ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ፥ ባሕሮች የሰላም እና የጋራ መበልጸጊያ ሥፍራ ሊሆኑ ይገባል ሲሉ አሳሰቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በአልጄሪያ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ከአገሪቱ የሲቪል ባለስልጣናት ጋር ተገናኝተው ንግግር አድርገዋል። ቅዱስነታቸው ለባለስልጣናቱ ባስተላለፉት መልዕክት፥ የሰው ልጅ ክብር ፈጽሞ ሳይደፈር እና ሳይበዘበዝ ማኅበረሰቡን የሰላም ምንጭ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በአልጄሪያ ሐዋርያዊ ጉብኝት መጀመሪያ ቀን በዋና ከተማ አልጄርስ ከባለስልጣናት፣ ከሲቪል ማኅበረሰብ ተወካዮች እና ከዲፕሎማሲያዊ አካላት ጋር ተገናኝተው መልዕክት አስተላልፈዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ከአገሪቱ ፕሬዝዳንት አብደልማጂድ ቴቡኔ ጋር በቤተ መንግሥት ከተገናኙ በኋላ በጃማ ኤል ጃዛየር የስብሰባ ማዕከል ወደ 1,400 ለሚጠጉ የሲቪል ባለስልጣናት ንግግር አድርገዋል።

ቅዱስነታቸው በቅዱስ ጴጥሮስ መንበር ስልጣን የመጀመሪያ ዓመታቸው አልጄሪያን ለመጎብኘት ላቀረበላቸው ግብዣ ፕሬዚዳንቱን ካመሰገኑ በኋላ እንድ ቅዱስ አጎስጢኖስ ማኅበር ተከታይ በጎርጎሮሳውያኑ 2004 እና 2013  ዓ. ም. አናባን መጎበኝታቸውን አስታውሰዋል።

የሰላም መንፈሳዊ ተጓዥ ሆነው ወደ አልጄሪያ መምጣታቸውን የገለጹት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ “በሰማያት ላይ ባለን አንድ አባት ስም እኛ ሁላችን ወንድማማቾች እና እህቶች ነን” ብለው፥ እርስ በርስ የመገናኘት፣ የማስታረቅ፣ የአንድነት፣ የእንግዳ ተቀባይነት እና ለማኅበረሰባዊነት መንፈስ የአልጄሪያን ሕዝብ አመስግነዋል።

የአልጄሪያ ሕዝብ ያሳየውን ታላቅ ለጋስነት ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ይህም ከሃብት ጋር የተያያዘ ከፍትህ ስሜት የሚመነጭ ነው” ብለው፥ “ይህ የፍትህ አመለካከት የእግዚአብሔርን ምስል በሌሎች ውስጥ የሚያይ በመሆኑ ቀላል እና ሥር ነቀል ነው” ብለዋል። አክለውም “በእርግጥም ምሕረት የሌለው ሃይማኖት እና አንድነት የሌለው ማኅበረሰብ በእግዚአብሔር ዓይን የተሳሳተ ነው” ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የአልጄሪያ የሲቪል ባለሥልጣናት ለዓለማችን ፍትህን ለማምጣት ውይይትን እና አንድነትን እንዲያጎለብቱ ጋብዘዋቸው፥ “የእያንዳንዱን ሰው ክብር በማስጠበቅ እና የሌሎችን ሕመም በመስማት፥ አለመግባባቶችን እና ግጭቶችን ከማብዛት ይልቅ በታሪክ ውስጥ የአዲስ ምዕራፍ ዋና ተዋናዮች መሆን ትችላላችሁ” ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤነዲክት 16ኛ እና ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ የግሎባላይዜሽን ሂደትን በማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተሳትፎ ሞዴል መምራት አስፈላጊ እንደሆነ መናገራቸውን አስታውሰው፥ “ይህም ሰዎችን እና አገራትን በሙሉ በዓለም ኢኮኖሚ ዕድገት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ ነው” ብለዋል።

“ስለዚህ በዚህች አገር የስልጣን ቦታ ላይ ያላችሁ በሙሉ ይህንን አመለካከት ከመፍራት ይልቅ በተለይ ወጣቶች የተስፋ አድማስን ማስፋት እንደሚችሉ የሚታወቁበትን ሕያው፣ ጠንካራ እና ነፃ የሆነ ማኅበረሰብን እንዲያበረታቱ አደራ ብለዋል።

የአንድ ሀገር እውነተኛ ጥንካሬ የሚለካው ባለሥልጣናት ጫናን በማሳደር ሳይሆን ነገር ግን በዜጎች መካከል ትብብርን በማሳደግ እና ሁሉንም ሰው የሚያሳትፍ ልማትን በማራመድ መሆኑን ተናግረው፥ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ለአልጄሪያን የጋራ ጥቅም ድጋፍ ለማድረግ እና የአገሪቱን ማንነት በሁሉም አገራት መካከል እንደ ድልድይ እንደምታጠናክር ቃል ገብተዋል።

“ባሕርና በረሃ ለሺህ ዓመታት በሰዎች እና በባሕሎች መካከል የጋራ መበልጸጊያ ቦታዎች ነበሩ” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ እነዚህን ቦታዎች ተስፋ የሚሞትባቸው የመቃብር ሥፍራነት መቀየር የለብንም” ብለው፥ “በረሃዎች እና ባሕሮች ግርማ ሞገስ የተላበሱ ናቸው” ሲሉ አክለዋል። ወሰን የሌለው ሰፊነታቸው ሰዎች ስለ ልዕለ ኃያልነት እንዲያስቡ ሊረዳቸው እንደሚችል ተናግረዋል።

“እነዚህን አስደናቂ የታሪክ እና የወደፊት ሕይወት ሥፍራዎችን ከክፋት ነፃ እናውጣቸው” ብለው፥ ተስፋ የመቁረጥ ምክንያቶችን በማስወግድ እና ከሌሎች የመጥፎ ዕድል ተጠቃሚዎች በማዳን የሰላም ቦታዎች እናድርጋቸው ሲሉ አሳስበዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ የአልጄሪያ ባለ ሥልጣናት መንፈሳዊ ጉልበታቸውን፣ እውቀታቸውን እና ሃብቶችን በማስተባበር መሬቱ እና ባሕሩ ሕይወት የሚኖርባቸው፣ ሰዎች እርስ በርስ የሚገናኙባቸው እና የሚያደንቋቸው ቦታዎች፣ እንዲያደርጓቸው አሳስበዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በንግግራቸው ማጠቃለያ፥ የአልጄሪያ ሲቪል ባለስልጣናት ልዩነት ተስፋን ሳያስቆርጣቸው ነገር ግን በብልሃት እንዲጋፈጧቸው አሳስበው፥ “ልዩነት ልባቸውን ነፃ የሚያደርጉ እና ሕሊናቸውን የሚጠብቁ ሰዎች ከታላላቅ መንፈሳዊ እና ሃይማኖታዊ ወጎች አንጻር ዓለምን የሚያዩበት አዳስ መንገድ፥ በሕይወት ውስጥ የማይናወጥ ዓላማን ሊጠቀሙ የሚችሉበት እና በአዲስ ዘመን ውስጥ እንደሚኖሩ የሚያሳይ ምልክት ነው” ሲሉ አስረድተዋል።

14 Apr 2026, 16:36