ፈልግ

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የአፍሪካ ሐዋርያዊ ጉብኝት የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የአፍሪካ ሐዋርያዊ ጉብኝት  (@Vatican Media) ርዕሰ አንቀጽ

የሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ተተኪ የሰላም መልዕክተኛ ሆነው ወደ አፍሪካ መምጣት

የቅድስት መንበር መገናኛዎች አርታኢ ክፍል ዳይሬክተር አንድሬያ ቶርኔሊ፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በአልጄሪያ ምድር ካረፉ በኋላ የደረጉትን የመጀመሪያ ንግግር በማስታወስ ባዘጋጀው ርዕሠ አንቀጽ፥ “የቅዱስነታቸው ንግግር እርስ በርስ ይቅር ለበባባል እና የወደፊት ሕይወት በኅብረት ለመገንባት ቁልፍ ጥሪ ነው” ሲል ገልጿል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“የሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ተተኪ ወደ አፍሪካ መጥተዋል” ያለው ርዕሠ አንቀጹ፥ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2023 ዓ. ም. መጀመሪያ ላይ የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በኮንጎ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ እና በደቡብ ሱዳን ሐዋርያዊ ጉብኝት ካደረጉበት ከሦስት ዓመታት በኋላ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በአፍሪካ አህጉር ረጅም ጉዞ መጀመራቸውን ገልጾ፥ ሰኞ ሚያዝያ 5/2018 ዓ. ም. ወደ አልጄሪያ መጓዛቸውን እና በሚቀጥሉት ቀናት ወደ ካሜሩን፣ አንጎላ እና ኢኳቶሪያል ጊኒ እንደሚጓዙ አስታውቋል።

አሥራ አንድ ቀናትን የሚወስድ ይህ ሐዋርያዊ ጉብኝት በችግር እና በግጭት በተዳከመ አኅጉር ውስጥ ከሚኖሩ ሕዝቦች ጋር ከፍተኛ የግንኙነት መርሃ ግብር ያለው እና በተጨማሪም የደስታ እና የተስፋ ምልክት የሆነ ልዩ ሚስዮናዊ ባህሪ ያለው እንደሆነ ተገልጿል።

“ይህ ሐዋርያዊ ጉብኝት የሚደረገው በአስደናቂ የታሪክ ወቅት መሆኑን መርሳት አይቻልም” ያለው ርዕሠ አንቀጹ፥ በመካከለኛው ምስራቅ ምን እየተከናወነ እንዳለ እና በአሜሪካ እና በኢራን መካከል የተደረገው ድርድር ከሽፎ የግጭት ስጋት እየጨመረ የመጣበት እንደሆነ ተገልጿል።

ስለዚም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በአልጄሪያ ለመጀመሪያ ጊዜ የሰማዕታት መታሰቢያን (ማቃም ኢቻሂድ) በጎበኙበት ወቅት ሰላም የጉብኝታቸው ማዕከላዊ ጭብጥ ሆኖ ብቅ ማለቱ ጉልህ ነበር ተብሏል።

“በዚህ ቦታ እግዚአብሔር ለእያንዳንዱ ሕዝብ ሰላምን እንደሚፈልግ እናስታውስ” ያለው ርዕሠ አንቀጹ፥ ጦርነት ባለመኖሩ ብቻ ሳይሆን የፍትህ እና የሰብዓዊ ክብር መገለጫ የሆነው እና የወደፊት ሕይወትን በእርቅ መንፈስ ለመጋፈጥ የሚያስችለን ይህ ሰላም ሊመጣ የሚቻለው በይቅርታ ብቻ እና ለነፃነት የሚደረገው እውነተኛ ትግል በእርግጠኝነት እውን የሚሆነው በልባችን ውስጥ ሰላም ሲገኝ ብቻ ነው” ብሏል።

የይቅርታ እና የሰላም ልመና በጥልቅ እውነታ የተሞላ ነው። ሰላም የክርስቲያናዊ መልዕክት ዋና ይዘት ብቻ ሳይሆን የወደፊት ሕይወትን ለመገንባት ብቸኛው ተግባራዊ መንገድም ነው።

“ይቅርታ ማድረግ ምን ያህል ከባድ እንደሆነ አውቃለሁ” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ “ሆኖም በዓለም ዙሪያ ግጭቶች እየተበራከቱ በመጡበት በዚህ ጊዜ ከትውልድ ወደ ትውልድ ቂምን የበለጠ መጨመር አንችልም” ብለዋል።

በጋዛ እና አሁን ደግሞ በሊባኖስ ውስጥ ሲቪሎች ሲጨፈጨፉ በወጣት ትውልድ መካከል ቂም እንደሚፈጠር አንድ ሰው እንዴት መገመት ይሳነዋል? በዩክሬን እና በሌሎች በርካታ የዓለማችን ክልሎች በሚደረጉ ጦርነቶች ምክንያት በሚፈጠሩ ጥላቻዎች እና ዓመጾች ተመሳሳይ ጥያቄ እንዴት ሊነሳ አይችልም?

ብዙ መሪዎች እንደዚህ ባሉ ሁኔታዎች ውስጥ ወደፊት መጓዝ የሚቻለው የጦር መሣሪያን ዳግም በማስታጠቅ ነው” ብለው ቢያምኑም፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ከአልጀርስ ባስተላለፉት መልዕክት የሞትን አደጋን የሚያስፋፉትን መደገፍ እንደማይገባ በማሳሰብ “መልካም የወደፊት ጊዜ ሊመጣ የሚችለው ስለ ሰላም በሚያስቡ ወንዶች እና ሴቶች በኩል ነው” ብለው፥ ዓመፅ ጎልቶ ቢታይም የመጨረሻው ቃል እንደማይኖረው ሁሉ፥ ፍትህ ሁል ጊዜ በኢ-ፍትሃዊነት ላይ ድልን ይቀዳጃል” የሚለውን አስታውሰዋል።

የሰላም መልዕክተኛ የሆነው የሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ተተኪ ድምጽ፣ በመስቀል ላይ ራሱን መስዋዕት ለማድረግ የመረጠው የእግዚአብሔር ልጅ የሰላም ድምፅ፣ ቤተ ክርስቲያን ፍፁም አናሳ ከሆነችበት ከዚያች ምድር ሲነሳ የበለጠ ኃይለኛ ሆኖ የሚሰማው ድምፅ፣በአገልግሎት እና የሁሉም ደስታ እና ስቃይ በመጋራት ላይ የተመሠረተ የጥቂት ክርስቲያኖች ምስክርነት ከሁሉም በላይ አስፈላጊ መሆኑ ይታወቃል” ሲል የቅድስት መንበር መገናኛዎች አርታኢ ክፍል ዳይሬክተር አንድሬያ ቶርኔሊ ርዕሠ አንቀጹን ደምድሟል።

13 Apr 2026, 18:15