ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የፈረንሳዩን ፕሬዝዳንት ማክሮንን በቫቲካን ተቀብለው አነጋገሩ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ጋር የተገናኙት በቫቲካን የቅዱስ ዳማሰስ አደባባይ በሚገኝ ሐዋርያዊ ሕንጻ ውስጥ እንደ ነበር ተገልጿል። ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ከቀዳማዊት እመቤት ብሪጂት ጋር ወደ ቦታው ሲደርሱ አቀባበል ያደረጉላቸው የጳጳሳዊ ቤት ዋና አስተዳዳሪ ሞንሲኞር ሊዮናርዶ ሳፒየንሳ ናቸው።
ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ወደ ትሮኔቶ እንግዳ መቀበያ ከደረሱ በኋላ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ጋር ሰላምታ ተለዋውጠዋል። ፕሬዝዳንቱ ከቅዱስነታቸው ጋር ሲገናኙ ይህ የመጀመሪያቸው ሲሆን ቀደም ሲል በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ መንበር አስተዳደር ዓመታት ቫቲካንን ሦስት ጊዜ መጎብኘታቸው ይታወሳል።
በቅድስት መንበር ጽሕፈት ቤት የተደረገ ውይይት
ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ጋር ከተወያዩ በኋላ የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ከሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን ጋርም የተገናኙ ሲሆን፥ ቀጥለውም በቫቲካን የመንግሥታት እና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ግንኙነት ክፍል ዋና ጸሐፊ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ፖል ሪቻርድ ጋላገር ጋርም ተገናኝተዋል።
የቅድስት መንበር መግለጫ ክፍል፥ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በቅድስት መንበር ጽሕፈት ቤት ያደረጓቸውን የወዳጅነት ውይይቶች በማስመልከት እንደዘገበው፥ በቅድስት መንበር እና በፈረንሳይ መንግሥት መካከል ያለው መልካም ግንኙነት እውቅና ማግኘቱን ግልጾ፥ “ውይይቶቹ በዋናነት በዓለም ዙሪያ ባሉት ግጭቶች ላይ የአመለካከት ልውውጥ በማድረግ፥ በሰላም አብሮ መኖር በውይይት እና በድርድር ሊመለስ እንደሚችል ተስፋ በማድረግ እና ውይይቱ አስፈላጊ በሆኑ ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ነበር” ሲል ገልጿል።
ከቅዱስ ኤጂዲዮ ማኅበረሰብ ጋር የተደረገ ውይይት
ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ሐሙስ ሚያዝያ 1/2018 ዓ. ም. ወደ ሮም ሲደርሱ በቅድሚያ ከጎበኟቸው አንዱ በሮም ትራስቴቬሬ የሚገኘው የቅዱስ ኤጂዲዮ ማኅበረሰብ ሲሆን፣ እዚያ ሲደርሱ የማኅበሩ ፕሬዝዳንት አቶ ማርኮ ኢምፓግሊያዞ፣ የማኅበሩ መሥራች አቶ አንድሪያ ሪካርዲ እና ማሪዮ ጂሮ አቀባበል አድርገውላቸዋል።
የፈረንሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዣን ኖኤል ባሮትን ጨምሮ በበርካታ ልዑካን የታጀቡት ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን የቅዱስ ኤጂዲዮ ማኅበረሰብን መጎብኘት በጀመሩበት ወቅት፥ በኮንጎ ዴሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ ጎማ ውስጥ የሻገተ ምግብ እደላን በመቃወሙ ምክንያት እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2007 ዓ. ም. በተገደለው ወጣት ፍሎሪበርት መታሰቢያ ላይ ተገኝተዋል። ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን የወጣት ፍሎሪበርት ብጽዕናን እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በሰኔ ወር 2025 ዓ. ም. ይፋ ማድረጓ ይታወሳል።
