቢኒ” የተሰኘ የወጣቶች ኦርኬስትራ እና “ጉይዶ ኪጂ ሳራቺኒ” የተሰኘ የሲዬና ካቴድራል መዘምራን መሆናቸው ታውቋል።

ኮንሰርቱ የተዘጋጀው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ የቅዱስ ጴጥሮስ ሐዋርያዊ መንበር ከተቀበሉ በኋላ የሚያከብሩትን የመጀመሪያ የብርሃነ ልደት በዓል እና ለታዋቂው ዓለም አቀፍ የዜማ መሪ ሪካርዶ ሙቲ የተሰጠውን የ2025ቱን የራትዚንገር ሽልማት ምክንያት በማድረግ እንደሆነ ታውቋል።

በሙዚቃ፣ በእምነት እና በሰው ልጅ መካከል ያለው ግንኙነት

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በኮንሰርቱ መደምደሚያ ላይ፥ በመንፈሳዊ ሙዚቃ፣ በእምነት እና በሰው ልጅ መካከል ስላለው ግንኙነት አፅንዖት በመስጠት ለታዳሚዎች ባደረጉት ንግግር፥ “ቅዱስ አጎስጢኖስ መንፈሳዊ ሙዚቃ “ልብን ወደ እግዚአብሔር የመምራት ጥበብ” ማለቱን አስታውሰው፥“ሙዚቃ የሰውን ልጅ ክብር ለማወቅ እና የአንድን ሰው ጥሪ ለማረጋገጥ የሚያግዝ መንገድ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

ሪካርዶ ሙቲ ሙዚቃ ከቤተ ክርስቲያን ጋር ለሚያደርገው ውይይት አስፈላጊነት የሰጠውን የዕድሜ ልክ ቁርጠኝነት ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፥ ሪካርዶ ሙቲ ለታላቁ ቅዱስ ግሪጎሪ ሞገስን ከሚሰጡት ከቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤኔዲክቶስ 16ኛ ጋር ያለውን የግል ግንኙነት አስታውሰዋል።

ሟቹን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በኔዲክቶስ 16ኛን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፥ ሪካርዶ ሙቲ እና ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በኔዲክቶስ 16ኛን በጀርመን ከሳልዝበርግ እና ሙኒክ እስከ ሮም ድረስ የነበራቸውን ግንኙነቶች ሙዚቃ ከሥነ ምግባራዊ ኃላፊነት ጋር የጋራ ግንዛቤን እንደፈጠረ ተናግረዋል።

የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በኔዲክቶስ 16ኛ ሙዚቃን ዘወትር የጥበብ ልብ አድርገው የሚቆጥሩት በመሆኑ እንዴት መጠበቅ እንደሚገባ ለሚያውቅ ሰው የ “ራትዚንገር ሽልማት” መሰጠት ተገቢ እንደ ሆነ እና “ሙዚቃ የእግዚአብሔርን ታላቅነት በዜማ የማሰማት ዕድል” እንደሆነ አስረድተው በማከልም፥  የዛሬው ሽልማት በሰዎች መካከል ውይይት እንዲቀጥል በማድረግ ወደ ጋራ ጥቅም እና መግባባት ያተኮረ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

በተጨማሪም በዓለም ዙሪያ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ልጆች ከመደበኛ ትምህርት መገለላቸውን ጠቅሰው፥የወጣት ተዋንያን መኖር እና ሪካርዶ ሙቲ ለትምህርት እና ለስልጠና ለሰጠው የረጅም ጊዜ ቁርጠኝነት አፅንዖት ሰጥተዋል።

በዚህም ምክንያት በቅርቡ በተከበረው የትምህርት ኢዮቤልዩ በዓል ወቅት የተዘረጋውን የእኩልነት እና የትምህርት ተደራሽነትን ደግፈው፥ ይህም ዓለም አቀፍ የትምህርት ተደራሽነትን ለማረጋገጥ የሚደረጉ ጥረቶችን ለማስተባበር ያለመ እንደሆነ አስረድተዋል።

ር. ሊ. ጳ. በኔዲክቶስ 16ኛ፣ ሪካርዶ ሙቲ እና ሞዛርት

የዜማ ሊቁ ሪካርዶ ሙቲ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ንግግር ቀደም ብሎ ባደረገው አጭር የምስጋና ቃል፥ ከመጀመሪያው ቅጽበት ጀምሮ ለቅዱስነታቸው ያለውን የግል ፍቅር ከገለጸላቸው በኋላ በቺካጎ ሲምፎኒ ኦርኬስትራ የሙዚቃ ዳይሬክተር ሆኖ ያሳለፋቸውን ዓመታት ጨምሮ ጥበባዊ ጉዞውን በማስመልከት አጭር ንግግር አድርጓል። በማከልም ከሁሉም በላይ ከታላቅ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት እና የነገረ መለኮት ሊቅ ከነበሩት ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በኔዲክቶስ 16ኛ ጋር የነበረውን ረጅም ግንኙነት አስታውሷል።

እያንዳንዱ ሕጻን በትምህርትና በሥነ ጥበብ ይሳተፍ ዘንድ!

በዝግጅቱ መጨረሻ ላይ ብጹዕ ካርዲናል ቶሌንቲኖ ዴ ማንዶካ በቅድስት መንበር የባሕል እና የትምህርት ጉዳዮች ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ ለዜማ ሊቁ ሪካርዶ ሙቲ እና ወጣት ሙዚቀኞች ምስጋናቸውን በማቅረብ ለዝግጅቱ ትምህርታዊ እና መንፈሳዊ ገጽታ አፅንዖት ሰጥተዋል።

ብጹዕ ካርዲናል ቶሌንቲኖ ዴ ማንዶካ በንግግራቸው፥ “ወጣት ሙዚቀኞች በእጆቻቸው እና በድምፃቸው ያቀረቡትን ለጸሎት እና ለመንፈሳዊ መነሳሳት የሚሆን መስዋዕተ ቅዳሴን አዳምጠናል” ብለው፥ የወጣት ተዋናዮች ሚናን ሲገልጹ፥ “በብቃት፣ በዲሲፕሊን እና በቁርጠኝነት ሲሠሩ መመልከት የአንደበተ ርቱዕነት ምልክት ነው” ብለዋል።

"ሙዚቃ በትምህርት እና በስልጠና ለወጣቶች የሚሰጠውን አስደናቂ እውነታ ስናይ የዓለምን አስደናቂ እውነታ ችላ ማለት አይቻልም” ስሉ ተናግረው፥ በዓለማችን ውስጥ 61 ሚሊዮን የሚሆኑ ሕፃናት ትምህርት ቤት መሄድ እንደማይችሉ እና 161 ሚሊዮን የሚሆኑት ደግሞ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት የማግኘት መብት እንደሌላቸው በመግለጽ “ይህ ሊድን የሚገባ ክፍት ቁስል ነው” ብለዋል።

ውበት የዓለምን ጨለማ የሚያጠፋ ሳይሆን ነገር ግን የሚያበራል እና ለመጋፈጥ ድፍረትን የሚሰጠን ነው” ብለው፥ የዛሬው ኮንሰርት ከማኅበረሰብ የተገለለ እያንዳንዱ ሕጻን እንዲማር እና እርምጃን እንድንወስድ ጥሪን የሚያቀርብ ነው” ብለዋል።

የ “ራትዚንገር ሽልማት” መንፈሳዊ እሴቶችን ያበረታታል

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ሽልማቱን ለዜማ ሊቁ ሪካርዶ ሙቲ እንዲሰጡ ከመጋበዛቸው በፊት፣ የ “ራትዚንገር ፋውንዴሽን” ፕሬዝደንት አባ ፌዴሪኮ ሎምባርዲ ሽልማቱን በማቅረብ የሪካርዶ ሙቲ ሥራ የፋውንዴሽኑ ተልዕኮ ማዕከል የሆኑትን እሴቶች የሚያሳይ መሆኑን በመጥቀስ፥ “የሪካርዶ ሙቲ መንፈሳዊ ሙዚቃ ትርጓሜ ጥልቀት በሙዚቃ፣ በቤተ ክርስቲያን እና በእምነት መካከል ባለው ግንኙነት ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩን ቀጥሏል” ብለዋል።

አባ ሎምባርዲ በማከልም፥ በሪካርዶ ሙቲ እና በዮሴፍ ራትዚንገር መካከል ያለውን ግንኙነት በማስታወስ፥ በሁለቱ መካከል ያለው የጋራ መከባበር እና መስማማት የነገር መለኮት ሊቅ እና የሙዚቃ ወዳጅ በሆኑት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ስም የሚሰጠውን ሽልማት ሙሉ በሙሉ ተገቢ ያደርገዋል” ብለዋል።

 

13 Dec 2025, 15:53