ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ “በእግዚአብሔር ዘንድ ማንም ሰው የተረሳ አይደለም” ሲሉ ገለጹ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ረቡዕ ሚያዝያ 7/2018 ዓ. ም. በካሜሩን በጀመሩት የመጀመሪያ ቀን ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው የንጉል ዛምባ የሕፃናት ማሳደጊያ ቤት ልጆችን እና ሠራተኞችን ጎብኝተዋል።
ለሕጻናቱ ባደረጉት የመጀመሪያ ንግግር አብረው በመሆናቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው፥ የሕፃናት ማሳደጊያው እውነተኛ መኖሪያ ቤት እንደሆነ ተናግረዋል። ነገር ግን ከሁሉም በላይ እንደ ልጆቹ የሚቀበላቸው እና በፍቅር የሚቀርባቸው እግዚአብሔር መሆኑንም አስታውሰዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በማዕከሉ ውስጥ የቤተሰብነት ስሜት እንዳለ ገልጸው፥ ሕጻናቱ ተመሳሳይ የሕይወት ችግር ልምዶችን እንደሚጋሩ እና በማዕከሉ ውስጥ እውነተኛ ቤተሰብን እንደሚፈጥሩ በመናገር፥ በወንድማማችነት እና በእህትማማችነት መንፈስ በኢየሱስ ክርስቶስ ዙሪያ በአንድነት መሰብሰብባቸው ጥንካሬን እንደሚሰጣቸው እና የሕይወት ችግሮችን አብረው ለመጋፈጥ እንደሚያስችላቸው አክለዋል።
ወላጅን በሞት ማጣት፣ ብቸኝነት እና ጥርጣሬ ብዙ ሕጻናትን ከሚያጋጠሟቸው ተግዳሮቶች መካከል ጥቂቶቹ እንደሆነ የገለጹት ቅዱስነታቸው፥ እነዚህ ልምዶች የወደፊት ሕይወታቸውን መግለጽ እንደሌለባቸው አሳስበው፥ ከደረሰባቸው ቁስል ለበለጠ መልካም ሕይወት እንደተጠሩ፣ እግዚአብሔር ለሚሰቃዩት ቅርብ እንደሆነ እና እያንዳንዳቸውን በግል እንደሚያውቃቸው አስታውሰዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ኢየሱስ ክርስቶስ ለሕፃናት ልዩ እንክብካቤ እና ልዩ ቦታ መስጠቱን የሚገልጸው የቅዱስ ወንጌል ክፍል በማስታወስ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ዛሬም በተመሳሳይ አሳቢነት እና ፍቅር እንደሚመለከታቸው አስረድተዋል።
ማንም ሰው ፈጽሞ አልተረሳም!
ኅብረተሰቡ ያለበትን ከፍተኛ ኃላፊነት ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፥ ብዙውን ጊዜ በግዴለሽነት በሚታወቅ ዓለም ውስጥ እንደ ወላጅ አልባ ሕፃናት ማሳደጊያ ያሉ ቦታዎች ሰዎች እርስ በርስ እንዲተባበሩ የሚገደዱበት መሆናቸውን ተናግረው፥ “በእግዚአብሔር ታላቅ ቤተሰብ ውስጥ ማንም ሰው እንግዳ ወይም የተረሳ አይደለም” ብለዋል።
በማዕከሉ ውስጥ ሕጻናትን የሚንከባከቡ ሠራተኞችን፣ በጎ ፈቃደኞችን እና ገዳማዊያትን ለቁርጠኝነታቸው እና ተነሳሽነታቸው አመስግነው፥ ሥራቸው ተጨባጭ የፍቅር መግለጫ እንደሆነ እና የእግዚአብሔር ምሕረት ያሚገለጽበት መንገድ እንደሆነ በማስረዳት፥ ሥራቸው ቁሳዊ ድጋፍ ማቅረብ ብቻ ሳይሆን አብረዋቸው ሆነው መመሪያን በመስጠት እና በማረጋጋት የወደፊት ተስፋን መስጠት እንደሆነ አስረድተዋል።
ቅዱስነታቸው በንግግራቸው ማጠቃለያ ከማቴዎስን ወንጌል በመጥቀስ፥ በጣም ተጋላጭ ለሆኑ ሰዎች እንክብካቤ ማድረግ ክርስቶስን ራሱን ማገልገል እንደሆነ ጠቁመዋል፥ በሕፃናት ማሳደጊያው ውስጥ የሚሠሩት ሰዎች ጥረታቸውን በጽናት እንዲቀጥሉ አበረታተዋል።
በመጨረሻም የማዕከሉ ሕጻናትን እና ሠራተኞችን ለእመቤታችን ድንግል ማርያም እንክብካቤ አደራ ሰጥተው፥ በተለይም በችግር ጊዜ እንድትጠብቃቸው እና እንድትደግፋቸው በጸሎት ተማጽነዋል።
