ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ፥ “ኢየሱስ ሕይወታችንን ሙሉ በሙሉ እንድናድስ ይጋብዘናል” ሲሉ ተናገሩ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በአልጄሪያ አናባ ከተማ በሚገኘው የቅዱስ አጎስጢኖስ ባዚሊካ ውስጥ ረቡዕ ሚያዝያ 7/2018 ዓ. ም. መስዋዕተ ቅዳሴን አሳርገዋል። በመስዋዕተ ቅዳሴው ሥነ-ሥርዓት ላይ ባሰሙት ቃለ-ምዕዳን፥ ታላቁ የቤተ ክርስቲያን ሊቅ ቅዱስ አጎስጢኖስ እንደተናገረው፥ “እግዚአብሔር ከችግሮቻችን እና ከፈተናዎቻችን ሊያወጣን፣ በእርሱ ጥንካሬ ሕይወታችን እንዲታደስ እና እንዲለውጥ የሚቀርብለትን ልመና ለመቀበል አይዘገይም!” በማለት ምዕመናንን አጽናንተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“ውድ የአልጄሪያ ክርስቲያኖች ሆይ! በዚህች ምድር የኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅር ትሑት እና ታማኝ ምልክቶች ሆናችሁ በእውነተኛ የእርስ በርስ ግንኙነቶች እና በየቀኑ በምታደርጉት ውይይቶች ወንጌልን በመመስከር በአካባቢያችሁ መልካም ጣዕም እና ብርሃን ትሆናላችሁ” ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ይህን የተናገሩት፥ በአናባ በሚገኘው የቅዱስ አጎስጢኖስ ባዚሊካ ውስጥ መስዋዕተ ቅዳሴ ባቀረቡበት ሥነ-ሥርዓት እና አራት የአፍሪካ አገራት ሐዋርያዊ ጉብኝት በጀመሩባት አልጄሪያ ውስጥ እንደ ነበር ታውቋል።

“በዚህ ሥፍራ ሰማዕታት ጸልየዋል፣ ቅዱስ አጎስጢኖስ መንጋውን ወዶታል” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ እውነትን በትጋት ይፈልጉ እንደ ነበር እና በጽኑ እምነት ኢየሱስ ክርስቶስን ያገለግሉ እንደ ነበር አስታውሰው፥ ምእመናንም የዚህ ወግ ወራሾች እንዲሆኑ፣ በወንድማማችነት እና በበጎ አድራጎታቸው አማካኝነት ምስክሮች እና ለዓለም የተስፋ ምልክቶች እንዲሆኑ ከላይ በተላኩ ሰዎች ነፃነት ውስጥ እንዲመላለሱ አሳስበዋል።

“ምንም እንኳን ዛሬ የምንገኝበት የዚህ ሥፍራ ስም ባለፉት ዘመናት መካከል ቢለዋወጥም ነገር ግን ቅዱሳን ከሰማዩ መኖሪያቸው ጋር ያላቸውን ግንኙነት በመጠበቅ ደጋፊዎቻችን እና ታማኝ ምስክሮች ሆነው ቆይተዋል” ሲሉ አስረድተዋል።

በታሪክ ውስጥ ኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱሳንን ወደ አዲስ ሕይወት እንዴት እንደጠራቸው ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፥ መዳንን ለሚፈልጉ ሰዎች በሙሉ ተመሳሳይ ግብዣ እንደሚቀርብላቸው ገልጸው፥ ይህ ጥሪ በአልጄሪያ የሚገኘውን የክርስቲያን ማኅበረሰብ ጨምሮ የመላው ቤተ ክርስቲያንን ተልዕኮ እንደሚያነሳሳ ተናግረው፥ ከዚህ አንፃር እምነት ምድራዊ ችግሮችን እንደሚያሸንፍ እና የእግዚአብሔር ጸጋ በረሃውን እንደሚለመልም አስረድተዋል።

ሕይወታችንን እንድናድስ ክርስቶስ ይጋብዘናል!

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ በዮሐንስ ወንጌል ምዕ. 3 ላይ ኢየሱስ ክርስቶስ፥ “ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር” ያለው ትዕዛዝ የማይቻል ቢመስልም ነገር ግን በትኩረት ካዳምጥነው ከባድ ጫና እና የውድቀት ኩነኔ ሳይሆን የነፃነት ስጦታ መሆኑን እንረዳለን ብለው፥ እንደገና መወለድ በመቻላችንም እግዚአብሔርን አመስግነዋል።

“በእግዚአብሔር ፍቅር ይህን ጥሪ እንድንቀበለው ተጠርተናል” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ ኢየሱስ ክርስቶስ የሰውን ልጅ ለማደስ የሚፈልገውን እና በእምነት በመጀመር ሕይወታችንን ሙሉ በሙሉ እንድናድስ ሲጋብዘን ይህን ለማድረግ የሚያስችለንን ጥንካሬን ጭምር ይሰጠናል” ብለዋል።

ኢየሱስ ሸክማችንን ከእኛ ጋር ለእኛ ይሸከማል

“ሕመማችን ወይም ኃጢአታችን ምንም ያህል ከባድ ቢሆንም እግዚአብሔር እነዚህን ሸክሞች ከእኛ ጋር እና ለእኛ ይሸከማል” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ “በድክመቶቻችን ምክንያት ተስፋ ብንቆርጥም እግዚአብሔር ኃይሉን የሚገልጥበት ትክክለኛ ጊዜው ያ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ቃለ-ምዕዳናቸውን በማሰማት ላይ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ቃለ-ምዕዳናቸውን በማሰማት ላይ   (@Vatican Media)

በዚህ መንገድ ክርስቲያኖች በእውነት ከላይ እንደሚወለዱ፣ በእግዚአብሔር ኃይል የኢየሱስ ክርስቶስ ወንድሞች እና እህቶች እንደሚሆኑ እና ቤተ ክርስቲያን በቅዱሳት ምስጢራት ዘወትር እንደምትመግባቸው አስረድተዋል።

የበጎነት እና የምስክሮች ማህበረሰብ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በመቀጠልም፥ ምእመናን በክርስቲያኖች መካከል ባለው ተጨባጭ መንፈሳዊ አንድነት ላይ እንዲያሰላሰሉበት ጋብዘው፥ እያንዳንዱ ሰው ሁሉን የሚያገኝበት፣ አንድ አካል ሆነው ያላቸውን ሃብት እርስ በርስ የሚጋሩበት፣ በድህነት እና በጭቆና መካከል ክርስቲያኖችን የሚመራው በጎ ሥራቸው መሆኑን በድጋሚ ገልጸዋል።

እግዚአብሔር በልባችን ውስጥ በጻፈው በዚህ ሕግ መሠረት ቤተ ክርስቲያን ያለማቋረጥ እንደገና እንደምትወለድ፣ እጅግ በሚያስፈልግበት ቦታ ተስፋን፣ ሰብዓዊ ክብርን እና እርቅን እንደምታቀርብ አስረድተዋል።

ቤተ ክርስቲያን የእያንዳንዱን ቋንቋ እና ባሕል ሕዝቦች እንደምትቀበል ያስታወቁት ቅዱስነታቸው፥ሐዋርያት በታላቅ ኃይል የኢየሱስን ትንሣኤ እንደመሰከሩ እና በሁሉም ላይ ታላቅ ጸጋ እንደ ነበረ ገልጸው፥ ይህን እንዲያደርጉ ያነሳሳቸው ልግስና የመዳን ምልክት እንደሆነ እና ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን በመነሳቱ ሕይወታችንም ሊለወጥ እንደሚችል ሐዋርያት መስክረዋል ብለዋል።

ሐዋርያዊ እረኞች ተልዕኳቸውን እንዲያድሱ የቀረበ ጥሪ

ቅዱስነታቸው ለብጹዓን ጳጳሳት እና ለካህናት ባስተላለፉት መልዕክት፥ ይህ ተልዕኮ በአደራ የተሰጣቸው ሰዎች ዘወትር እንዲያድሱት አሳስበው፥ ለክርስቲያኖች በሙሉ የአዲስ ሕይወት መልዕክት መሆን እንዳለበት አስገንዝበዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በመጨረሻም፥ ሐዋርያዊ እረኞች ፍርሃት እንዲያሳስታቸው ወይም ሌሎች ተግዳሮቶች ምስክርነታቸውን እንዲያዳክሙ መፍቀድ እንደሌለባቸው አስጠንቅቀው፥ እንደ ቅዱስ አጎስጢኖስ እና ሰማዕታት ፈለግ በአልጄሪያ የሚገኙ ክርስቲያኖች በአገራቸው ውስጥ የዓለም ጨው እና የዓለም ብርሃን እንዲሆኑ ጋብዘዋል።

“ውድ የአልጄሪያ ክርስቲያኖች ሆይ! በዚህች ምድር የኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅር ትሑት እና ታማኝ ምልክቶች ሆናችሁ በእውነተኛ የእርስ በርስ ግንኙነቶች እና በየቀኑ በምታደርጉት ውይይቶች በኩል ወንጌልን መስክሩ፤ በዚህ መንገድ በምትኖሩባቸው ቦታዎች ሁሉ መልካም ጣዕም እና ብርሃን ትሆናላችሁ” በማለት ቃለ-ምዕዳናቸውን ደምድመዋል።

በአልጄሪያ አናባ ከተማ ውስጥ የሚገኘው የቅዱስ አጎስጢኖስ ባዚሊካ
በአልጄሪያ አናባ ከተማ ውስጥ የሚገኘው የቅዱስ አጎስጢኖስ ባዚሊካ   (@Vatican Media)

 

15 Apr 2026, 16:40