ፈልግ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ጸሎት፣ በጎነት እና አንድነት ለክርስቲያኖች አስፈላጊ ናቸው” ሲሉ ገለጹ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በአልጄሪያ ለሚገኙ ክርስቲያን ማኅበረሰብ ባደረጉት ንግግር፥ “በጸሎት፣ በበጎ አድራጎት እና በአንድነት እንዲበረቱ አሳስበው፥ እስካሁን ላሳዩት ምስክርነት በማመስገን የሰላም እና የወንድማማችነት ምልክት እንዲሆኑ አሳስበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ከሰኞ ሚያዝያ 5/2018 ዓ. ም. ጀምሮ በአልጄሪያ በማድረግ ላይ ባሉት ሐዋርያዊ ግብኝታቸው፥ በመዲናዋ አልጄርስ ውስጥ በሚገኘው የአፍሪካ እመቤታችን ባዚሊካ ውስጥ ከክርስቲያን ማኅበረሰብ ጋር የተገናኙ ሲሆን፥ ይህም በአገሪቱ የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት አካል እንደሆነ ተገልጿል።

ቅዱስነታቸው በባዚሊካው ውስጥ ለተሰበሰቡት ምዕመናን ሰላምታቸውን አቅርበው፥ ማኅበረሰቡ ጥንታዊ ቅርስ እና የእምነት ምስክሮች ሆነው በመገኘታቸው ጥልቅ ደስታን እና አባታዊ ፍቅርን ገልጸውላቸዋል።

በተለይ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1990ዎቹ በአልጄሪያ የተገደሉትን አሥራ ዘጠኙን ገዳማውያን እና ገዳማውያትን አስታውሰው፥ ሰማዕታቱ ከሕዝብ ጋር በደስታ እና በሐዘን ለመቆም መምረጣቸውን አስታውሰዋል።

“ምስክርነታቸው ዛሬም ሕያው ሆኖ ይቀጥላል” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ “ደማቸው ፍሬ ማፍራቱን የማያቆም ሕያው ዘር ነው” ሲሉ አስረድተው፥ በክልሉ ያለውን ጥልቅ የክርስትና እምነት ታሪካዊ መሠረቶችን በመግለጽ፥ በዚያች ምድር የሚያስተጋባውን የቅዱስ አጎስጢኖስ ማኅበር ገዳም ኃይለኛ ድምፅ ከቅድስት ሞኒካ እና ከሌሎች ቅዱሳን ምሳሌዎች ጋር በማድረግ አስታውሰዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የአልጄሪያ ማኅበረሰብን ሲያገኙ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የአልጄሪያ ማኅበረሰብን ሲያገኙ   (@Vatican Media)

“ሁላችንም መጸለይ አለብን!”

በአልጄሪያ ውስጥ ባለው የቤተ ክርስቲያን ሕይወት ላይ ያሰላሰሉት ቅዱስነታቸው፥ መጀመሪያ በጸሎት ላይ ማትኮር አስፈላጊ እንደሆነ በመግለጽ፥ የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ በአንድ ወቅት ቃለ ምዕዳናቸው፥ “ሰው ሳይተነፍስ ሊኖር እንደማይችል ሁሉ ያለ ጸሎትም ሊኖር አይችልም” በማለት የተናገሩትን በማስታወስ “ሁላችንም መጸለይ አለብን” ብለዋል።  

የአካባቢው ማኅበረሰብ የሚጋራውን ተሞክሮ በመጥቀስ፥ ብዙዎች በጸጥታ ውስጥ ሆነው ጭንቀታቸውን ለመግለጽ፣ ለሚወዷቸው ሰዎች ለመጸለይ እና ሊያዳምጣቸው ፈቃደኛ የሆነ ሰው ለማግኘት ወደ ባዚሊካው እንደሚመጡ ጠቅሰዋል።

“ጸሎት ልብን አንድ ያደርጋል፣ ሰብዓዊነትን ያጎለብታል፣ ያጠናክራል፣ ያጠራልም” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ በጸሎት አማካኝነት በአልጄሪያ የምትገኘው ቤተ ክርስቲያን ሰብዓዊነትን፣ አንድነትን፣ ጥንካሬን እና ንጽሕናን በመዝራት እግዚአብሔር ብቻ ወደሚያውቀው ቦታ ትደርሳለች” ብለዋል።

በጎ አድራጎት ከቁሳዊ ድጋፍ በላይ ነው

የበጎ አድራጎት ሥራን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፥ ለችግር ተጋላጭ የሆኑ ሰዎች በተለይም አካል ጉዳተኛ ልጆችን እና ቤተሰቦቻቸውን የሚያገለግሉትን በማስታወስ፥ እንዲህ ዓይነቱ አገልግሎት የቁሳዊ ፍላጎቶችን ከማሟላት በላይ እንደሆነ በአፅንዖት ተናግረዋል።

“ምህረት እና አገልግሎት ቁሳዊ ዕርዳታ ከመስጠት የበለጡ ናቸው” ብለው፥ ይልቁንም የእግዚአብሔር ጸጋ የሚገኝባቸው እንደሆኑ ገልጸው፥ ይህም ተሳታፊዎች በሙሉ እንዲያድጉ እና እንዲበለጽጉ ያስችላቸዋል” ብለዋል።

ሕሙማንን መጎብኘት የመሳሰሉ ቀላል ድርጊቶች እንዴት ወደ ሰፊው የድጋፍ እና የማኅበረሰብ ሕይወት ማደግ እንደሚችሉ አስታውሰው፥ በዚህ አውድ ውስጥ ጥላቻና ዓመፅ ሲደርስባቸው ታማኝ ሆነው የቆዩትን የሰማዕታትን ምስክርነት በድጋሚ ጠቁመዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በባዚሊካው ውስጥ የተገኙት ምዕመናን ሲባርኩ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በባዚሊካው ውስጥ የተገኙት ምዕመናን ሲባርኩ   (@Vatican Media)

“ሰላም ለእናንተ ይሁን!”

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ስለ አንድነት እና ስለ ሰላም ሲናገሩ፥ የጉብኝታቸው ዋና ጭብጥ ከቅዱስ ወንጌል የተወሰደ መሆኑን በማስታወስ፥ “ሰላም ለእናንተ ይሁን!” በማለት ለምዕመናን ሰላምታቸውን አቅርበዋል።

በታይቤሪኑ ወንድም ሉክ የጻፈውን ጥንታዊ ጽሑፍን በመጥቀስ፥ በእግዚአብሔር ኃይል ሰላም እና ስምምነት በሕይወታችን ውስጥ በአንድነት ይነግሥ” ብለው፥ ከቤተ ክርስቲያን የመጀመሪያዎቹ ቀናት ጀምሮ ሰላም እና ስምምነት ለክርስቲያን ማኅበረሰብ ሕይወት ማዕከላዊ እንደ ነበር አስተውሰዋል።

ባዚሊካውም የዚህ ጥሪ ምልክት እንደሆነ ሲገልጹት፥ “በክርስቲያኖች እና በሙስሊሞች መካከል ያለው ኅብረት የአፍሪካ እመቤታችን ማርያም ምስል የተቀመጠበት የሕያው ድንጋይ ቤተ ክርስቲያንን ይወክላል” ብለዋል።

እምነት ግልጽነትን እና ወንድማማችነትን ሊያበረታታ እንደሚገባ አሳስበው፥ “እምነት ማንንም ሳይለይ አንድ ያደርገናል፣ ግራ መጋባትን ሳይፈጥር ያቀራርበናል” ብለው፥ በክፍፍል እና በግጭት በተሞላ ዓለም ውስጥ በአልጄሪያ ያለው አብሮ የመኖር ተሞክሮ አንድነት እና ሰላም ያለበትን ምስክርነት ይሰጣል” ሲሉ አስረድተዋል።

“በበረሃ ውስጥ ማንም ብቻውን ሊኖር አይችልም”

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በንግግራቸው ማጠቃለያ አብዛኛው የአልጄሪያ ክፍል በረሃማ መሆኑን በመጠቆም፥ በበረሃ ውስጥ ማንም ሰው ብቻውን ሊኖር እንደማይችል አስረድተው፥ እንዲህ ዓይነቱ አካባቢ ሰዎች እርስ በርስ እና ለእግዚአብሔር ያላቸውን ፍላጎት የሚያስታውስ መሆኑን አክለዋል።

“ደካማነታችንን ስንገነዘብ ልባችን እርስ በርስ ለመደጋገፍ ክፍት ይሆናል” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ ምዕመናን ተልእኳቸውን እንዲቀጥሉ በማበረታታት፥ የተባበረ እና ግልጽ የእምነት ማኅበረሰብ ሆነው እንዲቀጥሉ ጥሪያቸውን በማቅረብ ለምስክርነታቸውም አመስግነዋቸዋል።

ቅዱስነታቸው የአልጄሪያ ማኅበረሰብን በጸሎታቸው እንደሚያስታውሱት በማረጋገጥ ቡራኬያቸው ከመስጠታቸው በፊት ለአፍሪካ እመቤታችን ማርያም በአደራ ሰጥቷቸዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ወደ የአፍሪካ እመቤታችን ማርያም ባዚሊካ በመጡበት ወቅት

 

14 Apr 2026, 11:28