ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ፥ ዓመፅ የሌለበት የብርሃነ ትንሳኤውን ኃይል በመጥቀስ የሰላም ጥሪ አቀረቡ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
በዓለም ዙሪያ ባሉ አገሮች ዓመፅ እና ጦርነት እየተስፋፋ ባለበት ወቅት፣ ዜናዎች በየቀኑ እየጨመረ የስለመጣው ውጥረት እና እየጨመረ ያለውን የሞት ቁጥር እየዘገቡ ባሉበት በዚህ ወቅት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በኢየሱስ ክርስቶስ ሕማማት መታሰቢያ ሳምንት እና በሞት ላይ ድልን በተቀዳጀበት በብርሃነ ትንሳኤው መታሰቢያ በዓልም ለሰላም የማያቋርጥ ጥሪዎችን አቅርበዋል።
“ወንድሞች እና እህቶች ሆይ! ይህ የሰላም ንጉሥ እና አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ጦርነትን የሚቃወም እና ጦርነትን ለማካሄድ ማንም ሊጠቀምበት የማይችል አምላክ ነው” በማለት ለካቶሊካዊ ምዕመናን ታላቅ ሳምንት መጀመሪያ በሆነው በበዓለ ሆሳዕና እሑድ ባሰሙት ቃለ ምዕዳን ላይ ተናግረዋል።
ቅዱስነታቸው በቃለ ምዕዳናቸው፥ እግዚአብሔር ጦርነት የሚያካሂዱትን እና እጆቻቸው በደም የተበላሸ ሰዎች ጸሎት እንደማይሰማ ገልጸው፥ በስቅለተ ዓርብ ሮም ውስጥ ኮሎሲየም በተባለ ሥፍራ በተፈጸመው የመስቀል መንገድ ሥነ-ሥርዓት ላይ የሰዎችን ስቃይ ለመግለጽ መስቀልን በመሸከም፣ በጦርነት እየተሰቃዩ የሚገኙትን በማስታወስ በብርሃነ ትንሳኤው እሑድ ለመላው ዓለም እና ለሮም ነዋሪዎች ባስተላለፉት የብርሃነ ትንሳኤው በዓል መልዕክታቸውም፥ “መሣሪያ የታጠቁት መሣሪያቸውን እንዲያስቀምጡ፣ ግጭቶችን የማስቆም ኃይል ላላቸው ሰዎችም የሰላም ጥሪ አቅርበዋል።
“ሰይፍ የሚያነሱ ሁሉ በሰይፍ ይጠፋሉ” (ማቴ. 26፡52)
የሕማማት ሳምንት የተጀመረው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳስ ሊዮ 14ኛ እሑድ መጋቢት 20/2018 ዓ. ም. በዓለ ሆሳዕናን ምክንያት በማድረግ ከ40,000 በላይ ምዕመናን በተገኙበት በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ባቀረቡት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ነበር። በመስዋዕተ ቅዳሴው ሥነ-ሥርዓት ላይ የተገኙት በርካታ ምዕመናን የሰላም ንጉሥ የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን ለመግለጽ ዘንባባቸውን ከፍ ማድረጋቸውን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ሰዎች ሰይፍ እና ዱላ ሲያነሱበት የሰውን ልጅ ለማዳን ሲል ራሱን ማቅረቡን አስታውሰዋል።
በቅዱስ ወንጌል ውስጥ እንደተጻፈው፥ ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ እርሱን ለመከላከል መሣሪያ ሲስል አይቶ ኢየሱስ ክርስቶስ፥ “ሰይፍህን ወደ ቦታው መልስ፤ ሰይፍ የሚያነሱ ሁሉ በሰይፍ ይጠፋሉ”ሲል የተናገረውን ቃል አስታውሰዋል።
ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱን አላስታጠቀም፣ ራሱንም አልተከላከለም፣ ጦርነትን አልተዋጋም” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ “ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱን ከማዳን ይልቅ፣ በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ በእያንዳንዱ ጊዜ እና ቦታ የተፈጠረው መከራ በሙሉ በጫንቃው ተሸክሞ ራሱን በመስቀል ለመቸንከር ፈቅዷል” ብለዋል።
ስልጣንን አላግባብ ከመጠቀም መልካም ነገር ሊገኝ አይችልም
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በቅዱስ ጴጥሮስ ባሲሊካ ውስጥ ባቀረቡት የጸሎተ ሐሙስ መስዋዕተ ቅዱሴ ላይ ባሰሙት ቃለ ምዕዳን፥ እያንዳንዱን የሰውን ልጅ ህልውና ገጽታ የሚነካ፣ በተለይም በዚህ ጨለማ እና የተበታተነ ዓለም ውስጥ የተለያዩ ኃይሎች የሚያወድሙትን ሰላምን አስታውሰዋል።
“በሐዋርያዊ አገልግሎት ዘርፍ፣ በማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ዘርፎች ስልጣንን አላግባብ በመጠቀም መልካም ነገር ሊመጣ አይችልም” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ስልጣንን አላግባብ በመጠቀም የተነሳ “የኢምፔሪያሊስት ሥርዓት የዓለም ወረራ ከውስጥ ሊታወክ እንደሚችል ገልጸው፥ እስካሁን ድረስ በሕግ ሥር የነበረው ዓመፅ ገሃድ መሆኑን ገልጸው፥ “ድሃው፣ የታሰረው እና የተናቀው ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ሞት ጨለማ ቢወርድም ነገር ግን አዲስ ፍጥረትን ወደ ብርሃን ያመጣል” ሲሉ አስረድተዋል።
ኢየሱስ ክርስቶስ፥ ራስን የመስጠት፣ የአገልግሎት እና የፍቅር ምሳሌ ሆኖልናል
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በሮም በሚገኘው የቅዱስ ዮሐንስ ዘ ላተራን ጳጳሳዊ ባሲሊካ ውስጥ የጌታን እራት ለማስታወስ በቀረበው መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ከአንድ ዓመት ገደማ በፊት የሾሟቸውን የወጣት ካህናት እግር አጥበዋል።
“ይህ ምሳሌያዊ ሥነ-ሥርዓት የእግዚአብሔርን የማንጻት ኃይል የሚያስታውሰን መሆኑን የተናገሩት ቅዱስነታቸው፥ ግጭቶችን ብቻ ሳይሆን የጣዖት አምልኮን፣ ስም ማጥፋትን እና የተበላሸ ስብዕናችን የመሳሰሉ የተዛቡ ተግባራትን ጭምር ያጥባል” ሲሉ ተናግረዋል።
“በሌሎች ላይ የበላይነትን ስናሳይ ራሳችንን ኃያላን እናደርጋለን፥ እኩዩቻችንን ስንገድል አሸናፊዎች እንመስላለን፣ በሌሎች ስንፈራ ራሳችንን ታልቅ አድርገን እንቆጥራለን” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ “ነገር ግን በተቃራኒው እንደ እውነተኛ አምላክ እና እውነተኛ ሰው ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱን አሳልፎ በመስጠት የአገልግሎት እና የፍቅር ምሳሌ ሆኖልናል” ብለዋል።
የኢየሱስ ክርስቶስን ፈለግ መከተል
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በሕማማት ሳምንት የሰላም ጥሪያቸው፥ በክፋት እና በፍቅር መካከል ያለውን ዘላቂ ልዩነት በመግለጽ፥ እንዲሁም በኮሎሲየም መስቀል ተሸክመው ያቀረቡት የመስቀል መንገድ ጸሎት እና የቅድስት ምድር የቀድሞ ተንከባካቢ አባ ፍራንችስኮ ፓተን ያዘጋጁት የአስተንትኖ ጽሑፍም ይህንን ተመሳሳይ ውጥረት እንደሚያስተጋባ አስረድተዋል።
አባ ፍራንችስኮስ ፓተን በአስተንትኖአቸው፥ ኢየሱስን በሚከተሉት እና በእርሱ ላይ በሚያፌዙት ወይም በሚሰድቡት መካከል ያለውን ልዩነት በማስታወስ፥ “የዕለት ተዕለት ሕይወታችን እውነታም ይህ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በአሲሲ ቅዱስ ፍራንችስኮስ የተዘጋጀውን እና በስቅለተ ዓርብ ምሽት የኢየሱስ ክርስቶስን ፈለግ በመከተል ወደ 30,000 የሚጠጉ ምእመናን በኮሎሲየም ያቀረቡት ተመሳሳይ የመስቀል መንገድ ጸሎትን አስታውሰዋል።
እግዚአብሔር እንድንሞት አይፈልግም
በብርሃነ ትንሳኤው ዋዜማ በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ የነበሩ ወደ 6,000 የሚደርሱ ምዕመናን ጨለማ አጅቦአቸው እንደ ነበር የገለጹት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ እግዚአብሔር ሞታችንን እንደማይፈልግ ገልጸው፥ ተጎጂዎችን ወደ ቁጥር ብቻ የሚቀንሰውን የግጭት ትረካዎችን አስታውሰዋል።
“ሰው ሥጋን ሊገድል ቢችልም የፍቅር አምላክ ከሞት በላይ እንደ ሆነ እና መቃብር ሊያስረው የማይችል የዘላለም ሕይወት ነው” ሲሉ አስረድተዋል።
ቅዱስነታቸው እግዚአብሔር እስራኤላውያንን ከግብፅ ባርነት ነፃ ያወጣበትን ባሕር ጠቅሰው፥ “አዲስ የሰላም እና የአንድነት ዓለም እንዲፈጠር በማሳሰብ፥ አዲስ የነፃነት ሕይወት መግቢያ በር በማለት የገለፁት ቦታ የሞት ሥፍራ እንደሆነም ገልጸዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በሜዲትራኒያን ባሕር ከሊቢያ በተነሳ አንድ ጀልባ ላይ አደጋ መድረሱ ሌላ አሳዛኝ ሁኔታ እንደሆነ እና በዚህ አደጋ ምክንያት ቢያንስ 70 ሰዎች መሞታቸው ወይም መጥፋታቸው ሲታወቅ፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በሜዲትራኒያን ውስጥ የስደተኞች መዳረሻ የጣሊያን ደሴት ላምፔዱሳ መጭው ሰኔ 27/2018 ዓ. ም. በመሄድ በሕይወት የተረፉትን እንደሚጎበኟቸው ታውቋል።
“እግዚአብሔር ከእኛ ጋር የሚኖር ሕያው አምላክ ነው”
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በብርሃነ ትንሳኤው እሁድ ጠዋት በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከተሰበሰቡት 60,000 ምዕመናን ጋር የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎትን በማቅረብ፥ ሞት ዘወትር የሚያደናቅፍ መሆኑን ተናግረዋል።
“ሞት በኢፍትሃዊነት፣ በራስ ወዳድነት፣ ድሆችን በመጨቆን እና እጅግ ለተቸገሩት ትኩረት ባለመስጠት የሚደርስ መሆኑን እናያለን” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ በዓመፅ፣ ዓለምን በደረሰ ቁስል፣ ከመካከላችን እጅግ ደካማ በሆኑት ላይ በሚደርሱ በደሎች በኩል፣ የምድርን ሃብት በሚዘርፍ የትርፍ ጣዖት፣ በሚገድል እና ንብርተን በሚያጠፋ የጦርነት ዓመፅ እና ከየአቅጣጫው በሚወጣው የሥቃይ ጩኸት በኩል ሞትን እናየዋለን” ብለዋል።
ሆኖም አንድ ሰው የኢየሱስ ክርስቶስ መቃብር ባዶ መሆኑን ለማወቅ ዓይኑን ከፍ አድርጎ መመልከት እንደሚገባ አሳስበው፥ በእያንዳንዱ ሞት ውስጥ ከመቃብር እና ከመከራ ባሻገር አዲስ ሕይወት እንዳለ የሚገልጸውን የብርሃነ ትንሳኤውን ግብዣ መቀበል እንደሚገባ በድጋሚ ተናግረዋል።
“እግዚአብሔር ሕያው እና ከእኛ ጋርም ይኖራል” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ ጨለማን በሚያበራው የትንሣኤ ምስጢር ለሚደግፈን ተስፋ የልባችንን አደራ መስጠት እንደሚገባ እና “የሞት ኃይል የሕይወታችን የመጨረሻ ዕጣ ፈንታ ሊሆን አይችልም” ሲሉ ተናግረዋል።
“ክርስቶስን ከሞት ያስነሳው ኃይል ሙሉ በሙሉ ዓመፅ የሌለበት ነው”
በመጨረሻም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ብርሃነ ትንሳኤውን በማስመልከት ለመላው ዓለም እና ለሮም ከተማ ነዋሪዎች ባስተላለፉት መልዕክት፥ በዓለም ላይ ለሚሆነው ነገር ግድየለሽ መሆን እንደማይገባ አሳስበዋል።
“ዓመፅን እየተለማመድን፣ በእርሱ እየተገዛን እና ግድየለሾች እየሆንን እንገኛለን” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ በሺዎች በሚቆጠሩ ሰዎች ላይ በሚደርስ ሞት፣ ግጭት ለሚዘራው ጥላቻ እና መከፋፈል፣ በሁላችንም ላይ ለሚደርሱ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ውጤቶች ግድየለሾች ነን” ብለዋል።
“ኢየሱስ ክርስቶስን ከሞት ያስነሳው ኃይል ሙሉ በሙሉ ዓመፅ የሌለበት እንደሆነ እና የዓለም ጦርነቶች በዚህ የብርሃነ ትንሳኤው ምሳሌ የጦር መሣሪያን ባልታጠቁ እጆች አመጽን እና ጦርነትን ማሸነፍ እንዳለባቸው ጠቁመዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ከካስቴል ጋንዶልፎ ለፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና ለዓለም መሪዎች በሙሉ ባቀረቡት ጥሪ፥ “ወደ ውይይት ተመልሳችሁ ለችግሮች መፍትሄን እንድትፈልጉ በተለይም በብርሃነ ትንሳኤው ወቅት ሰላም በልባችን ውስጥ እንዲነግሥ ለማድረግ ዓመፅ የሚቀነስባቸው መንገዶች እንድትፈልጉ” በማለት ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል።
