ፈልግ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ሰላም ተቀባይነት ኖሮት በተግባር እንዲገለጽ አሳሰቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ በካሜሩን ባሰሙት የመጀመሪያ ይፋዊ ንግግር፥ ሰላም፣ ፍትህ እና የጋራ ጥቅም አዲስ ቁርጠኝነት እንደሚያስፈልጋቸው በመግለጽ፥ ሰላም ወደ መፈክርነት መቀየር እንደሌለበት አሳስበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ረቡዕ ሚያዝያ 7/2018 ዓ. ም. ወደ ካሜሩን ከደረሱ በኋላ በመዲናዋ ያውንዴ በሚገኘው ቤተ መንግሥት ውስጥ ለባለሥልጣናት፣ ለሲቪል ማኅበረሰብ ተወካዮች እና ለዲፕሎማቶች ንግግር አድርገዋል።

ለባለሥልጣናቱ ባደረጉት ንግግር፥ ለሰላም፣ ለፍትህ እና ለጋራ ጥቅም አዲስ ቁርጠኝነት እንደሚያስፈልግ ጥሪ አቅርበው፥ ካሜሩንውያን ልዩነታቸውን የአንድነት እና የጥንካሬ ምንጭ አድርገው እንዲመለከቱት አሳስበዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በመካከለኛዋ የአፍሪካ አገር ሐዋርያዊ ጉብኝት ሲጀምሩ ለተደረገላቸው ደማቅ አቀባበል ምስጋናቸውን አቅርበው፥ ካሜሩንን በባሕል እና በተፈጥሮ ሃብቶቿ ብዛት “ትንሿ አፍሪካ” ሲሏት ገልጸዋት፥ “ብዝሃነቷ አቅመ ደካማነት ሳይሆን ሃብት ነው” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ የወንድማማችነት ቃል ኪዳን እና ዘላቂ ሰላም ለመገንባት ጠንካራ መሠረት መሆኑን አስረድተዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ለባለስልጣናቱ ንግግር ሲደርጉ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ለባለስልጣናቱ ንግግር ሲደርጉ   (@Vatican Media)

የውይይት እና የተስፋ ተልዕኮ

ራሳቸውን የውይይት፣ የወንድማማችነት እና የሰላም ሐዋርያዊ እረኛ እና አገልጋይ ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ለሁሉም ካሜሩንያን ቅርብ የመሆን ምልክት እና የጋራ ጥቅምን ለመገንባት እንዲነሳሱ ለማበረታታት የታሰበ መሆኑን ገልጸዋል።

በዓለም ውስጥ ተስፋ መቁረጥ መኖሩን የተናገሩት ቅዱስነታቸው፥ ተስፋ መቁረጥ ሲስፋፋ እና አንገብጋቢ ፈተናዎች ሲያጋጥሟቸው ብዙዎች አቅመ ቢስ እንደሚሆኑ ቢገነዘቡም በተለይም በወጣቶች መካከል ለፍትህ እና ለሰላም ከፍተኛ ጥማት መኖሩን ተናግረው፥ የበለጠ ፍትሃዊ ማኅበረሰብን በመገንባት ረገድ ወጣቶች ንቁ ሚና እንዲጫወቱ ጥሪ አቅርበዋል።

ቅድስት መንበር ከካሜሩን ጋር ያላትን ትብብር ለማጠናከር ያላትን ቁርጠኝነት አረጋግጠው፥ ይህም ለሰብዓዊ ክብር እና ለሃይማኖት ነፃነት ወሳኝ እንደሆነ አስረድተዋል።

ማኅበረሰብን በትህትና እና በኃላፊነት ማገልገል

የቀደሙት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ውርስን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፥ ስለ ተስፋ፣ ስለ እርቅ እና ስለ ኃላፊነት ያስተላለፉት ጥሪ ዘላቂ ጠቀሜታ እንዳለው ጠቁመዋል።

የቅዱስ አጎስጢኖስን ንግግር በመጥቀስ፥ ሥልጣን በመሠረቱ የአገልግሎት ዓይነት መሆኑን ባለስልጣናትን በማስታወስ፥ የሚያስተዳድሩ ሰዎች ለሥልጣን ባላቸው ፍቅር ሳይሆን ሌሎችን ለማገልገል ባደረባቸው የግዴታ ስሜት መሆን እንዳለበት አስረድተው፥ “እንዲህ ዓይነቱ አገልግሎት በቁጥር ዝቅተኛ የሆኑትን ጨምሮ ለሁሉ ሰው ጥቅም ቁርጠኝነትን እና በኅብረተሰቡ ውስጥ ስምምነትን ማስፋፋትን ይጠይቃል” ብለዋል።

በመከራ መካከል ስለ ሰላም መጸለይ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ አገሪቱን እያጋጠሟት ያሉ ተግዳሮቶችን በመቃኘት፥ እንደ ሰሜን ምዕራብ፣ ደቡብ ምዕራብ እና ሩቅ ሰሜን ባሉ የአገሪቱ አካባቢዎች የሚከሰተውን ዓመፅ በግልጽ ተናግረው፥ በግጭት ምክንያት የሚፈጠረው ጥልቅ ስቃይ ማለትም የሰዎች ሕይወት መጥፋት፣ የቤተሰቦች መፈናቀል እና ተስፋ የተነፈጉትን ወጣቶችን ጠቅሰዋል።

“ከልዩ ልዩ ስቃዮች በስተጀርባ እውነተኛ የሰዎች መልክ፣ ታሪክ እና የተሰበሩ ተስፋዎች አሉ” ሲሉ ከተናገሩ በኋላ፥ በዓመቱ መጀመሪያ ላይ ያቀረቡትን ጥሪ በማደስ፥ በፍቅር እና በፍትህ ላይ የተመሠረተ ሰላምን በመደገፍ የዓመፅ እና የጦርነት አመክንዮ ውድቅ እንዲደረግ በማሳሰብ፥ ልብን የሚከፍት እና መተማመንን ማሳደግ የሚችል እውነተኛ ሰላም የሚመጣው ያለ መሣሪያ ትጥቅ እና ትጥቅን በማስፈታት እንደሆነ አስረድተዋል።

“ዓለም ሰላምን ተጠምታለች፤ ጦርነት ይብቃ!” ሲሉ አጥብቀው የተናገሩት ቅዱስነታቸው፥ ሰላም ዝቅተኛ ግምት ሳይሰጠው ነገር ግን በዕለት ተዕለት ሕይወት እና በተቋማዊ አሠራር ውስጥ መካተት አለበት ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በካሜሩን ቤተ መንግሥት
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በካሜሩን ቤተ መንግሥት   (@Vatican Media)

የተቋማት እና የሲቪል ማኅበረሰብ ሚና

በሥልጣን ላይ ካሉት ጀምሮ ሰላም የጋራ ኃላፊነት መሆኑን ያረጋገጡት ቅዱስነታቸው፥ “ማስተዳደር ማለት ዜጎችን በእውነት ማዳመጥ እና ዘላቂ መፍትሄዎችን በማግኘት ረገድ ላበረከቱት አስተዋጽኦ ዋጋ መስጠት ማለት ነው” ብለው፥ እንዲሁም ለማኅበራዊ ፖሊሲዎች አዲስ አቀራረብ እንዲደረግ ጥሪ በማቅረብ፥ ያለ ድሆች ተሳትፎ ከሚደረጉ ተነሳሽነቶች አልፎ መሄድ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

የሲቪሉ ማኅበረሰብ ወሳኝ ሚናን ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ የወጣቶች እና የሴቶች ቡድኖችን፣ የሠራተኛ ማኅበራትን፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን እና የሃይማኖት መሪዎችን በማስታረቅ፣ ለተፈናቀሉ ሰዎች እንክብካቤ በማድረግ እና የጋራ ውይይትን በማጎልበት ላደረጓቸው ጥረቶች በሙል ሲቪል ማኅበረሰብን በማድነቅ፥ መሠረታዊ ግንኙታቸው ግጭቶችን ለመፍታት እና የሰላም ባህልን ለማሳደግ ያስችላቸዋል ብለዋል።

ሴቶች በትምህርት እና በማኅበራዊ መልሶ ግንባታ ሳይሰለቹ የሰላም ፈጣሪዎች በመሆን ላበረከቱት አስተዋጽኦ ልዩ ምስጋና አቅርበው፥ “ድምፃቸው በውሳኔ አሰጣጥ ሂደቶች ውስጥ ሙሉ በሙሉ መታወቅ አለበት” ብለዋል።

ታማኝነት፣ ፍትህ እና ሙስናን በመዋጋት

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ተዓማኒነትን ወደ ነበረበት ለመመለስ ግልጽነት፣ የሕግ የበላይነት እና እምነት የተጣለባቸው ተቋማት እንደሚያስፈልጉ ተናግረው፥ ባለስልጣናት የእርስ በርስ ግንኙነት ገንቢዎች እንጂ የክፍፍል ምንጭ መሆን እንደሌለባቸው አሳስበው፥ የደኅንነት እርምጃዎች ዘወትር ሰብዓዊ መብቶችን የሚያስከብሩ መሆናቸው እንዲረጋገጥ ጥሪ አቅርበው፥ “እውነተኛ ሰላም የሚገኘው ሁሉም ሰው ድኅንነቱ ሲጠበቅ፣ ተደማጭነትን ሲያገኝ እና መብቱ እንደተከበረለት ሲሰማው ነው” ብለዋል።

በተጨማሪም ሙስናን ያስጠነቀቁት ቅዱነታቸው፥ “ሙስና ሥልጣንን የሚያበላሽ እና ተዓማኒነቱን የሚገፍፍ ኃይል” ሲሉ ገልጸውት፥ እንዲሁም መሪዎች ራሳቸውን ከትርፍ ጥማት እንዲያርቁ በማሳሰብ፥ ይልቁንም የሰውን ልጅ ዕድገትን እንደ እውነተኛ የዕድገት መለኪያ አድርገው እንዲቆጥሩት አሳስበዋል።

እንግዶች በቤተ መንግሥት ውስጥ የቅዱስነታቸውን ንግግር ሲያዳምጡ
እንግዶች በቤተ መንግሥት ውስጥ የቅዱስነታቸውን ንግግር ሲያዳምጡ   (@Vatican Media)

በወጣቶች እና በወደፊት ላይ መሥራት

ሃሳባቸውን ወደ ወጣቶች ያዞሩት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ “ወጣቶች የአገሪቱ እና የቤተ ክርስቲያን ተስፋዎች ናቸው” ብለው፥ ሥራ አጥነትን፣ መገለልን እና ማኅበራዊ ድህነትን ሊያስከትሉ የሚችሉ አደጋዎች መኖራቸውን አልሸሸጉም።

“በወጣቶች ትምህርት፣ በስልጠና እና በሥራ ፈጠራ ላይ መሥራት ሰላምን ለማሳደግ ስትራቴጂያዊ ምርጫ ነው” ብለው፥ ስደትን ለመከላከል እና አደንዛዥ ዕጽን ለመዋጋት፣ የጉልበት ብዝበዛ የመሳሰሉ ማኅበራዊ ችግሮችን ለመዋጋት ትምህርት ቁልፍ መሆኑን በማሳሰብ፥ የካሜሩን ወጣቶች ጥልቅ መንፈሳዊነት በማድነቅ፥ በአግባቡ ከተንከባከቡት ለሰላም፣ ለፍትህ እና ለአብሮነት ያላቸውን ቁርጠኝነት ሊያነሳሳ እንደሚችል ተናግረዋል።

ወደ እርቅ የሚወስድ የጋራ መንገድ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በሃይማኖቶች መካከል የበለጠ ውይይት እንዲኖር እና የሃይማኖት መሪዎች በእነዚህ ጥረቶች ውስጥ እንዲሳተፉ በማበረታታት፥ ቤተ ክርስቲያን ያለ ልዩነት ለሁሉም የትምህርት፣ የጤና አጠባበቅ እና የበጎ አድራጎት አገልግሎት ለማዳረስ ዘላቂ ቁርጠኝነት እንዳላት በመግለጽ፥ ከሲቪል ባለስልጣናት እና ከዓለም አቀፍ አጋሮች ጋር ሰብዓዊ ክብርን እና እርቅን ለማሳደግ ቀጣይነት ያለው ትብብር ለማድረግ ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ንግግራቸውን ሲያጠናቅቁ፥ ለካሜሩን እና ሕዝቦቿ የእግዚአብሔርን ቡራኬ በመመኘት፥ መላው የካሜሩን ሕዝብ የእግዚአብሔርን መንግሥት ለመቀበል፣ የፍትህ እና የሰላም ጊዜን በጋራ ለመገንባት የሚችልበትን ጸጋን እግዚአብሔር እንዲሰጠው ለምነዋል።

ቅዱስነታቸው በካሜሩን ቤተ መንግሥት

 

16 Apr 2026, 18:45