ፈልግ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ሰላምን ለመገንባት ወደሚያግዝ ወደ መንፈስ ቅዱስ ዘንድ ጸሎት አቀረቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ የላቲን ሥርዓት በምትከተል ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ዘንድ በዓለ ኃምሳ በተከበረበት እሑድ ግንቦት 16/2018 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡት ምዕመናን ቃለ-ምዕዳን አሰምተዋል። ከምዕመናኑ ጋር ሆነው ወደ እመቤታችን ማርያም የሰማይ ንግሥት ጸሎትንም አድርሰዋል። በዕለቱ በተከበረ የጴንጤቆስጤ ወይም በዓለ ኃምሳን በማስመልከት ለምዕመናኑ ባሰሙት ቃለ ምዕዳን፥ ሰዎች የእምነት በር ከፋች ወደ ሆነው እና ሁሉንም በቤቷ ውስጥ በደስታ እንድምትቀበል ቤተ ክርስቲያንን ወደሚያበረታታ መንፈስ ቅዱስ ዘንድ ጸሎታቸውን እንዲያቀርቡ አሳስበው፥ መንፈስ ቅዱስ ራስ ወዳድነትን፣ አለመተማመንን እና ጭፍን ጥላቻን በማሸነፍ ወንድማማችነትን እንዲያሳድግ ጸሎታቸውን አቅርበዋል።

ክቡራት እና ክቡራን የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች፥ ከዚህ ቀጥሎ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ለምዕመናን ያሰሙትን ቃለ-ምዕዳን ትርጉም ሙሉ ይዘቱን እንደሚከተለው እናቀርብላችኋለን፥

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“ውድ ወንድሞቼ እህቶቼ፥ መልካም ዕለተ ሰንበት ይሁንላችሁ! በዚህ በጴንጤቆስጤ በዓል፥ በጥንት ዘመን ቤተ ክርስቲያን ላይ በብዛት የፈሰሰውን እና ዛሬ ለአባሎቿ አዲስ ስለሚሰጥ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ እንድናስብ ተጋብዘናል። ይኸው መንፈስ ቅዱስ በዕለት ተዕለት ሕይወታችን ውስጥ ብርሃንና ጥንካሬን ይሰጠናል።

የዛሬው የአምልኮ ሥርዓት በሚያቀርብልን የመንፈስ ቅዱስ ምስል ላይ እናሰላስል። መንፈስ ቅዱስ የእምነት በሮችን ይከፍታል። ቅዱስ ወንጌል እንደሚነግረን፥ ‘በመሸ ጊዜ፥ ደቀ መዛሙርቱ ተሰብስበው በነበሩበት፥ አይሁድን ስለ ፈሩ ደጆቹ ተዘግተው ሳሉ፥ ኢየሱስ መጣ፤ በመካከላቸውም ቆሞ፥ ሰላም ለእናንተ ይሁን አላቸው’ (ዮሐ. 20፡19)። እንደዚሁም፥ ‘ድንገት እንደሚነጥቅ ዓውሎ ነፋስ ከሰማይ ድምፅ መጣ፥ ተቀምጠው የነበሩበትንም ቤት ሁሉ ሞላው’ (ሐዋ. 2፡2)። እነዚያን በሮች በመክፈት ደቀ መዛሙርቱ ወጥተው ከሞት ስለተነሳው ኢየሱስ ክርስቶስ የምሥራችን እንዲያውጁ አነሳሳቸው።

ዛሬ መንፈስ ቅዱስ የሚከፍታቸው በሮች የትኞቹ ናቸው? ብለን ራሳችንን ልንጠይቅ እንችላለን።

የመጀመሪያው በር የእግዚአብሔር ነው። ምክንያቱም መንፈስ ቅዱስ በኢየሱስ ክርስቶስ እንደተገለጠው የእግዚአብሔርን ምስጢር እንድንረዳ ያስችለናል። እግዚአብሔር ለእኛ የመንፈስ ቅዱስን ስጦታ በመስጠት እውነተኛ እምነትን ይሰጠናል። የቅዱሳት መጻሕፍት ትርጉም እንድንረዳ ያግዘናል፤ ራሱን ባልንጀራችን አድርጎ የሕይወቱ ተካፋዮች ያደርገናል። መንፈስ ቅዱስ የእግዚአብሔርን የግል ተሞክሮ እንድናገኝ ያግዘናል፣ ሕግን በመጠበቅ ብቻ ሳይሆን በውስጣችን እሱን እንድናውቅ እና በዕለት ተዕለት ሕይወታችን ውስጥ የእርሱን መኖር የሚገልጹ ምልክቶችን እንድናገኝ ይረዳናል።

ሁለተኛው በር የቤተ ክርስቲያን በር ነው። የመንፈስ ቅዱስ እሳት ከሌለ ቤተ ክርስቲያን የፍርሃት እስረኛ ተሆናለች። የዓለም ፈተናዎችን የምትፈራ፣ በራሷ ተዘግታ በመቆየቷ ምክንያት ከጊዜ ወደ ጊዜ ከሚለዋወጥ ዓለም ጋር ወደ ውይይት መግባት አትችልም። መንፈስ ቅዱስ የቤተ ክርስቲያንን በሮች ይከፍታል። ይህም በእግዚአብሔር እና በጎረቤቶቻቸው ላይ በሮቻቸውን ለዘጉ፣ በተስፋ እና በመኖር ደስታ ላይ ለሚገኙት ሰዎች በሙሉ ክፍት እንድትሆን ያስችላታል። ነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ጥቅምት 4/2023 ዓ. ም. ለጳጳሳት ሲኖዶስ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር፥ ‘የምትባርክ እና የምታበረታታ፣ በሮቿን ለሁሉም ሰው ክፍት ያደረገች ቤተ ክርስቲያን እንድንሆን ተጠርተናል’ ሲሉ አስታውሰዋል።

በመጨረሻም መንፈስ ቅዱስ ተቃውሞን፣ ራስ ወዳድነትን፣ አለመተማመንን እና ጭፍን ጥላቻን እንድናሸንፍ በመርዳት የልባችንን በር ይከፍታል። እንዲሁም እንደ እግዚአብሔር ልጆች እንደ ወንድማማቾች እና እህትማማቾስ እንድንኖር ያስችለናል። የእግዚአብሔር መንፈስ በሚገኝበት በግለሰቦች፣ በቡድኖች እና በሕዝቦች መካከል ወንድማማችነት ይወለዳል። ልዩነቶች ቢኖሩም እንኳ ሁሉን አንድ የሚያደርግ ተመሳሳይ የፍቅር ቋንቋ እንዲናገሩ ያስችላቸዋል።

ወንድሞች እና እህቶች ሆይ! በእኛ ዘመንም ቢሆን በተለይም በዚህ የጴንጤቆስጤ በዓል ዕለት መንፈስ ቅዱስን መጥራት እና የተዘጉትን በሮች ሁሉ እንዲከፍት መጠየቅ አለብን። እግዚአብሔር እንደሚወደን እንደገና ማወቅ አለብን። ስለዚህም ሁሉም ሰው እንደ ቤቱ አድርጎ የሚያያትን ቤተ ክርስቲያን መመሥረት እና በሁሉም ሕዝቦች መካከል ሰላም የሚነግሥበት የወንድማማችነት ዓለም መገንባት እንችላለን።

እንደ መጀመሪያዎቹ ደቀ መዛሙርት የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ እና የቤተ ክርስቲያን እናት ለሆነች ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት አደራ እራሳችንን እንሰጣለን።”

 

 

25 May 2026, 16:34