ፈልግ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ቫቲካን ለተገኙ መንፈሳዊ ነጋዲያን ሰላምታ ሲያቀረቡ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ቫቲካን ለተገኙ መንፈሳዊ ነጋዲያን ሰላምታ ሲያቀረቡ   (@Vatican Media)

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ሁላችንም እግዚአብሔርን እና ፍቅሩን ፈላጊዎች ነን ማለታቸው ተነገረ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አስራ አራተኛ የካቲት ወር ታትሞ ለንባብ በቀረበው ‘ፒያሳ ሳን ፔትሮ’ መጽሔት ላይ እግዚአብሔርን ከማመን ጋር ለሚታገለው ሮኮ ምላሽ ሲሰጡ የእምነት ዋናው ጉዳይ እግዚአብሔርን ማመን ወይም አለማመን ሳይሆን እርሱን መፈለግ እንደሆነ አበክረው ገልጸዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የጣሊያን መጽሔት የሆነው 'ፒያሳ ሳን ፔትሮ' በየካቲት ወር እትሙ “መከራን የሚቋቋም እምነት” በሚል አርዕስት ለንባብ የቀረበ ሲሆን፥ ከአንባቢያን ጋር ለመወያየት በተዘጋጀው የመጽሄቱ ክፍል ላይ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በደቡባዊ ጣሊያን በምትገኘው ሬጂዮ ካላብሪያ የሚኖረው እምነት የለሹ ሮኮ በእግዚአብሔር ለማመን የሚያደርገውን ትግል አስመልክቶ ለብፁዕነታቸው ለፃፈው ደብዳቤ ምላሽ ሰጥተዋል።

ሮኮ፡ አምላክን የሚፈልግ እምነት የለሽ
ሮኮ በደብዳቤው ላይ የፀሐይ መውጣትን፣ መጥለቅን፣ በከዋክብት የተሞላውን ሰማይና ተፈጥሮን አስመልክቶ ቀደም ሲል የጻፈውን ግጥም ጠቅሶ፥ እነዚህ ሁነቶች “የስምምነትን ምስጢር” እንዲያሰላስል ማድረጉን የገለጸ ሲሆን፥ ግጥሙ የሚያበቃው “አለማመኔን አምናለሁ፣ ምንም ነገር እንደሌለ ሙሉ በሙሉ እርግጠኛ ነኝ፣ እግዚአብሔርን መናፈቄን እቀጥላለሁ፣ ታሪኬ እግዚአብሔር ነው፣ እረፍት አልባነቴ እግዚአብሔር ነው!” በማለት ይቋጫል።

ሮኮ እገዛ ለማግኘት ለርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በፃፈው ጽሁፍ ላይ የሚከተሉትን ጥያቄዎች የጠየቀ ሲሆን፥ “በአንድ ጊዜ ራስን አምላክ የለሽ አድርጎ መቁጠር እና እግዚአብሔርን መውደድ የሚቻለው እንዴት ነው? እግዚአብሔርን የመውደድ ፍላጎት እንዳለኝ ይሰማኛል፣ ነገር ግን ራሴን አምላክ የለሽ ነኝ ብዬ ነው የምቆጥረው፣ ወይም ምናልባት እኔ አንድ እንደሆንኩ አምናለሁ እናም አምላክን እየፈለግኩ ነው?” በማለት ጠይቋል።

የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ምላሽ
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ቅዱስ አውግስጢኖስ በአንድ ወቅት “አንተ በውስጤ ነበርክ፣ እኔ ግን ከራሴ ውጪ ነበርኩ፣ እናም እዚያ ፈለኩህ!” ያለውን ንግግር በመጥቀስ ለሮኮ ምላሽ የሰጡ ሲሆን፥ ብፁዕነታቸው አክለውም “እግዚአብሔርን የሚወዱ፣ በቅን ልብ የሚሹት አምላክ የለሽ ሊሆኑ እንደማይችሉ ለመንገር እነዚህ ቃላት በቂ ናቸው” ካሉ በኋላ፥ “እውነተኛው የእምነት ችግር እግዚአብሔርን ማመን ወይም አለማመን ሳይሆን እርሱን መፈለግ ነው!” ሲሉ በአጽንዖት መክረዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በመቀጠል “እግዚያብሔር አጥብቀው በሚፈልጉት ሰዎች ልብ ውስጥ እራሱን ያኖራል፥ ምናልባትም ትክክለኛው ልዩነት በአማኞች እና በማያምኑ መካከል ሳይሆን እግዚአብሔርን በሚፈልጉ እና በማይፈልጉ ሰዎች መካከል ነው” ብለዋል።

የማያምኑ የሚመስላቸውም እንኳን እንደ እውነቱ ከሆነ አምላካቸውን አጥብቀው የሚሹ ሊሆኑ እንደሚችሉ ያስረዱት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ በመጨረሻም “አየህ ሮኮ ሁላችንም ፍቅርን እንናፍቃለን፣ ሁላችንም እግዚአብሔርን ፈላጊዎች ነን፥ በዚህም ውስጥ የሕይወታችን ክብር እና ውበት አለ” በማለት ደምድመዋል።

25 Feb 2026, 14:26