ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ፥ በፈተና ውስጥ የሚገኙ ካኅናትን በጸሎታችን እንድናስባቸው አሳሰቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ለሚያዝያ ወር እንዲሆን በማሰብ ይፋ ባደረጉት የጸሎት ሃሳብ፥ ካቶሊካዊ ምዕመናን በሙሉ፥ በጥሪያቸው የግል ፈተና ያጋጠማቸውን ካህናት በጸሎት እንዲያስቧቸው አደራ ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በቪዲዮ ምስል በኩል ባስተላለፉት ጥሪ፥ ችግር ላጋጥማቸው ካኅናት በሚያደርጉት የሚያዝያ ወር ጸሎት እንዲተባበሩ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ካቶሊካዊ ምዕመናንን ከአደራ ጋር አሳስበዋል።

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ዓለም አቀፍ የጸሎት መረብ፥ “ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ጋር አብረን እንጸልይ” በሚል ርዕሥ ያዘጋጀውን ወርሃዊ የቪዲዮ መልዕክት ይፋ አድርጓል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ካኅናትን በሙሉ ለእግዚአብሔር አደራ በሰጡበት ጸሎታቸው፥ በተለይም በፈተና እና ችግር ውስጥ ለሚገኙት፣ ብቸኝነት እጅግ ለጎዳቸው፣ ጥርጣሬ ለገባቸው እና ተስፋ ከማድረግ ይልቅ ድካም ለሚሰማቸው ካኅናት የእግዚአብሔርን ድጋፍ ለምነዋል።

አንዳች ቅድመ ሁኔታን ሳያስቀምጥ ትግላቸውን እና ቁስላቸውን አውቆ የሚወዳቸው መሆኑን ለመረዳት ሲጥሩ፥ ተራ እና አጋዥ የሌላቸው ብቸኛ አገልጋዮች ሳይሆኑ ነገር ግን ትሑት እና ጠንካራ ደቀ መዛሙርት መሆናቸውን በማወቅ እግዚአብሔር ካኅናትን የሚወዳቸው መሆኑን ተናግረዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በጸሎታቸው፥ “ቸር አባት ሆይ! ካህናቶቻችንን መንከባከብ አስተምረን፤ ሳንፈርድባቸው ማዳመጥን፣ ፍጹምነታቸውን ብቻ ሳንሻ እንድናመሰግናቸው፥ መንግሥትህን በቃልም ሆነ በተግባር የምናውጅበት የጥምቀት ተልዕኮን ከእነርሱ ጋር መጋራትን እና በቅን ጸሎታችን እንድንደግፋቸው እርዳን” በማለት የእግዚአብሔርን ድጋፍ ጠይቀዋል።

ቅዱስነታቸው ለመላው ካቶሊካዊ ምዕምናን በላኩት የአደራ መልዕክት፥ ብዙ ጊዜ እኛን የሚያገለግሉ ካኅናትን እንድንደግፋቸው በማሳሰብ፥ “መንፈስ ቅዱስ በካህናቶቻችን ልብ ውስጥ የቅዱስ ወንጌልን ደስታ እንደገና እንዲያቀጣጥል” በማለት ጸሎታቸውን አቅርበዋል።

“ለካኅናት ጤናማ ጓደኝነትን፣ ድጋፍ የታከለበት ወንድማዊ ግንኝነትን፣ ነገሮች በሙሉ ባይመቻችላቸውም የጥሪአቸውን ውበት ዘወትር እንደገና የሚያገኙበትን ጸጋ ስጣቸው” በማለት ጸሎታቸውን አቅርበዋል።

“በአንተ ላይ ያላቸውን እምነት እንዳያጡ፣ ቤተ ክርስቲያንህን በትሕትና እና በለጋስነት የሚያገለግሉበትን ደስታን ጭምር በመስጠት እርዳቸው” በማለት ጸሎታቸውን ደምድመዋል”

ለእምነታችን ድጋፍ የሆኑ ካኅናትን ማገዝ

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ዓለም አቀፍ የጸሎት መረብ አስተባባሪ የሆኑት አባ ክሪስቶባል ፎኔስ ከቅዱስነታቸው የቪዲዮ መልዕክት ጋር በማጣመር በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፥ ለካኅናት መጸለይ በተለይ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ሃሳብ ጋር ቅርበት እንዳለው ተናግረዋል።

“ሰብዓዊ አብሮነት፣ ከልብ የመነጨ ወዳጅነት እና ከሁሉም በላይ የጸሎት ድጋፍ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆኑ ማስታወስ አስፈላጊ ነው” ያሉት አባ ፎኔስ፥ በዚህ መሠረት ካኅናት ብቻቸውን እንዳልሆኑ ማወቅ አለባቸው” ብለዋል።

ካኅናት እንደ ማንም ሰው ምሕረት፣ ቅርበት እና ግንዛቤን ማግኘት የሚያስፈልጋቸው ደካማ ሰዎች ናቸው” ሲሉ ገልጸዋል።

ከማኅበራዊ ሕይወት በተጨማሪ ካኅናት በማኅበረሰቦቻቸው እና በመንጋዎቻቸው በኩል የሚደረግላቸው የጸሎት ድጋፍ ሊሰማቸው እንደሚገባ እና የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የሚያዝያ ወር የጸሎት ሃሳብም ምዕመናን በሙሉ ለካኅናት መንፈሳዊ ድጋፍ እንዲያደርጉ ዕድል የሚሰጥ መሆኑ ተገልጿል።

 

09 Apr 2026, 11:38