በርዕሰ ሊቀ ጳጳሳት ልብና ሐሳብ ውስጥ ያለው የፅንሰተ ማርያም አመለካከት
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን
እ.አ.አ ታሕሳስ 08/2025 የጽንሰታ ማርያምን ውበት እናሰላስላለን። በሉቃስ ወንጌል 1፡26-38 ውስጥ የተጠቀሰው የብስራተ ማርያም ታሪክ እያከበርነው የሚንገኘው የጽንሰታ ማርያም በዓል ምን እንደሆነ ለመገንዘብ እንድንችል ይረዳናል፣ በተለይም ደግሞ የመልአኩ ገብርኤል ሰላምታ ይህንን በዓል በላቀ ሁኔታ እንድንገነዘብ ያደርገናል። እርሱም በሰውኛ ቋንቋ ለመተርጎም የሚያዳግቱ ቃላትን በመጠቀም “ጸጋን የተሞላሽ” በማለት ይጀመራል። ማርያም ብሎ በስሟ ከመጥራቱ በፊት 'ጸጋን የተሞላሽ' በማለት በመጀመር በዚህም በእግዚአብሔር የተሰጣትን አዲስ ስም ይፋ አደረገ፣ ይህም ወላጆቿ ከሰጧት ስም የበለጠ ዋጋ እንዳለው አሳየ። እኛም “ጸጋ የሞላሽ ማርያም ሆይ!” እያልን ነው የምንጠራት።
ታዲያ “ጸጋ የሞላሽ” ማለት ምን ማለት ነው? ይህ ማለት ማርያም በእግዚአብሔር ሕልውና የተሞላች ናት ማለት ነው። እግዚአብሔር በምልአት በውስጧ ስላደረ ለኃጢአት ምንም ቦታ በውስጧ የለም ማለት ነው። ዓለማችን በተለያዩ ክፉ በሆኑ ነገሮች ተበክሎ ባለበት በሁኑ ወቅት ይህ በጣም ትልቅ የሆነ ነገር ነው። እያንዳንዳችን ውስጣችንን ብንመለከት የጨለሙ ጎኖቻችንን መመልከት እንችላለን። ከማርያም በስተቀር ሁሉም ታላላቅ ቅዱሳን የሚባሉ ሳይቀሩ ኃጢያተኞች ነበሩ። ሁል ጊዜ የሰው ልጆች የልምላሜ መገለጫ የሆነች፣ በኃጢአት ያልተበከለች፣ ያለአዳም ኃጢአት የተጸነሰች፣ ሙሉ በሙሉ “እንዳልከኝ ይሁንልኝ” በማለት ወደ ዓለም በመምጣት እና ለዓለም አዲስ ታሪክ የፈጠረውን እግዚአብሔርን በውስጧ በማኖር የታዘዘች እርሷ ብቻ ናት።
ሁል ጊዜ “ጸጋ የሞላሽ ማሪያም ሆይ!” በምንልበት ወቅቶች ሁሉ ለእርሷ ብቻ ሳይሆን ይህንን ታላቅ ነገር በሕይወቷ ያከናወነውን እግዚብሔርንም እናመሰግናለን። “ጸጋን የተሞላሽ ማሪያም ሆይ” በምንልበት ወቅት ይህንንም የምንለው ለየት ባለ እና ክብር በተሞላው መልኩ ነው። እርሷ ሁል ጊዜ ወጣት እንደ ሆነች አድርገን ነው የምንቆጥረው ምክንያቱ ኃጢአት አላስረጃትምና ነው። እኛን ልያስረጀን የሚችል አንድ ነገር ብቻ ነው፣ ይህም የውስጥ እርጅና ነው፣ በእድሜ ማርጀት ሳይሆን ከኃጢአት የሚመጣ እርጅና። እኛን የሚያስረጀን ኃጢአት ነው፣ ምክንያቱም ኃጢአት ልባችንን ስለሚበክል ነው። ልባችንን ይዘጋል፣ ልባችንን ያፈርሳል፣ ልባችን እንዲሰቃይ ያደርጋል። ነገር ግን በጸጋ መሞላት ከኃጢአት ነጻ ያደርጋል። ማርያም ሁሌም ወጣት ናት የምላችሁ በዚሁ ምክንያት ነው።
በየዓመቱ የስብከተ ገና ሣምንት ወቅት መንፈሳዊ ጉዞ፣ የንጽሕታ ማርያም አመታዊ ክብረ በዓል በማክበር ቤተክርስቲያኗ ትኩረቷን ወደ ማርያም እንድታዞር ይጋብዛል። የዚህ በዓል ታሪካዊ ሥር መሰረቶች በ19ኛው ክፍለ ዘመን ላይ ያተኩራል። ከ171 ዓመታት በፊት፣ እ.አ.አ ታህሳስ 8/1854 ዓ.ም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፒዮ 9ኛ ይህንን የካቶሊክ ቤተክርስቲያን እምነት በሐዋርያዊ ዶግማ ውስጥ በላቲን ቋንቋ “ኢንፊቢሊስ ዲዩስ” (የማይነገር አምላክ) የሚለውን ዶግማ አውጀው ነበር።
እንዲህ ይላል፡- “እጅግ የተባረከች ድንግል ማርያም፣ በተፀነሰችበት የመጀመሪያ ቅጽበት፣ በሰው ዘር አዳኝ በኢየሱስ ክርስቶስ ክብር ምክንያት፣ ከሁሉም የመጀመሪያ ኃጢአት እድፍ ተጠብቃለች የሚለው ትምህርት በእግዚአብሔር ተገልጧል፣ ስለዚህም በሁሉም ምዕመናን በጥብቅ እና በማይታበይ ሁኔታ ሊታመን ይገባል” ይላል።
ከሦስት ዓመታት በኋላ እ.አ.አ በ1857 ዓ.ም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በሮም በሚገኘው የስፔን ደረጃዎች አቅራቢያ በሚገኘው 'ፒያሳ ዲ ስፓኛ' የሚገኘውን የንጽሕት ማርያም መታሰቢያ ሐውልት ባርከው አስመረቁ።
ማርያም ከመጀመሪያው ኃጢአት ተጠብቃ ቆይታለች
በላቲን ቋንቋ "ኢንፋቢሊስ ዲውስ" (የማይነገር አምላክ) የተሰኘው ጳጳሳዊ መልእክት ከሆነ ከሃምሳ ዓመታት በኋላ፣ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፒየስ 12ኛ በላቲን ቋንቋ "አድ ዳይም ኢሉም ላኤቲሲሙም" ("በዚያ በጣም አስደሳች ቀን) በተሰኘው ጳጳሳዊ መልእክት ላይ በወቅቱ የነበሩት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፒዮ 9ኛ "ማርያም ከተፀነሰችበት የመጀመሪያ ቅጽበት ጀምሮ ከመጀመሪያው ኃጢአት (የአዳማም አጢያት ተብሎ ከሚታወቀው) ሙሉ በሙሉ ነፃ እንደሆነች በሐዋርያዊው አስተምህሮ ስልጣን ላይ ተንተርሰው እንደ መለኮታዊ መገለጥ አውጀዋል" ሲሉ አስታውሰዋል።
መልእክቱ "ሰዎች ድንግል ማርያም ከእያንዳንዱ የአጢያት እድፍ እንደተጠበቀች ካመኑ እና ከተናገሩ፣ የመጀመሪያውን ኃጢአት፣ በኢየሱስ ክርስቶስ የተገኘውን የሰው ልጅ መልሶ ማቋቋም፣ ወንጌልን፣ ቤተክርስቲያንን እና በመጨረሻም የመከራ ህግን ጭምር አምነው መቀበል አለባቸው" ሲል ገልጿል።
ጽንሰተ ማርያም እና የማርያም ወደ ሰማይ መፍለስ
በላቲን ቋንቋ "ሙኒፊሴንቲሲመስ ዲውስ" በአምርኛው በግርድፉ ሲተረጎም (እጅግ ቸር አምላክ) በተሰኘው እና እ.አ.አ 1950 በተጻፈው በሐዋርያዊ ሕገ ጋት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፒዮ 12ኛ "ንፁህ የእግዚአብሔር እናት፣ ዘላለማዊ ድንግል ማርያም፣ የምድራዊ ህይወቷን ከጨረሰች በኋላ፣ በሥጋ እና በነፍስ ወደ ሰማያዊ ክብር ተወስዳለች" ሲሉ ገልጸዋል።
ይህ የትንሣኤ ዶግማ - በእየአመቱ እ.አ.አ በነሐሴ 15 ቀን የሚከበረውን የፍልሰተ ማርያም አመታዊ በዓል - ከንጽንሰተ ማርያም ፅንሰ-ሀሳብ ጋር በቅርበት የተቆራኘ ነው። እ.አ.አ የ1950ቱ ሕገ ጋት "በልዩ መብት" ይላል፣ "ኃጢአትን በንጽሕና ፅንሰ-ሐሳቧ አሸንፋለች፤ ስለዚህ፣ በመቃብሩ ውስጥ ሰውነቷ ሳይበላሽ ወይም ሳይፈርስ የመቆየት ሕግ አልተገዛችም፣ እንዲሁም የሰውነቷን ቤዛ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ መጠበቅ አላስፈለጋትም" ይላል።
እ.አ.አ በ1958 ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዩሐንስ 23ኛ ወደ 'ፒያሳ ዲ ስፓኛ' ሄደው በድንግል ማርያም መታሰቢያ ሐውልት ግርጌ ሥር ነጭ ጽጌረዳዎችን አኖሩ - ይህም ተተኪዎቹ የሚቀጥሉበት ወግ ነው። እ.አ.አ በታህሳስ 8/1960 ዓ.ም በጽንሰተ ማርያም ፅንሰ-ሀሳብ በዓል ላይ፣ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ "የጨለማውን ሌሊት ጨለማ" የሚበትነውን የንጋት ኮከብ ማርያም ንጽሕት ብለው ሰየሟት።
ስለ እምቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የአለአዳም አጢያት መጸነስ እና ግርማዋን ስለማጉላት የሚገልጸው የካቶሊክ ቤተክርስቲያን አስተምህሮ ለእያንዳንዱ ጥሩ ክርስቲያን የታወቀ ነው፣ ለክቡራን ነፍሳት ደስታ እና የሚማርክ ውበት ነው። በሥርዓተ አምልኮ፣ በቤተክርስቲያን አባቶች ድምፅ፣ እሷን ለማክበር በሚጓጉ ብዙ ልቦች ናፍቆት ውስጥ ይገኛል…
የጳጳስ ጳውሎስ ስድስተኛ ቃል ኪዳን
የሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ መደምደሚያ የመጀመሪያ ዓመት ዝክር ላይ፣ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ጳውሎስ ስድስተኛ እ.አ.አ በታህሳስ 8/1966 ዓ.ም በቅዳሴ ሥነ ሥርዓት ወቅት፣ የአለ አዳም አጢያት መፀነስ “የልዩነት ምስጢር፣ የቅድስት ማርያም ፍጹምነት ምስጢር” መሆኑን አፅንዖት ሰጥተው ተናግረው ነበር።
“ማርያም፣ በመለኮታዊ ንድፍ (ምን ያህል ጥበብ እና ፍቅር ይዟል!)፣ በክርስቶስ መልካምነት - ብቸኛው የመዳናችን ምንጭ - ከማንኛውም ፍጽምና የተጠበቀች ብቸኛ የሰው ልጅ ፍጡር” ሲሉ አክለው ገልጸዋታል።
ማርያምን “በደህንነት ምስጢር ዕቅድ መሠረት በትምህርትና በአምልኮ ውስጥ ልዩ ቦታ እንድትይዝ የሚያስችሏት መስፈርቶች - ስለዚህም የክርስቶስና የቤተክርስቲያን ምዕመናን እናት ናት” ሲሉ መናገራቸውም ይታወሳ።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዩሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ እና ቤተክርስቲያኗን ለማርያም አደራ መስጠት
እ.አ.አ በ1978 ዓ.ም የቅዱስ ጴጥሮስ ተተኪ ሆነው ከተመረጡ በኋላ በርዕሰ ሊቃነ ጵጵስና ዘመናቸው መጀመሪያ ላይ፣ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዩሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ቤተክርስቲያኗን ለማርያም በልዩ መንገድ አደራ ሰጥተዋል። በዚያው ዓመት እ.አ.አ ታህሳስ 8 ቀን በመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ላይ፣ ማርያም ያለ አዳም አጢያት ስለ መፀነሷ የተናገሯቸው ቃላት ከኢየሱስ ሕይወት ጋር የተቆራኙ ናቸው።
የመለኮታዊ ሕይወት ባለቤት የሆነው ክርስቶስ - ማለትም በእያንዳንዱ ሰው ውስጥ ጸጋ - ባከናወነው የድህንነት ምስጢር አማካኝነት፣ ለእናቱ በተለየ ሁኔታ ለጋስ መሆን አለበት… ይህ ወልድ ለእናቱ ያሳየው ልግስና ወደ ሕልውናዋ የመጀመሪያ ቅጽበት ይመለሳል። ይህም ያለ አዳም አጢያት በንጽሕና መፀነስ ይባላል።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ቤኔዲክቶስ 16ኛ እና በንጽህናት መፅንስ ውስጥ ያለው የእምነት እውነቶች
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ቤኔዲክቶስ 16ኛ እ.አ.አ በታህሳስ 8/2008 ዓ.ም የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ላይ ባብራሩት የማርያም ያለአዳም አጢያት የመጸነስ ምሥጢር የእምነታችንን ሁለት መሠረታዊ እውነቶች ያስታውሰናል፡-
በመጀመሪያ፣ የመጀመሪያው ኃጢአት (ከአዳም የወረስነው አጢያት) ሲሆን፣ ከዚያም በክርስቶስ ጸጋ በእርሱ ላይ ድልን ተጎናጽፈናል- ይህ ድል በቅድስት ማርያም ውስጥ እጅግ የሚያበራ ድል ነው። ያለመታደል ሆኖ፣ ቤተክርስቲያን “የመጀመሪያ ኃጢአት” ብላ የምትጠራው ነገር መኖር፣ በዙሪያችን እና ከሁሉም በላይ በውስጣችን ብቻ ከተመለከትን በጣም ግልፅ ነው… ውድ ወገኖቼ፣ በንጽሕት ማርያም፣ ዓለምን የሚያድነውን ውበት ነጸብራቅ እናሰላስላለን፡ በክርስቶስ ፊት የሚያበራውን የእግዚአብሔር ውበት እንመለከታለን። በማርያም ውስጥ፣ ይህ ውበት ሙሉ በሙሉ ንፁህ፣ ትሑት፣ ከማንኛውም ኩራት እና ግምት የጸዳ ነው።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እና ድንግልን ማርያምን ማመስገን
እ.አ.አ ታህሳስ 8/2015 ዓ.ም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ 50ኛ ዓመት ክብረ በዓል ላይ የተከበረውን እጅግ በጣም ጥሩ የምሕረት ኢዮቤልዩን ከፍተዋል። በዚያው ቀን በፒያሳ ዲ ስፓኛ በሚገኘው ያለአዳም አጢያት የተጸነሰች የንጽሕት ማርያም አምልኮ በዓል ወቅት፣ ለማርያም የምስጋና ጸሎት እንዲህ ሲሉ አቀረቡ፡-
ንጽሕት እናቴ ሆይ፣ እናመሰግንሻለን፣
ምክንያቱም በዚህ የእርቅ ጉዞ ላይ
ብቻችንን እንድንሄድ አልፈቀድሽልንም፣ ነገር ግን አብረሽን ትጓዢያለሽ፣
ከእኛ ጋር ትሆኛለሽ እና በችግራችን ሁሉ ትደግፊናለሽ።
አሁንም ሆነ ሁልጊዜ፣ እናቴ፣ የተባረክሽ ነሽ።
የሊቀ ጳጳስ ሊዮ 14ኛ እና የማርያም መንገድ
እ.አ.አ በታህሳስ 8/2025 ዓ.ም በሮም የሰዓት አቆጣጠር ከሰዓት በኋላ ከቀኑ 4 ሰዓት ላይ፣ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የቀደሙትን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳትን ፈለግ ተከትለው በሮም በሚገኘው 'ፒያሳ ዲ ስፓኛ' በሚገኘው የቅድስት ድንግል ማርያም ሐውልት ግርጌ ሥር ለመጸለይ ወደ ሥፍራው አቅንተው ነበር።
በጥቅምት 12 ቀን ለማርያም መንፈሳዊነት ኢዮቤልዩ ባደረጉት ስብከት፣ “የማርያም መንገድ ከኢየሱስ ጀርባ ነው፣ የኢየሱስም መንገድ ወደ እያንዳንዱ ሰው ይመራል” በማለት አፅንዖት ሰጥተው መናገራቸው ይታወሳል።
ለናዝሬቷ ማርያም ያለን ፍቅር፣ ከእሷ ጋር የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ያደርገናል፤ ወደ እርሱ እንድንመለስ፣ የተነሣው ሰው አሁንም የሚጎበኘን እና የሚጠራንን የሕይወት ክስተቶች እንድናሰላስል እና እንድናገኝ ያስተምረናል።
በማርያም በላቲን ቋንቋ "ቶታ ፑልቻራ" (ሙሉ በሙሉ ውብ ነሽ) ውስጥ፣ የሰው ልጅ ዓለምን የሚያድን የውበት ነጸብራቅን ማሰላሰል ይችላል።
