ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ፥ “የኢየሱስ ዕርገት ወደ አብ የሚወስደን፣ ኅብረትን እና ሰላምን የሚገነባ ነው" ሲሉ ገለጹ
ክቡራት እና ክቡራን የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች፥ ከዚህ ቀጥሎ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ለምዕመናን ያሰሙትን ቃለ-ምዕዳን ትርጉም ሙሉ ይዘቱን እንደሚከተለው እናቀርብላችኋለን፥
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
“ውድ ወንድሞቼ እህቶቼ፥ መልካም ዕለተ ሰንበት ይሁንላችሁ! በዓለም ዙሪያ በሚገኙ በርካታ አገራት ውስጥ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የዕርገት በዓል ዛሬ ይከበራል። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚለው፥ የኢየሱስ ክርስቶስ ምስል ከምድር ተነስቶ ወደ ሰማይ ሲያርግ ተየ። “...ይህንም ከተናገረ በኋላ እነርሱ እያዩት ከፍ ከፍ አለ፤ ደመናም ከዐይናቸው ሰውራ ተቀበለችው...” (ሐዋ. 1:9) ይህም ከረጅም ጊዜ በፊት የተከሰተ ምስጢር መሆኑን እንድናስብ ሊያደርገን ይችላል። ነገር ግን እንደዚህ አይደለም። ምክንያቱም የአንድ አካል ክፍሎች ከራስ ጋር እንደተሳሰሩ ሁሉ እኛም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር አንድ ነን። ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ሰማይ በወጣ ጊዜ ከአብ ጋር ሙሉ ኅብረት እንዲኖረን እኛን ከራሱ ጋር ወደ አብ ዘንድ ይወስደናል። ይህን በማስመልከት ቅዱስ አጎስጢኖስ፥ “የመሪ መቅደም የአባላት ሁሉ ተስፋ ነው” ብሎ ተናግሯል (ስብከት 265፣ 1.2)።
በእርግጥም የኢየሱስ ክርስቶስ ሕይወት በሙሉ የዕርገት እንቅስቃሴ ነው። በሰብዓዊነቱ አማካኝነት መላውን ዓለም አቅፎ በማሳተፍ፣ የሰው ልጆችን ከኃጢአት አውጥቶ ከፍ በማድረግ ይዋጃቸዋል። ቀደም ሲል ከነበሩበት የጨለማ፣ የኢ-ፍትሃዊነት እና ተስፋ የመቁረጥ ሕይወት ፍጹም በሆነው የትንሳኤው ድል ብርሃንን፣ ይቅርታን እና ተስፋን እንዲያገኙ ያደጋቸዋል። በዚህም የእግዚአብሔር ልጅ በመሞቱ ‘ሞታችንን በትንሳኤው ወደ ሕይወት መልሶታል’ (የፋሲካ መቅድም ፩)።
ስለዚህ የኢየሱስ ክርስቶስ ዕርገት ከረጅም ጊዜ በፊት ስለተገባልን ቃል ኪዳን የሚነግረን ሳይሆን፥ ወደ ሰማያዊ ክብሩ የሚወስደን ሕያው ትስስር ነው። በዚህ ሕይወት ውስጥ አድማሳችንን ከፍ የሚያደርግ እና የሚያሰፋ እንዲሁም የአስተሳሰብ፣ የስሜት እና የድርጊት መንገዳችንን ከእግዚአብሔር ልብ ጋር አንድ በማድረግ በቅርበት ይመራል።
ከዚህም በላይ በዚህ የዕርገት ጉዞ ወደ አብ ዘንድ የሚወስድ መንገድ መኖሩን እንገነዘባለን። ‘...የምሄድበትንም መንገድ ታውቃላችሁ...’ ብሏል (ዮሐ. 14:1-6)። በእርግጥም ይህን መንገድ የምናገኘው በኢየሱስ ክርስቶስ ውስጥ ነው። በሕይወቱ ስጦታ ነው፤ በአርአያነቱ እና በትምህርቶቹ ነው። እንዲሁም ቤተ ክርስቲያን የአርአያነት ምልክት አድርጋ በምታቀርባቸው፥ በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እና በቅዱሳን በኩል ማግኘት እንችላለን። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ በዕለታዊ ሕይወታችን አብረውን ስለሚኖሩ አባቶች፣ እናቶች፣ አያቶች፣ በሁሉም የዕድሜ ክልል እና ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ሰዎች፣ ቅዱስ ወንጌልን በደስታ እና በቅንነት ለመኖር ጥረት ስለሚያደርጉ ሰዎች (‘ደስ ይበላችሁ፤ ሐሴት አድርጉ’ ሐዋርያዊ ምክር ቁ.7) መናገር ይወዱ ነበር።
ለድጋፋቸው እና ለጸሎታቸው ምስጋና ይግባውና ከእነርሱ ጋር እኛም በየቀኑ ወደ ሰማይ ማረግን መማር እንችላለን። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዳለው፥ ‘በቀረውስ ወንድሞች ሆይ! እውነተኛ የሆነውን ነገር ሁሉ፥ ክቡር የሆነውን ነገር ሁሉ፥ ጽድቅ የሆነውን ነገር ሁሉ፥ ንጹሕ የሆነውን ነገር ሁሉ፥ ፍቅር ያለበትን ነገር ሁሉ፥ ምስጉን የሆነውን ነገር ሁሉ፥ በጎነት ቢሆን ምስጋናም ቢሆን፥ እነዚህን አስቡ’ (ፊልጵ. 4:8)። ከእኔ የተማራችሁትን እና የተቀበላችሁትን የሰማችሁትንም ያያችሁትንም ሁሉ አድርጉ፤ የሰላምም አምላክ ከእናንተ ጋር ይሆናል (ፊልጵ. 4:9)። በዚህ መንገድ በጥምቀት የተቀበልነው መለኮታዊ ሕይወት ሳያቋረጥ ወደ ከፍታ፣ ወደ አብ ዘንድ ሊወደን፣ በእኛ እና በዙሪያችን ሊያድግ፣ በዓለም ውስጥ የኅብረት እና የሰላም ፍሬዎችን ሊያሰራጭ ይችላል።
ለመንገዳች ብርሃን ሆና የምትመራን የሰማይ ንግሥት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዘወትር በጉዞአችን ትደግፈን።” በማለት ቃለ-ምዕዳናቸውን ደምድመዋል።
