ፈልግ

2022.10.20 Donne, donna

ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14፥ ማኅበራዊ ግንኙነት የሰውን ልጅ እውነት ማክበር እንደሚገባ አሳሰቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን 60ኛውን ዓለም አቀፍ የማኅበራዊ መገናኛ ቀን በምታከብርበት ግንቦት 9/2018 ዓ. ም. የቴክኖሎጂ ፈጠራ ወደ ሰው ልጅ እውነት እንዲጓዝ ካቶሊካዊ ምዕመናን እንዲያግዙ አሳስበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከተሰበሰቡት ምዕመናን ጋር “የእመቤታችን ማርያም የሰማይ ንግሥት” ጸሎት ባደረሱበት ወቅት ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን 60ኛውን ዓለም አቀፍ የማኅበራዊ መገናኛ ቀን እሁድ ግንቦት 9/2018 ዓ. ም. ማክበሯን አስታውሰዋል።

በዕለቱ የተከበረውን ዓለም አቀፍ የመገናኛ ቀን አስመልክተው ባደረጉት ንግግር፥ “ሁሉም ሰው የሰውን ልጅ እውነት የሚያከብሩ የመገናኛ ዓይነቶችን ማስተዋወቅ ይገባል” ሲሉ አሳስበዋል።

በቅርብ ዓመታት ውስጥ የመገናኛ ቴክኖሎጂ ከፍተኛ ዕድገት ማሳየቱን የተናገሩት ቅዱስነታቸው፥ የቴክኖሎጂ ፈጠራ ለሰው ልጅ ጥቅም እንዲውል ጥሪ አቅርበው፥ እያንዳንዱ ሰው የሰውን ልጅ እውነት የሚያከብሩ የመገናኛ ዓይነቶችን ለማስተዋወቅ ራሱን እንዲያዘጋጅ አሳስበው የቴክኖሎጂ ፈጠራ ወደዚያ መምራት እንዳለበት ተናግረዋል።

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የ60ኛው ዓለም አቀፍ የመገናኛ ቀን መልዕክት

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ “የሰውን ድምጽ እና ፊት መጠበቅ” በሚል ጭብጥ ላይ ያተኮረ 60ኛውን ዓለም አቀፍ የማኅበራዊ መገናኛ ቀን መልዕክታቸውን ጥር 16/2018 ዓ. ም. ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በዚህ መልዕክታቸው፥ “እግዚአብሔር የሰውን ልጆች በመልኩ እና በአምሳሉ የፈጠራቸው በመሆኑ፥ የሰው ልጆች መልኮች እና ድምጾች ቅዱስ ናቸው” ሲሉ አስረድተው፥ "እያንዳንዳችን ከራሳችን የሕይወት ተሞክሮ የሚመነጭ እና ከሌሎች ሰዎች ጋር በመገናኘት የሚገለጥ የማይተካ እና የማይስተካከል ጥሪ አለን” ብለዋል።

ሆኖም ግን አዳዲስ የዲጂታል ቴክኖሎጂዎች፥ ድምጾችን፣ ፊቶችን እና ስሜቶችን በማስመሰል ልዩነታችንን አደጋ ላይ ይጥላሉ ብለዋል።

የዲጂታል ቴክኖሎጂዎች የሰውን ድምጽ፣ መልክ፣ ጥበብ እና እውቀት፣ ንቃተ ህሊና እና ኃላፊነት፣ ርኅራኄ እና ወዳጅነትን በማስመሰል ልዩነታችንን አደጋ ላይ እንደሚጥሉ በማስረዳት፥ “ሰው ሠራሽ ወይም “አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ” በመባል የሚታወቁ ሥርዓቶች በመረጃ ሥርዓቶች ላይ ጣልቃ ከመግባታቸውም በላይ የሰው ልጅ ግንኙነቶችን በጥልቀት በመረዳት ላይ ተጽዕኖ ያሳድራሉ” ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በመልዕክታቸው፥ “የሰው ልጅ እውነተኛ ስጋት የማዳመጥ እና የማሰብ ችሎታውን ለሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) እና ለማኅበራዊ ሚዲያ ስልተ ቀመሮች ለመተው ፈቃደኛ መሆኑ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

“ሁልጊዜ ከእኛ የተለዩ ከሆኑት ሌሎች ሰዎች ጋር መገናኘት እና መግባባት የምንችልባቸውን መንገዶች እንዲሁም ከእነርሱ ጋር የግድ መዛመድን መማር የምንችልበትን ዕድል ተነፍገናል” ብለው፥ “ከሌሎች ጋር መሆን ካልቻልን ምንም ዓይነት ግንኙነት ወይም ወዳጅነት ሊኖር አይችልም” ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ለዚህ ችግር ምላሹ፥ “ሰዎች በሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) አጠቃቀም እና በእርስ በርስ ባለን ግንኙነት ላይ ኃላፊነት፣ ትብብር እና ዕውቀት ሊኖራቸው ይገባል” ሲሉ አሳስበዋል።

“የዲጂታል አብዮት ዲጂታል ዕውቀትን ይጠይቃል” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ “ከማኅበረሰብ እና ከባሕላዊ ትምህርት ጋር ተዳምሮ ስልተ ቀመሮች እውነታን እንዴት እንደሚቀርጹ፣ በሥራው ዓለም ተጽዕኖን እንዴት እንደሚፈጥሩ፥ በአቀባበል ላይ የተወሰኑ ይዘቶች መኖራቸውን፣ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ኢኮኖሚያዊ መርሆዎች እና ሞዴሎች ምን እንደሆኑ እና እንዴት ሊለወጡ እንደሚችሉ ለመረዳት ዕውቀት ሊኖር ይገባል” ብለዋል።

“ለሰዎች መልሰን ለመናገር ፊቶች እና ድምጾች ያስፈልጉናል” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ሁሉም የቴክኖሎጂ ፈጠራዎች የመግባባት ስጦታን እንደ ጥልቅ የሰው ልጅ እውነት አድርገው ሊመለከቱት እና ሊያተኩሩበት ይገባል” ሲሉ መልዕክታቸውን ደምድመዋል።

18 May 2026, 16:22