የር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ “የሰው ልጅ አስደናቂነት” የተሰኘ የመጀመሪያ መልዕክት ይፋ እንደሚደረግ ተገለጸ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
“የሰው ልጅ አስደናቂነት” የተሰኘ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ሐዋርያዊ መልዕክት ይፋ የሚሆነው ሰኞ ግንቦት 17/2018 ዓ. ም. ሲሆን ይዘቱም በሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) ዘመን ለሰው ልጅ ደኅንነት ቅድሚያ መስጠት በሚለው ላይ ትኩረት እንደሚሰጥ ታውቋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት የፈረሙበት ሐዋርያዊ መልዕክቱ፥ “አዳዲስ ነገሮች” (Rerum novarum) በሚል የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 13ኛ ይፋ ያደረጉት ሐዋርያዊ መልዕክት 135ኛ ዓመት መታሰቢያን እንደሚያስታውስ ታውቋል።
የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ “የሰው ልጅ አስደናቂነት” የተሰኘ ሐዋርያዊ መልዕክት ይፋ የሚሆነው በቫቲካን በሚገኘው የቅዱስ ሲኖዶስ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት አዳራሽ ውስጥ ከረፋዱ አምስት ሰዓት ተኩል ላይ እንደሚሆን ታውቋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በሚገኙበት በዚህ ዝግጅት ላይ ልዩ ልዩ እንግዶች ንግግር የሚያደርጉ ሲሆን እነሱም ብጹዕ ካርዲናል ቪክቶር ማኑዌል ፈርናንዴዝ፥ በቅድስት መንበር የእምነት አስተምህሮ ጳጳሳዊ ምክር ቤት አስተባባሪ፣ ብጹዕ ካርዲናል ሚካኤል ቼርኒ፥ በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ ዕድገት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት አስተባባሪ፣ ፕሮፌሰር አና ሮውላንድስ፥ በዩናይትድ ኪንግደም የዱራም ዩኒቨርሲቲ የሃይማኖት ምሁር፤ ሚስተር ክርስቶፈር ኦላ፥ በሰሜን አሜሪካ የአንትሮፒክ ተባባሪ መሥራች እና የ “አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ” ትርጓሜ ምርምር ኃላፊ፣ እና ፕሮፌሰር ሊዮካዲ ሉሾምቦ፣ አይ.ቲ.፥ በካሊፎርኒያ በሚገኘው ሳንታ ክላራ ዩኒቨርሲቲ የኢየሱሳውያን የሥነ-መለኮት ትምህርት ቤት የፖለቲካዊ ሥነ-መለኮት እና የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ማኅበራዊ አስተምህሮ ፕሮፌሰር እንደሆኑ ታውቋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ንግግር አድርገው ቡራኬ ከሰጡ በኋላ የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን የመዝጊያ ንግግር እንደሚያደርጉ የዕለቱ መርሃ-ግብር ያመለክታል።
