ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ፥ “የኢየሱስ ልደት ተስፋ ለሚያስፈልገው ዓለማችን የብርሃን ስጦታ ነው” ሲሉ ገለጹ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የላቲን የአምልኮ ሥርዓት በሚከተሉ ካቶሊካዊ ምዕመናን ዘንድ የብርሃነ ልደቱ በዓል እየተቃረበ ባለበት በዚህ ወቅት ሮም ውስጥ በሚገኘው የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጳጳሳዊ ባዚሊካ ውስጥ የተለመደውን በዓል አንድ ሺህ ከሚሆኑ ምዕመናን ጋር አክብረዋል። ቅዱስነታቸው የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት ምሳሌያዊ ትዕይንት ወደሚፈጸምበት ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጳጳሳው ባዚሊካ ከሚሄዱ ምዕመናን ጋር በቫቲካን ተገናኝተዋል።
የምዕመናን ቡድኑ የቅዱስ ጴጥሮስን መካነ መቃብር ለመጎብኘት ከመላው ዓለም የመጣ መሆኑን የገለጹት ቅዱስነታቸው፥ ይህም ቅዱስ ሥፍራን ለመጎብኘት ከዓለም ዙሪያ የሚመጣውን ትውልድ የሚያሳይ መሆኑን አስረድተዋል። የምዕመናን ቡድኑ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ጋር ከተገናኙ በኋላ “የምዕራቡ ቤተልሔም” በመባልም በሚታወቅ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጳጳሳዊ ባዚሊካ ውስጥ የቀረበውን የመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓት ተካፍሏል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ለምዕመናን ቡድኑ ባደረጉት ንግግር፥ የተወለደው ሕጻን ኢየሱስ ክርስቶስ የተቀመጠበት ግርግም ጥንታዊ ቅርስ መሆኑን ገልጸዋል፥ ቅዱስ ፍራንችስኮስ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1223 ዓ. ም. ወደ ቅድስት ሀገር ንግደት በማድረግ የመጀመሪያውን የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት ምሳሌያዊ ትዕይንትን ለማዘጋጀት መነሳሳቱን በመግለጽ፥ “ይህም የኢየሱስ ክርስቶስን ልደት ለማስታወስ የተዘጋጀ የመጀመሪያ ትዕይንት እንደሆነ የሚያሳይ ነው” ብለዋል። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ማለትም ከ800 ዓመታት በላይ የዓለም ምዕመናን የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት ምሳሌያዊ ትዕይንት ማዘጋጀት ባሕል ማድረጋቸው ይታወቃል።
ዛሬ ዓለማችን የሚፈልገው የተስፋ መልዕክት
የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በኔዲክቶስ 16ኛ እና ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በብርሃነ ልደቱ ትዕይንት በሰጡት አስተያየት ላይ ያሰላሰሉት ቅዱስነታቸው፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በኔዲክቶስ 16ኛ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2009 ዓ. ም. የልደት በዓልን በማስመልከት ባስተላለፉት መልዕክት፥ እግዚአብሔር የጦር መሣሪያ ወይም ኃይል ሳይጠቀም ትእቢትን፣ ዓመፅን እና የሰውን ልጅ የስግብግብነት ፍላጎትን ለማሸነፍ እንደመጣ መናገራቸውን ገልጸዋል።
ከአሥር ዓመታት በኋላ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የገና በዓል ትዕይንትን ስናስተነትን፥ መንፈሳዊ ጉዞን እንድንጀምር የሚጋብዘን እና ከእያንዳንዱ ሰው ጋር ለመገናኘት ትሕትናን በመልበስ ሰው በመሆን በመጣው በኢየሱስ ክርስቶስ መማረካችንን ማሰብ ያስፈልጋል” ብለዋል።
“ይህ ትክክል ነው” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ ምክንያቱም ቅድስት ቤተሰብ በቤተልሔም ዋሻ ውስጥ ራሱን የድህነት ማስወገጃ አድርጎ ማቅረቡን አስረድተው፥ “የክርስቶስን ፈለግ በመከተል አዲስ ሕይወት እንደገና መጓዝ የምንጀምረው ከዚህ ነው” ብለዋል።
በኢየሱስ ክርስቶስ ልደት ምሳሌያዊ ትዕይንት የተሳተፈው የምዕመናን ቡድን በሮም ጎዳናዎች በኩል ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጳጳሳዊ ባዚሊካ ሲሄድ የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት የመሆን አስደሳች ምልክት እንደሆነ ተገልጿል። ቅዱስ አባታችን “ይህ ተልዕኮ ዛሬ እና ዘወትር በዕለት ተዕለት ሕይወታችሁ የተስፋ ነጋዲያን በማድረግ የመጽናናት እና የብርታት መልዕክተኞች ያደርጋችኋል” ብለው፥ ተልዕኳቸው ወጣቶች ሆኑ አዛውንት፣ ጤናሞች ሆነ ሕሙማን፣ ብቸኞች እና ስቃይተኞች፥ ለሁሉም ሰው አንድ ነው” ሲሉ አስረድተዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በንግግራቸው መዝጊያ ላይ፥ የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት ምሳሌያዊ ትዕይንት፥ እኛ ፈጽሞ ብቻችን የማንሆንበት እና አስደናቂ የመዳን ሥራ አካል መሆናችንን የሚያሳይ ምልክት መሆኑን አፅንዖት ሰጥተዋል።
ከዓለም ዙሪያ በሮም ወደሚገኘው የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጳጳሳዊ ባዚሊካ የመጡት የኢየሱስ ልደት ምሳሌያዊ ትዕይንት ተሳታፊዎች የብርሃን ስጦታ መልዕክትን ወደ ዓለም በማሰራጨት ዓለማችን እጅግ ተስፋ ማድረግ መቀጥልን ዘላቂ ባህል እንዲያደርጉት አደራ ብለዋል።
