ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ምዕመናን መሪዎች ግልጽነትን እና ኅብረትን ማሳደግ እንደሚገባ አሳሰቡ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ በቅድስት መንበር በሚገኝ የምዕመናን፣ የቤተሰብ እና የሕይወት መምሪያ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት አስተባባሪነት በቤተ ክርስቲያን ማኅበራት ውስጥ በመሪነት ለሚያገለግሉ ምዕመናን ሐሙስ ግንቦት 13/2018 ዓ. ም. በተዘጋጀው ስብሰባ ላይ ተገናኝተው ንግግር አድርገዋል።
በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለሚገኙ የመሪነት ሚናዎች አፅንዖት በመስጠት መለዕክት ያስተላለፉት ቅዱስነታቸው፥ የማንኛውም ማኅበር ወይም እንቅስቃሴ አስተዳደር ለማኅበሩ ስኬት እና ረጅም ዕድሜ ወሳኝ መሆኑን በማስታወስ፥ “አስተዳደር ማለት በማኅበር ውስጥ የሚገኙ ሰዎች የዕድገት ቦታ እንዲሆኑ ለማስቻል እርግጠኛ እና ግልጽ የሆነ አቅጣጫ መስጠት ማለት ነው” ሲሉ አስረድተዋል።
በቤተ ክርስቲያን ውስጥ አመራር ማለት ተግባራዊ ጉዳዮችን ማስተባበር ብቻ ሳይሆን፥ ከሁሉም በላይ በኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር የማዳን ፈቃድ መግለጫ ሆኖ መሥራት ነው” ብለው፥ በምዕመናን ማኅበራት ውስጥ አስተዳደር ማለት ምዕመናን ማኅበረሰብ ለመሪዎቹ ድምጽ በነጻነት የሚሰጡት የአገልግሎት ዓይነት መሆኑን በማስረዳት፥ መሪዎች ይህን የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ መቀበል የሚያስከትለውን ሦስት ውጤቶች ጠቁመዋል።
“በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የማኅበራት አመራር መላውን ምዕመናን የሚጠቅም፣ የግል ጥቅምን የማይፈልግ፣ በግድ የሚያሸክሙት ሳይሆን በውዴታ እና በነፃነት የሚቀበሉት እንደሆነ እና ከጳጳሳት ሐዋርያዊ አስተዋይነት ጋር በመተባበር እና በመታዘዝ የሚከናውኑት ተነሳሽነት ነው” ሲሉ አስረድተዋል።
“በአስተዳደር ውስጥ እነዚህ ባህሪያት መኖር ዘወትር አስፈላጊ ነው” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ የጋራ መደማመጥ፣ ኃላፊነት፣ ግልጽነት፣ ወንድማዊ መቀራረብ እና ማኅበረሰብ ግንዛቤ እንደሆኑ ገልጸው፥ “መልካም አስተዳደር ሁሉንም ነገር በግል ዓይን ብቻ ከመመልከት ይልቅ በመደጋገፍ የማኅበሩ አባላት ሁሉ ኃላፊነት የታከለበት ተሳትፎን የሚያበረታታ ሊሆን እንደሚገባ አስታውሰዋል።
ቅዱስነታቸው በመቀጠልም፥ “በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የምዕመናን መሪዎች ትንቢታዊ ሚና ለአዳዲስ ተግዳሮቶች ምላሽ ለመስጠት እንዲቻል አስቸኳይ ሐዋርያዊ ፍላጎቶች የትኞቹ እንደሆኑ ለይቶ ማወቅን ይጠይቃል” ብለዋል።
“አንድ ማኅበር እውነተኛ እና ፍሬያማ የሚሆነው በአባላቱ መካከል ብቻ ሊከናወኑ በሚገቡ ተግባራት ሳይገደቡ ነገር ግን የጊዜውን ሁኔታ ተረድቶ ወደ ሁሉ ዘንድ በመድረስ፣ የዘመኑን ባህል እና ገና ያልተዳሰሱ የተልዕኮ መስኮችን በመመለከት ነው” ሲሉ አስረድተው፥ እንደዚሁም፥ “በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የምዕመናን ማኅበራት እና እንቅስቃሴዎች እርስ በእርስ እና እንዲሁም ከመላዋ ቤተ ክርስቲያን ጋር ያላቸውን ኅብረት ለመቀበል የተጠሩ ናቸው” ብለዋል።
“እውነተኛ የአገልግሎት ተነሳሽነት ያለው በእኛ ማኅበር ወይም እንቅስቃሴ ነው” የሚሉ አንዳንድ ማኅበራት መኖራቸውን የተናገሩት ቅዱስነታቸው፥ እነዚህ የቤተ ክርስቲያን እንቅስቃሴዎች ከእርሳቸው ሃሳብ ጋር ባይስማሙም ከመላዋ ቤተ ክርስቲያን እና ከአካባቢያቸው ጳጳስ ጋር በኅብረት መኖር እንዳለባቸው በጥብቅ አሳስበዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች የአንድነትን ከፍተኛ ጥቅም ለመጠበቅ ሲሉ የተለያዩ አስተያየቶችን፣ የባህል አውዶችን እና የግል ባህሪያትን ማዳመጥ እንዳለባቸው አሳስበው፥ ምዕመናን መሪዎች እንቅስቃሴዎቻቸው የቆመለትን ዓላማ እና ተነሳሽነት በትሕትና፣ በዋህነት እና ከራስ ወዳድነት ነፃ በሆነ ፍቅር እንዲመሰክሩ አደራ ብለዋል።
ቅዱስነታቸው በመጨረሻም፥ እያንዳንዱ የቤተ ክርስቲያን እውነተኛ ተነሳሽነት በውስጡ ታማኝነትን እና ግልጽነትን እንደሚያካትት ተናግረው፥ የምዕመናን ማኅበራት እና የቤተ ክርስቲያን እንቅስቃሴዎች ሥራን እና ታሪክን በማድነቅ ከመካከላቸው በርካታ ጥሩ የተዘጋጁ እና ውጤታማ ወንጌላውያን መገኘታቸውን አስታውሰው፥ እነዚህ ስጦታዎች በሙሉ በእግዚአብሔር ጸጋ እንዲያድጉ መንከባከብ እና መርዳት እንደሚገባ፥ በዚህ ሂደትም ቤተ ክርስቲያን እንደምትደግፋቸው እና እንደምትከተላቸው በመናገር፥ ለቤተ ክርስቲያን ማኅበራት እና እንቅስቃሴዎች መሪ ምዕመናን ያስተላለፉትን መልዕክት ደምድመዋል።
