ፈልግ

እስራኤል በሊባኖስ ላይ የፈጸመቸ ጥቃት ውጤት እስራኤል በሊባኖስ ላይ የፈጸመቸ ጥቃት ውጤት  (AFP or licensors)

ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ፥ “ሲቪሎችን ከጦርነት አደጋ የመጠበቅ የሞራል ግዴታ አለብን” ሲሉ ተናገሩ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ እሑድ ሚያዝያ 4 /2018 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከተሰበሰቡት ምዕመናን ጋር ሆነው “የእመቤታችን ማርያም የሰማይ ንግሥት” ጸሎት አድርሰዋል። ከጸሎት ሥነ-ሥርዓቱ ቀጥሎ ባደረጉት ንግግር የሱዳን ጦርነት ሦስተኛ ዓመት በማስታወስ፥ “አንድ ማኅበረሰብ በሆኑት መካከል እየተካሄደ ያለው የእርስ በእርስ ጦርነት በተቻለ ፍጥነት እንዲቆም” በማለት ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ቀጥሎም በጁሊያውያን የቀን አቆጣጠር መሠረት የብርሃነ ትንሳኤውን በዓልሩ ለሚያከብሩ የምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት የሰላም መልካም ምኞታቸውን በማቅረብ እንዲሁም የዩክሬን እና የሊባኖስን ሕዝቦችን በጸሎት ማስታወስ እንደሚገባ በማሳሰብ፥ በመጨረሻም ከሚያዝያ 5/2018 ዓ. ም. ጀምሮ በአራት የአፍሪካ አገራት የሚያደርጓቸውን ሐዋርያዊ ጉብኝት ምዕምናን በጸሎት እንዲደግፉ አደራ ብለዋል።

“በእያንዳንዱ የሰው ልጅ ሕሊና ውስጥ የተቀረጸው እና በዓለም አቀፍ ሕግ እውቅናን ያገኘው የሰው ልጅ መርህ፥ ሲቪሉን ሕዝብ ከጦርነት አስከፊ ውጤቶች የመጠበቅ የሞራል ግዴታን ይጠይቃል” ሲሉ አስረድተዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ይህን ሐሳብ መነሻ በማድረግ እሑድ ሚያዝያ 4 /2018 ዓ. ም. ጠዋት በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡት ምዕመናን ንግግር አድርገዋል።

በዩክሬን ላለው አሳዛኝ ጦርነት ትኩረት መስጠት

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ሰላምን በተመኙበት ንግግራቸው፥ “ከሞት በተነሳው በኢየሱስ ክርስቶስ ባለን የጋራ እምነት መሠረት ብርሃነ ትንሳኤውን ለሚያከብሩት የምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት ሰላምን እመኝላቸዋለሁ” ብለዋል። ቅዱስነታቸው በዕለቱ ያቀረቡት ጸሎትም በጦርነት ምክንያት በሚሰቃዩት ሰዎች እና በተለይም በዩክሬን ሕዝብ ላይ ያተኮረ እንደ ነበር ተመልክቷል።

“በጦርነት ምክንያት ልባቸው በሐዘን ለተጎዳባቸው ሰዎች የኢየሱስ ክርስቶስ የትንሳኤ ብርሃን መጽናናትን እና የሰላም ተስፋን እንዲያመጣላቸው፣ ለዚህ አሳዛኝ ጦርነት የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ትኩረት እንዲሰጥ!” በማለት ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

በሊባኖስ ውስጥ ያለው ሕመም፣ ፍርሃት እና ተስፋ

የአውሮፓ እና የመካከለኛው ምሥራቅ አገራት የሐዘን እና የፍርሃት ቀናትን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፥ በእግዚአብሔር ላይ የማይናወጥ ተስፋ ባለው በሊባኖስ ሕዝብ ላይም በማስተንተን፥ በጦርነት ውስጥ የሚገኙ ወገኖች የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደርጉ እና በአስቸኳይ ሰላማዊ መፍትሄን እንዲፈልጉ ጥሪ አቅርበዋል።

“ከፍተኛ ስቃይ የደረሰበት የሱዳን ሕዝብ”

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በዓለም ዙሪያ የሚያደርጉትን ምሳሌያዊ ጉብኝት በመቀጠል፥ ረቡዕ ሚያዝያ 7/2018 ዓ. ም. የሚውለውን የሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት ሦስተኛ ዓመት በማስታወስ፥ “በዚህ ኢ-ሰብዓዊ እና አሳዛኝ ጦርነት በርካታ የሱዳን ንፁሃን ሕዝብ እየተሰቃየ ይገኛል!” ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ “በአንድ ማኅበረሰብ ውስጥ በሚገኙ ወንድማማቾች መካከል እየተካሄደ ያለው ጦርነት ያለ ቅድመ ሁኔታ በፍጥነት እንዲቆም፥ ተዋጊዎችም መሣሪያዎቻቸውን እንዲያስቀምጡ” በማለት ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

ለሐዋርያዊ ጉብኝታቸው የሚቀርቡ ጸሎቶች

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተገኙት ምዕመናን ሰላምታ ካቀረቡላቸው በኋላ ከሚያዝያ 5-15/2018 ዓ. ም. ድረስ በአልጄሪያ፣ በካሜሩን፣ በአንጎላ እና በኢኳቶሪያል ጊኒ ለሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት የምዕመናንን የጸሎት ድጋፍ በመጠየቅ ንግግራቸውን ደምድመዋል።

13 Apr 2026, 17:37