ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ፥ ሥነ-ጽሑፍ የወንድማማችነት እና የሰላም ትምህርት ቤት ሊሆን ይገባል ሲሉ አሳሰቡ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
“የእያንዳንዱን ሰው ክብር ለሚቀበል በተለይም እጅግ ተጋላጭ ለሆነው፥ ከጊዜ ወደ ጊዜ የወንድማማችነት እና የሰላም ትምህርት ቤት የሚሆን ሥነ ጽሑፍ ያስፈልጋል” ብለዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ይህንን መልዕክት ያስተላለፉት በጣሊያን ቱሪን ከተማ ከግንቦት 6-10/2018 ዓ. ም. ድረስ ለሚካሄደው ዓለም አቀፍ የመጽሐፍ ትርኢት ባስተላለፉት የቴሌግራም መልዕክት እንደሆነ ታውቋል።
በቅዱስነታቸው ስም መልዕክቱን ለቱሪን ከተማ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ ካርዲናል ሮቤርቶ ሬፖሌ ያስተላለፉት የቅድስት መንበር ዋና ጽሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፒትሮ ፓሮሊን ሲሆኑ፥ ሐሙስ ጠዋት በዝግጅቱ የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓት ላይ ለዓለም አቀፍ ትርኢቱ ተሳታፊዎች በንባብ ያቀረቡት ብጹዕ ካርዲናል ሮቤርቶ መሆናቸው ታውቋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በመልዕክታቸው፥ “የደራሲ ኤልሳ ሞራንቴ ሥራን የሚጠቅስ እና ‘በልጆች የዳነው ዓለም’ የሚል ጭብጥ ያለው የዚህ ዙር ርዕሥ አስፈላጊ እና ወቅታዊ ነው” ሲሉ ገልጸውታል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ በአስፈሪ ጦርነት እና በግዴለሽነት በተጨናነቀ ዓለም ውስጥ ልጆች ዓለምን በአዲስ ዓይን የማየት ተፈጥሯዊ ችሎታቸው በኅብረተሰቡ ውስጥ የተስፋ ብርሃን ያበራሉ” ሲሉ አስረድተዋል።
ቅዱስነታቸው በመልዕክታቸው መደምደሚያ፥ “ዝግጅቱ ውይይትን እና ስምምነትን በማጎልበት የባሕልን አስፈላጊነት እንደገና እንደሚያውቅ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።
የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የቴሌግራም መልዕክት፥ በዚህ ወር መጀመሪያ በቱሪን ዝግጅት ላይ ለሚሳተፉ የቫቲካን አሳታሚ ድርጅት ተወካዮች ያስተላለፉትን ቃላት እንደሚያስተጋባ ታውቋል።
ቅዱስነታቸው በዚህ አጋጣሚ፥ ንባብ አእምሮን የሚያበለጽግ፣ ንቃተ ህሊና ያለው እና በሚገባ የተቀረጸ ወሳኝ ስሜትን ለማዳበር እንደሚረዳ ተናግረው፥ በተጨማሪም ዝግ አስተሳሰብን ለመከላከል እና ግትር አመለካከቶችን ለማስወገድ እንዲቻል ሁሉም ሰው መጽሐፍትን እንዲያነብ አሳስበዋል።
