ፈልግ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ሊባኖስን ጨምሮ በመካከለኛው ምሥራቅ ሰላም እንዲሰፍን ጸሎት አቀረቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ረቡዕ ግንቦት 12/2018 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡት ታዳሚዎች ሳምንታዊውን የጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ክፍል ባቀረቡበት ወቅት የአርሜኒያ ቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ መሪ ለሆኑት ብጹዕ ወቅዱስ አራም ቀዳማዊ ሰላምታ አቅርበው፥ ሊባኖስን ጨምሮ በመካከለኛው ምሥራቅ አገራት ሰላም እንዲሰፍን ምዕመናን እንዲጸልዩ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ረቡዕ ግንቦት 12/2018 ዓ. ም. በኪልቂያ መንበር የአርሜኒያ ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ መሪ ለሆኑት ብጹዕ ወቅዱስ አራም ቀዳማዊ ሰላምታቸውን አቅርበዋል።

በቫቲካን በሚገኘው ቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ጋር ተገናኝተው ሰላምታ የተለዋወጡት የአርሜኒያ ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ መሪ ብጹዕ ወቅዱስ አራም ቀዳማዊ ሰኞ ግንቦት 10/2018 ዓ. ም. በቫቲካን ሐዋርያዊ ሕንጻ ውስጥ ተገናኝተው ከቅዱስነታቸው ጋር በኅብረት መጸለያቸው ይታወሳል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በረቡዕ ዕለት የጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ መጀመሪያ ላይ ባደረጉት ንግግር፥ ብጹዕ ወቅዱስ አራም ቀዳማዊን እና ልዑካቸውን በቫቲካን በመቀበላቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው፥ “የወንድማማችነት ጉብኝታቸው ቤተ ክርስቲያኖቻችን ወደ ሙሉ ኅብረት በምትጓዝበት በዚህ ወቅት ቀድሞውኑ በመካከላችን ያለውን የአንድነት ትስስር ለማጠናከር መልካም አጋጣሚ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ወደ መንፈስ ቅዱስ ዘንድ ባቀረቡት ጸሎት፥ ብጹዕ ወቅዱስ አራም ቀዳማዊ ከልዑካናቸው ጋር ወደ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ እና ቅዱስ ጳውሎስ መካነ መቃብር የሚያደርጉትን መንፈሳዊ ንግደት እንዲባርክ ጸልየዋል።

“ይህ መንፈሳዊ ጉብኝታችሁ እና ስብሰባችሁ ወደ ሙሉ አንድነት በሚወስደው መንገድ ላይ ተጨማሪ እርምጃ እንድትወስዱ በቦታው የተገኙት በሙሉ ወደ እግዚአብሔር ዘንድ በብርቱ እንዲጸልዩ እጋብዛለሁ” ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በመቀጠልም፥ በሊባኖስ እና በመካከለኛው ምሥራቅ ሰላም እንዲሰፍን ሁሉም ሰው እንዲጸልይ በማሳሰብ፥ “የዚህ አካባቢው ሕዝቦች በዓመፅ እና በጦርነት እንደገና  ተበታትነዋል” ብለዋል።

የኪልቅያ መንበር አብያተ ቤተ ክርስቲያን ሊባኖስን፣ ሶርያን፣ ቆጵሮስን፣ ኩዌትን፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶችን፣ የባሕረ ሰላጤውን ክልል፣ ኢራንን፣ ግሪክን እና በደቡብ እና በሰሜን አሜሪካ የሚገኙ የአገራቱን ቤተ ክርስቲያናትን እንደሚያካትት ታውቋል። እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከ1930 ዓ. ም. ጀምሮ የኪሊቂያ ታላቋ ቤተ ክርስቲያን ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት የሊባኖስ ከተማ በሆነች አንቴሊያስ እንደሚገኝ ታውቋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ከብጹዕ ወቅዱስ አራም ቀዳማዊ ጋር ሰኞ ግንቦት 10/2018 ዓ. ም. በተገናኑበት ወቅት የሊባኖስን ሕዝብ በዕለታዊ ጸሎታቸው እንደሚያስታውሷቸው እና ለመካከለኛው ምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናትም ያላቸውን አሳቢነት አረጋግጠዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ረቡዕ ግንቦት 12 ባቀረቡት የጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ወቅት፥ ብጹዕ ወቅዱስ አራም ቀዳማዊ ለክርስቲያኖች የአንድነት እንቅስቃሴ በተለይም በካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን እና በምሥራቃዊ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት መካከል በሚደረገው ሥነ-መለኮታዊ ውይይት ባላቸው የማያቋርጥ የግል ቁርጠኝነት አመስግነዋቸዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በንግግራቸው መደምደሚያ፥ “አዕምሮን ወደሚያበራ ቅዱስ ጎርጎርዮስ፣ ወደ ናሬግ ቅዱስ ጎርጎርዮስ፣ ወደ ጸጋው ቅዱስ ነርሴስ እና ከሁሉም በላይ የእግዚአብሔር እናት የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት በአንድነት እንለምን” ብለው፥ ይህም ሁላችን የምንፈልገውን ሙሉ አንድነት እንድናገኝ ያግዘናል” ሲሉ አስረድተዋል።

 

20 May 2026, 16:42