ፈልግ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የአልጄሪያ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን ፈጽመው ወደ ካሜሩን መጓዛቸው ተገለጸ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በአልጄርስ ውስጥ የሚገኘውን የካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን የሕፃናት ማሳደጊያን ከጎበኙ በኋላ በአልጄሪያ ሲያደርጉ የቆዩትን ሐዋርያዊ ጉብኝት መፈጸማቸው እና በአራት የአፍሪካ አገሮች የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ሁለተኛ መዳረሻ እገር ወደ ሆነች ወደ ካሜሩን ተጉዘዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የአራት አፍሪካ አገራት ሐዋርያዊ ጉብኝት የመጀመሪያ ዙር አጠናቅቀው ረቡዕ ሚያዝያ 7/2018 ዓ. ም. ጠዋት ከአልጄርስ “ሁዋሪ ቡሜዲኔ” ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ በአካባቢው የሰዓት አቆጣጠር ከረፋዱ አራት ሰዓት ከሩብ አካባቢ ወደ ካሜሩን የተጓዙ ሲሆን፥ ወደ ካሜሩን ያውንዴ-ንሲማለን ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ የሚደርሱት ረቡዕ ዕለት ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት አካባቢ እንደሚሆን ተገልጿል።

ቅዱስነታቸው ወደ አልጌርስ አየር ማረፊያው ከመድረሳቸው በፊት በአልጄሪያ የቅድስት መንበር ሐዋርያዊ እንደራሴ ጽሕፈት ቤትን ተሰናብተው፣ በሚስዮናዊ የበጎ አድራጎት እህቶች የሚተዳደረውን የአፍሪካ እመቤታችን ማርያም መዋዕለ ሕጻናትን የጎበኙ ሲሆን፥ ሕጻናቱ ለቅዱነታቸው አጭር ትርኢት ካቀረቡላቸው በኋላ ሰላምታ ተለዋውጠዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ሰኞ ሚያዝያ 5/2018 ዓ. ም. ወደ አልጀርስ ሲደርሱ የክብር አቀባበል ከተደረገላቸው በኋላ የአገሪቱን ፕሬዝዳንት አብደልማጂድ ቴቡኔን በቤተ መንግሥታቸው መጎብኘታቸው፣ ቀጥለውም የማቃም ኢቻሂድ የሰማዕታት መታሰቢያን ከጎበኙ በኋላ ከባለስልጣናት፣ ከሲቪል ማኅበረሰብ ተወካዮች እና ከዲፕሎማሲያዊ አካላት ጋር ተገናኝተው የአልጀርስን ታላቁን መስጊድ መጎብኘታቸው ይታወሳል።

በተጨማሪም በባብ ኤል ኦውድ በሚገኘው የቅዱስ አጎስጢኖስ የወዳጅነት ማዕከል ውስጥ ሚስዮናውያን እህቶች አቀባበል ካደረጉላቸው በኋላ እና በአፍሪካ እመቤታችን ባዚሊካ ውስጥ ከአልጄሪያ ማኅበረሰብ ጋር መገናኘታቸውም ይታወሳል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በአልጄሪያ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ሁለተኛ ቀን ማለትም ማክሰኞ ሚያዝያ 6/2018 ዓ. ም.  ቅዱስ አጎስጢኖስ ጳጳስ ሆኖ ወዳገለገለባት አናባ ከተማ ተጉዘው እንደ ነበር ይታወሳል።

ቅዱስነታቸው በአናባ የአርኪኦሎጂ ቦታውን ከጎበኙ በኋላ በትናንሽ የድሆች እህቶች ማኅበር በሚተዳደረው የእንክብካቤ ማዕከል ውስጥ ከበርካታ አረጋውያን ጥቂት ጊዜ ካሳለፉ በኋላ ከሰዓት በኋላ በቅዱስ አጎስጢኖስ ባዚሊካ ውስጥ የቀረበውን መስዋዕተ ቅዳሴን መርተዋል።

ረቡዕ ሚያዝያ 7/2018 ዓ. ም. ጠዋት የአልጄሪያ ፕሬዝዳንት አብደልማጂድ ቴቡኔ፣ የሲቪል ማኅበረሰብ እና የቤተ ክርስቲያን ተወካዮች በተገኙበት በአውሮፕላን ማረፊያው ለቅዱስነታቸው አጭር የስንብት ሥነ-ሥርዓት ተደርጎላቸዋል።

15 Apr 2026, 16:50