ፈልግ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ የጣሊያን ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ አባላት ንግግር ሲያደርጉ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ የጣሊያን ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ አባላት ንግግር ሲያደርጉ   (@Vatican Media)

ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ፥ “የቤተ ክርስቲያን ፍሬያማነት በአኃዝ ላይ መመሥረት የለበትም” ሲሉ አሳሰቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ 82ኛ ጠቅላላ ጉባኤያቸውን ያካሄዱት የጣሊያን ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ አባላትን ግንቦት 20/2018 ዓ. ም. በቫቲካን ተቀብለው ንግግር አድርገውላቸዋል። ቅዱስነታቸው ለአባላቱ ባደረጉት ንግግር፥ አስፈላጊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ እና ውስብስብ በሆነው በዛሬው ዓለም ውስጥ ለወንጌል ቅድሚያ እንዲሰጡ አሳስበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ በቫቲካን ውስጥ በተካሄደው 82ኛው ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ለተሳተፉት አባላት ባደረጉት ንግግር፥ “በጣሊያን በምትገኝ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለሚያገለግሉ ካህናት፣ ዲያቆናት፣ ገዳማውያን እና ገዳማውያት፣ ምዕመናን እና እግዚአብሔርን ለሚጠሙት በሙሉ ያላቸውን ፍቅር ገልጸዋል።

“ይህ ስጦታ እንደ ዛሬው ውስብስብ በሆነው ዘመን ውስጥ ቢሆን ወንጌልን ለመመስከር የሚያስችል ጸጋ ያለበት ነው” ሲሉ ገልጸው፥ ይህንንም በቅርቡ በፖምፔ፣ በኔፕልስ እና በአሴራ ባደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ወቅት በተጨባጭ የተመለከቱት እንደ ነበር አብራርተዋል።

በሰዎች ሕይወት ውስጥ ድካም፣ መከፋፈል እና ብቸኝነት መኖሩን የሚያመላክቱ ብዙ ምልክቶች መኖራቸውን የተናገሩት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ በማኅበረሰቦች ውስጥ አንዳንድ ጊዜ እምነትን ለሌሎች ማስተላለፍን እና ወጣት ትውልድ እንዳይሳተፍ የሚያደርግ ፈተና ሊያጋጥም እንደሚችል ተናግረው፥ “ቢሆንም ወንጌል ያነቃናል” ሲሉ አፅንዖት ሰጥተዋል።

የጣሊያን ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ
የጣሊያን ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ   (@Vatican Media)

መከሩ ብዙ ነው

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ በማቴ. 9:37 “መከሩ ብዙ ነው፥ ሠራተኞች ግን ጥቂቶች ናቸው” በሚለው ጥቅስ ላይ በማሰላሰል፥ “የመከሩ ጌታ ሠራተኞችን ወደ መከሩ እንዲልክ አጥብቃችሁ ጸልዩ” ሲሉ አሳስበዋል።

እግዚአብሔር ሳይሰለች ዘወትር የማያልቅ የመዳን እና የሙሉ ሕይወት ፍላጎት በሰዎች ልብ ውስጥ ያስቀምጣል” ብለው፥ ለመከሩ ብዛት እግዚአብሔርን ካመሰገኑ በኋላ፥ ተግባራችንም የእርሱን የርኅራሄ እይታ ተቀብለን የራሳችን ማድረግ ነው” ብለዋል።

ስለማያበቅል ጭንጫ መሬት ለማጉረምረም ወይም በአኃዝ ላይ ብቻ ለማትኮር የተፈጠርን አይደለንም” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ ይልቁንም “ከሞት በተነሣው በኢየሱስ ክርስቶስ ዓይኖች ማየትን እንድናውቅ ተጠርተናል” ሲሉ አፅንዖት ሰጥተዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ለጣሊያን ብጹዓን ጳጳሳት ባስተላለፉት መልዕክት፥ “በኢየሱስ ክርስቶስ ቅንዓት የሚቃጠል ልብ መንፈስ ቅዱስ እንዲሰጣቸው እና ብዙ ሠራተኞች አብረዋቸው እንዲሠሩ ጸሎት አቅርበዋል።

ለወንጌል ቅድሚያን መስጠት

“ቅድሚያ የሚሰጠው ለቅዱስ ወንጌል ነው” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ከአሲሲው ቅዱስ ፍራንችስኮስ እስከ ቅዱስ ጳውሎስ 6ኛ፣ እስከ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እና በሁሉም የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ የዘለቀ እንደሆነ ገልጸው፥ “እምነት ከወንጌል የተወለደ፣ ከሞት ከተነሳው ኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ሕያው ግንኙነት ያለው እና በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚገኝ ነው” ሲሉ አስረድተዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በንግግራቸው፥ እንደ ጳጳሳት በዛሬው ዓለም ወንጌልን ማስቀደም በሕይወታችን ውስጥ ከፍተኛ ፍላጎት በመቀስቀስ ወደፊት እንድንጓዝ የሚያደርገን ስጦታ ነው” ብለዋል።

በመሆኑም እነዚህን ሦስት ጥያቄዎች ራሳችንን መጠየቅ አለብን ብለው፥ የመጀመሪያው ጥያቄ፥ በስብከታችን፣ በትምህርተ ክርስቶስ አስተምሮአችን፣ በሥርዓተ አምልኮአችን፣ በበጎ አድራጎት ሥራችን እና በማኅበረሰቦቻችን ሕይወት ውስጥ የትኛው የእግዚአብሔር ፊት እንዲገለጽ እንፈቅዳለን? ሁለተኛው ጥያቄ፥ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር መገናኘትን እንዴት እናበረታታለን? ሦስተኛው ጥያቄ፥ ዛሬ ሌሎችን ወደ ክርስትና ሕይወት መጋበዝ ለእኛ እና ለቤተ ክርስቲያኖቻችን ምን ማለት ነው?” ብለው፥ ሐዋርያዊ እረኞች እነዚህን ጥያቄዎች በቸልታ ሳይመለከቱ ራሳቸውን እንዲጠይቁ አሳስበዋል።

እምነትን ለሌሎች ማስተላለፍ

“ለክርስትና ባሕል አዲስ ትኩረት መስጠት አስፈላጊ ነው” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ ይህም ቅዱሳት ምስጢራትን ለመቀበል ከሚደረግ ዝግጅት በላይ እንደሆነ አስረድተው፥ “ቅዱሳት ምስጢራት የአንድ ማኅበረሰብ እምነት የሚወለድበት እና ሰዎችን የብርሃነ ትንሳኤው ሕይወት ተካፋይዮች የሚያደርግ እና ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ኅብረትን በመፍጠር ወደ ክርስቲያናዊ ወንድማማችነት የሚመራ መንገድ ነው” ብለዋል።

“እምነት ወደ ሌሎች ዘንድ ሊተላለፍ እና ሊያድግ የሚችለው በሕያው እና እንግዳ ተቀባይ ማኅበረሰቦች ውስጥ ነው” ብለው፥ ቅዱስ ቃልን በሚያዳምጡ እና በሚጸልዩ፣ ቅዱስ ቁርባንን የሕይወታቸው ምንጭ አድርገው በሚይዙ፣ ድሆችን እንደ ወንድሞቻቸው እና እህቶቻቸው አድርገው በሚመለከቱ እና ቤተሰቦችን ወደ ጎን በማያደርጉ ማኅበረሰቦች ውስጥ ነው” ብለዋል።

“ብጹዓን ጳጳሳት የእግዚአብሔርን ቃል እና የእግዚአብሔርን ሕዝብ ለማዳመጥ፥ የዘመኑን ምልክቶች በሚገባ ለማወቅ የተጠሩ ናቸው” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ “በማኅበረሰቡ ውስጥ እውነተኛ ማዳመጥ ሲኖር  ያ ማኅበረሰብ ወደ ውስጥ ከማየት ይልቅ ራሱን ለተልዕኮ በማዘጋጀት እንዴት መታደስ እንዳለበት ያውቃል” ብለዋል።

የሲኖዶሳዊነት ጉዞ ትርጉም ይህ እንደሆነ በማስረዳት፥ ሲኖዶሳዊት ቤተ ክርስቲያን እያንዳንዱ ሰው እንደ ጥሪው ከመንፈስ ቅዱስ የተቀበለውን ስጦታ ለጋራ ግንባታ ማቅረብ የሚችልበት ነው” ሲሉ ገልጸው፥ይህም ማለት ተሳትፎ በቤተ ክርስቲያን ሕይወት ምርጫ ያለው ሳይሆን ይልቁንም የኅብረት እና የተልዕኮ መስፈርት በመሆኑ ዘዴ፣ ኃላፊነት እና ተጠያቂነት ሊኖረው ይገባል” ብለዋል።

በአሃዝ ላይ ሊመሠረት አይገባም

እግዚአብሔር የቤተ ክርስቲያንን ፍሬያማነት በአሃዝ፣ በታይታ ወይም በተጽዕኖ ፈጣሪነት እንደማይለካ አፅንዖት ሰጥተው የተናገሩት ቅዱስነታቸው፥ ብጹዓን ጳጳሳቱ አስፈላጊ በሆነው ነገሮች ላይ ብቻ ማተኮር እንዳለባቸው አሳስበዋል።

ትኩረታቸውም በክርስትና ሕይወት ውስጥ ቀጣይነት ባላቸው ጅምሮች እና ዝግጅቶች ላይ መሆን እንዳለበት፥ ቤተሰቦችን በደስታ የሚቀበል እና የሚሰበሰቡበት፣ የወጣቶች ጥያቄ ያለ ገደብ የሚደመጥበት ሚስዮናዊ ቁምስና ማዘጋጀት ሊሆን እንደሚገባ አሳስበዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በመጨረሻም፥ የጣሊያን ብጹዓን ጳጳሳት ጉዞን ለቤተ ክርስቲያን እናት ለሆነችው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በአደራ በመስጠት፥ ሐዋርያው ጳውሎስ ለቆላ. 2:7 ላይ፥ “አብዝታችሁ ምስጋናን በማቅረብ እንደ ተማራችሁት ሥር ሰድዳችሁ በእርሱ ታነጹ፤ በእምነትም ጽኑ” ያለውን በመጥቀስ፥ አስፈላጊ ለሆነው ብቻ ትኩረት እንዲሰጡ፥ እምነትን እንዲያስፋፉ፣ ከእግዚአብሔር ሕዝብ ጋር አብረው እንዲጓዙ እና ሁልጊዜ የሚጠራውን፣ የሚያጽናናውን እና ለአገልግሎት የሚልክውን የጌታን ድምፅ እንዲያቁ በማሳሰብ ንግግራቸውን ደምድመዋል።

 

30 May 2026, 14:21