ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ በቅድስት መንበር የሰው ሠራሽ አስተውሎት ኮሚሽን መቋቋሙን አጸደቁ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
በቅድስት መንበር የሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) ተጓዳኝ ኮሚሽን መቋቋሙን በመግለጽ በጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት የሰው ልጅ ሁለንተናዊ ዕድገት አስተባባሪ ብጹዕ ካርዲናል ሚካኤል ቼርኒ፥ ግንቦት 8/2018 ዓ. ም. የፈረሙበትን የማረጋገጫ ጽሑፍ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ አጽድቀዋል።
“በቅርብ አሥርት ዓመታት ውስጥ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ወይም “አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ” (AI) ፈጣን ዕድገት በማሳየት እና በስፋት ጥቅም ላይ በመዋል በሰው ልጆች እና በአጠቃላይ በሰብዓዊነት ላይ ያለውን ተጽዕኖ ከግምት ውስጥ በማስገባት ቤተ ክርስቲያን ለእያንዳንዱ የሰው ልጅ ባላት ክብር እና አሳቢነት በተለይም ከሁለገብ ዕድገት ጋር በተያያዘ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ኮሚሽን መመሥረቱን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ አጽድቀዋል” ሲል ጽሑፉ ገልጿል።
በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ ዕድገት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት አስተባባሪ ብጹዕ ካርዲናል ሚካኤል ቼርኒ ሚያዝያ 25/2018 ዓ. ም. ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ጋር ከተወያዩ በኋላ ያቋቋሙትን ኮሚሽን ቅዱስነታቸው አጽድቀዋል። የኮሚሽኑን የመጀመሪያ ዓመት ሥራ በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ ዕድገት ጽሕፈት ቤት እንደሚያስተባብረው ታውቋል።
በኅብረት የሚሠሩ በርካታ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤቶች
ኮሚሽኑ የተቋቋመው ከሰባት የቫቲካን ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤቶች በተወጣጡ ተወካዮችን ሲሆን ጽሕፈት ቤቶቹም፥ በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ ዕድገት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት፣ በቅድስት መንበር የእምነት አስተምህሮ ጳጳሳዊ ምክር ቤት፣ በቅድስት መንበር የባሕል እና የትምህርት ጉዳዮች ጳጳሳዊ ምክር ቤት፣ በቅድስት መንበር የመገናኛ ጽሕፈት ቤት፣ በቫቲካን የሥነ ሕይወት ጥናት ጳጳሳዊ አካዳሚ፣ በቫቲካን ጳጳሳዊ የሳይንስ አካዳሚ እና በቫቲካን የማኅበራዊ ሳይንስ አካዳሚ መሆናቸውን ጽሑፉ ገልጿል።
ከእነዚህ ጽሕፈት ቤቶች መካከል አንዱ ኮሚሽኑን ለአንድ ዓመት ጊዜ የማስተባበር ኃላፊነት ሲኖረው፥ ይህም ሊታደስ እንደሚችል እና ቀጣይ ሥራዎችን የሚያስተባብር አካል የሚወስኑት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት መሆናቸው ታውቋል።የአጠቃቀም ፖሊሲዎችን ጨምሮ ከሰው ሠራሽ አስተውሎት ጋር በተያያዙ እንቅስቃሴዎች እና ፕሮጀክቶች መካከል ትብብርን እና የመረጃ ልውውጥን ማመቻቸት የአስተባባሪው ጽሕፈት ቤት ኃላፊነት መሆኑን ጽሑፉ አብራርቷል።
ብጹዕ ካርዲናል ሚካኤል ቼርኒ የኮሚሽኑን አስተባባሪ አካላት ያቋቋሙት “ወንጌልን ስበኩ” በሚለው ሐዋርያት ደንብ አንቀጽ 28 መሠረት ሲሆን፥ በዚህም የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ የበርካታ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤቶች ኃላፊነቶችን የሚመለከቱ የጋራ እና ተከታታይ ምክክር የሚያስፈልጋቸው ጉዳዮችን የሚፈታ ልዩ የጽሕፈት ቤት ኮሚሽን ማቋቋም እንደሚችል ተገልጿል።
የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ቀዳሚ ርዕሥ
ይህም ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤቶች ለመጀመሪያ ጊዜ አንድ ላይ ተሰበሰቡበው ያዋቀሩት ሳይሆን፥ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ጥር ወር 2025 ዓ. ም. የእምነት አስተምህሮ ጳጳሳዊ ምክር ቤት ከባሕል እና ትምህርት ጉዳዮች ጳጳሳዊ ምክር ቤት ጋር በመሆን በሰው ሠራሽ አስተውሎት እና በሰው ልጅ ብልህነት መካከል ያለውን ግንኙነት በማስመልከት “ጥንታዊ እና አዲስ” የተሰኘ ጽሑፍ ማዘጋጀቱ ይታወሳል።
በተጨማሪም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ሰው ሠራሽ አስተውሎት እና ሌሎች የቴክኖሎጂ ዕድገቶች በማኅበረሰባችን ላይ ሊያመጡ የሚችሉ ተግዳሮቶችን ብዙ ጊዜ በተናገሯቸው ርዕሦች ውስጥ ማካተታቸው ይታወሳል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ለሐዋርያዊ መንበር ከተመረጡበት ከጥቂት ቀናት በኋላ ማለትም እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ግንቦት 10/2025 ዓ. ም. ከብጹዓን ካርዲናሎች ጋር ባደረጉት ስብሰባ የሐዋርያዊ ስልጣን ስማቸውን የመረጡት በኢንዱስትሪ አብዮት ወቅት የነበሩት ሁኔታዎችን ምክንያት በማድረግ፥ “አዳዲስ ነገሮች” የሚል ሐዋርያዊ መልዕክት ከጻፉት ከርዕሠ ጳጳሳት ሊዮ 13ኛ እንደሆነ አስረድተዋል።
ቅዱስነታቸው ከዚህም ጋር፥ “በዘመናችን ውስጥ ቤተ ክርስቲያን በሰው ልጅ ክብር፣ በፍትህ እና በሥራ ዋስትና ላይ ሌላ የኢንዱስትሪ አብዮት በሚያስነሳ እና አዳዲስ ተግዳሮቶችን በሚፈጥር የሰው ሠራሽ አስተውሎት መስክ ለሁሉም ሰው የሚያገለግል በቤተ ክርስቲያን ማኅበራዊ አስተምህሮ ላይ የተመሠረተ ምላሽ ትሰጣለች” ብለዋል።
