ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ የሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ሁለተኛ አገር ወደ ሆነች ካሜሩን ገብተዋል

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በአራት የአፍሪካ አገራት የሚያደርጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት በመቀጠል ሚያዝያ 7/2018 ዓ. ም. ወደ ካሜሩን የተጓዙ ሲሆን፥ የካሜሩን ጉብኝታቸው ከአንጎላ እና ከኢኳቶሪያል ጊኒ አስቀድመው የሚያደርጉት ሁለተኛ እንደሆነ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ከአልጄሪያ ተነስተው ወደ ካሜሩን ያውንዴ-ንስማለን ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ የደረሱት ረቡዕ ሚያዝያ 7/2018 ዓ. ም. በአካባቢው ሰዓት አቆጣጠር ከሰዓት በኋላ በስምንት ሰዓት ከሃምሳ ሰባት ደቂቃ ላይ እንደ ነበር ታውቋል።

በቅዱስነታቸው ሐዋርያዊ ጉብኝት መርሃ ግብር መሠረት፥ የጉብኝታቸው የመጀመሪያ አገር ወደ ሆነች አልጄሪያ የደረሱት ሰኞ ሚያዝያ 5/2018 ዓ. ም. ጠዋት እንደ ነበር ሲታወስ፥ በካሜሩን እስከ ቅዳሜ ሚያዝያ 10/2018 ዓ. ም. ድረስ ከቆዩ በኋላ የተቀሩትን አንጎላን እና ኢኳቶሪያል ጊኒን ጎብኝተው ሐሙስ ሚያዝያ 15/2018 ዓ. ም. ወደ ሮም የሚመለሱ መሆኑን የሐዋርያዊ ጉብኝታቸው መርሃ-ግብር ያመለክታል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ወደ ካሜሩን ሲደርሱ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ጆሴፍ ዲዮን ንጉቴ አቀባበል ያደረጉላቸው ሲሆን፥ ቀጥሎም በሁለት ሕጻናት አበባ ከተበረከተላቸው በኋላ የሁለቱም አገራት ልዑካን በተገኙበት ብሔራዊ መዝሙሮች ተዘምረዋል። ከአቀባበል ሥነ-ሥርዓቱ በኋላ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር አጭር የግል ውይይት አድርገዋል።


ቅዱስነታቸው በካሜሩን ያደረጉት የመጀመሪያ ቀን ውሎ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በካሜሩን በሚያደርጉት የመጀመሪያ ቀን ጉብኝታቸው በፕሬዚዳንታዊ ቤተ መንግሥት ከሪፐብሊኩ ፕሬዝዳንት ፖል ባርቴሌሚ ቢያ ጋር ከተገናኙ በኋላ ለአገሪቱን ባለስልጣናት፣ ለሲቪል ማኅበረሰብ ተወካዮች እና ለዲፕሎማሲ አካላት ንግግር አድርገዋል።

ቅዱስነታቸው በመቀጠልም የንጉል ዛምባ ወላጅ አልባ ሕፃናት ማሳደጊያን ጎብኝተው እዚያም ከማዕከሉ ነዋሪዎች እና ሠራተኞች ጋር ሰላምታ ተለዋውጠዋል። በመጨረሻም ከአገሪቱ ብጹዓን ጳጳሳት ጋር በጉባኤው ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት ውስጥ በግል ከተገናኙ በኋላ የዕለቱን መርሃ ግብር ፈጽመዋል።

 

16 Apr 2026, 09:02