ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ክርስቲያኖች እና ሙስሊሞች ሰብዓዊነትን እንዲያበረታቱ አሳስቡ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ሰኞ ግንቦት 3/2018 ዓ. ም. ከዮርዳኖስ ንጉሣዊ የሃይማኖቶች ተቋም አባላት እና ከቅድስት መንበር የሃይማኖት ተቋማት የጋራ ውይይት አስተባባሪ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት አባላት ጋር በቫቲካን ተገናኝተዋል።
በዮርዳኖስ ልዑል ሐሰን ቢን ታላል ድጋፍ የተመሠረተው የንጉሣዊ ተቋም አባላት፥ “የሰው ልጅ ርህራሄ እና መረዳዳት በዘመናዊው ዓለም” በሚል ርዕሥ በሮም በተዘጋጀው የሃይማኖቶች የጋራ ውይይት ላይ ተካፋይ ሆነዋል።
ርህራሄ በክርስትና እና በእስልምና እምነት ውስጥ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ርህራሄ እና መተሳሰብ ለክርስትና እምነትም ሆነ ለእስልምና እምነት አስፈላጊ አመለካከቶች እንደሆኑ ጠቁመው፥ በእስልምና ባሕል ርህራሄ (ራፋ) እግዚአብሔር በአማኞች ልብ የሚያስቀምጠው ስጦታ እንደሆነ እና አል-ራኡፍ (ሁልጊዜም ርህሩህ) የሚለው በዘጠና ዘጠኙ መለኮታዊ ስሞች ውስጥ መካተቱን በመግለጽ፥ ይህም ርህራሄ ዘወትር ከእግዚአብሔር ዘንድ የሚመጣ መሆኑን እንደሚያስታውስ ተናግረዋል።
በሌላ በኩልም መለኮታዊ ርኅራኄ በኢየሱስ ክርስቶስ ስብዕና ውስጥ በተባጭ የሚታይ እና የሚዳሰስ መሆኑን ተናግረው፥ እግዚአብሔር ሥጋን በመልበስ የሰውን ሥቃይ ከማየት እና ከመስማት አልፎ በመለማመድ ይበልጥ የርኅራኄ ሕያው ምሳሌ መሆኑን ቅዱስነታቸው አስረድተዋል።
ድሆችን ማፍቀር
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ “ርኅራኄ እና መረዳዳት ለክርስቲያኖችም ሆነ ለሙስሊሞች ተጨማሪ ወይም አማራጭ ነገር ሳይሆን በእርግጥ በሁለቱም ሃይማኖቶች ውስጥ ላሉ አማኞች ማኅበራዊ አንድምታ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
ከክርስቲያን እይታ አንጻር ድሆችን ማፍቀር እንዲሁም መከራቸውን መካፈል አስፈላጊ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸው፥ በዚህ ረገድ የዮርዳኖስ መንግሥት ስደተኞችን በመቀበል ላሳየው ለጋስነት አድናቆታቸውን ገልጸዋል።
ቴክኖሎጂ እና ግድየለሽነት
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በንግግራቸው ማጠቃለያ፥ ቴክኖሎጂ በርኅራኄ እና በመተሳሰብ ላይ ያለውን ተጽዕኖን በማስታወስ፥ “ዛሬ በቴክኖሎጂ እገዛ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ እርስ በርስ ለመገናኘት መቻላችን እውነት ቢሆንም፥ የሰዎችን መከራ የሚያሳዩ ምስሎችን እና የቪዲዮ ቅንብሮችን በተከታታይ መመልከት ልባችንን ከመቀስቀስ ይልቅ ሊያደክመው ይችላል” ሲሉ አስረድተዋል።
የነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን የአንድ ወቅት ቃለ-ምዕዳን በመጥቀስ እንደተናገሩት፥ “የሌሎች መከራ እንደማነካን፣ እንደማይመለከተን ወይም ጉዳያችን እንዳልሆነ በማመን በማኅበራዊ ሚዲያዎች አማካይነት ስቃያቸውን ዘወትር መመልከት ለምደናል” ብለዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ “በዚህ አውድ ውስጥ ክርስቲያኖች እና ሙስሊሞች በጋራ ተልዕኮ ውስጥ ለመሳተፍ የሚያስችላቸውን የየራሳቸውን ወጎች እና እሴቶች እንዲጠቀሙ ተጠርተዋል” ብለው፥ ሰብዓዊነት በቀዘቀዘበት ቦታ ማደስ እንደሚገባ፣ ለሚሰቃዩት ድምጽ መስጠት እና ግድ የለሽነትን ወደ አንድነት መለወጥ ይገባል” ሲሉ አሳስበዋል።
