ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ፥ የአምልኮ ሥርዓት ባህል እና ተሃድሶ የወንጌል ስርጭትን እንደሚያበረታቱ ገለጹ
ክቡራት እና ክቡራን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡት ምዕመናን ያቀረቡትን አስተምህሮ ሙሉ ትርጉም ከማቅረባችን በፊት ለዕለቱ የመረጡትን የቅዱስ ወንጌል ክፍል እናነብላችኋለን፥
“በመጽናት እና መጻሕፍት በሚሰጡት መጽናናት ተስፋ ይሆንልን ዘንድ አስቀድሞ የተጻፈው ሁሉ ለትምህርታችን ተጽፎአል። የትዕግሥት እና የመጽናናት አምላክ እንደ ክርስቶስ ኢየሱስ ፈቃድ እርስ በርሳችሁ በአንድ አሳብ መሆንን ይስጣችሁ። ይኸውም በአንድ ልብ ሆናችሁ በአንድ አፍ እግዚአብሔርን፥ እርሱም የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አባት እንድታከብሩ ነው” (ሮሜ 15 4-6)።
ክቡራት እና ክቡራን ከዚህ ቀጥሎ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በዛሬው ዕለት ለምዕመናኑ ያቀረቡትን የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ትርጉም ሙሉ ይዘት እንደሚከተለው እናቀርብላችኋለን፥
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
"ውድ ወንድሞች እና እህቶች ሆይ! እንደምን አደራችሁ! የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፒዮስ 12ኛ፥ ‘በእግዚአብሔር እና በሰው መካከል ያለ አስታራቂ’ (Mediator Dei) በሚለው ሐዋርያዊ መልዕክታቸው እንዲህ ብለው ነበር። “ቤተ ክርስቲያን ያለ ምንም ጥርጥር ሕያው ናት። ሕያው እንደ መሆኗ መጠን አስተምህሮችዋ የተጠበቁላት ከሆነ ጊዜያዊ ፍላጎቶችዋን እና ሁኔታዎችን እያስተናገደች በተቀደሱ የአምልኮ ሥርዓቶችዋ አማካይነት ታድጋለች፣ ትስፋፋለች፣ ትለምዳለችም (ቅዱስ ጉባኤ ደንብ ‘SC’ ቁ. 59)።
ከዚህ መርህ ጋር ሙሉ በሙሉ በሚስማማ መልኩ ሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ ባወጣው ደንብ መግቢያ ላይ፥ “በተለይም አምልኮ ሥርዓትን ለማሻሻል እና ለማስተዋወቅ ጠንካራ ምክንያቶች ሊኖሩ እንደሚገባ ይገነዘባል” (ቁጥር 1)። ጉባኤው የተካሄደበት ምክንያትም የምዕመናን የክርስትና ሕይወት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የሚሄድበትን ኃይል ለመስጠት፣ ሊለወጡ የሚችሉ ተቋማትን ከዘመናችን ፍላጎቶች ጋር በተሻለ ሁኔታ ለማስማማት፣ በኢየሱስ ክርስቶስ በሚያምኑ ሁሉ መካከል አንድነትን ሊያሳድግ የሚችል ማንኛውንም ነገር ለማበረታታት እና መላውን የሰው ልጅ ወደ ቤተ ክርስቲያን ለመጥራት የሚረዳውን ማንኛውንም ነገር ለማጠናከር ነው” (ibid.)።
ጉባኤው በተካሄደበት ወቅት ቤተ ክርስቲያኒቱ ለዘመናት እግዚአብሔርን ያከበረችበት እና ምዕመናኖችዋን የቀደሰችበት የአምልኮ ሥርዓቶችዋን ማደስ አስፈላጊ እንደሆነ ተገንዝባለች። ለሥርዓተ አምልኮ እንቅስቃሴ ምስጋና ይግባውና በኋላ ላይ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ በሐዋርያዊ መልዕክታቸው፥ “በሥርዓተ አምልኮ መታደስ እና በቤተ ክርስቲያን ሕይወት መታደስ መካከል በጣም የቀረበ ትስስር አለ” ያሉት ጎልቶ ወጥቷል። ቤተ ክርስቲያን ሥርዓተ አምልኮን መፈጸም ብቻ ሳይሆን እራሷን በሥርዓተ አምልኮ ትገልጻለች፤ ሥርዓቱን በተጨባጭ ትኖረዋለች፤ እንዲሁም ከሥርዓተ አምልኮ ለሕይወቷ ጥንካሬን ታገኛለች” (Dominicae Cenae, 13)።
በቅዱስ አምልኮ በኩል የሚሰጡ የጸጋ ስጦታዎችን ምእመናን እንዲያገኙ ለማበረታታት የቅዱስ ጉባኤው ደንብ በጣም ውጤታማ በሆነ ጽሑፉ የሚከተለውን መመሪያ አስቀምጧል፥ “ያ ወግ የሚመስለው የአምልኮ ሥርዓት ሊቆይ ይችላል፤ ነገር ግን ሕጋዊ ለሆነ የዕድገት መንገድ ዘወትር ክፍት ሆኖ ይቀጥላል” (ቅዱስ ጉባኤ ደንብ ‘SC’ ቁ. 23)። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤኔዲክቶስ 16ኛ የጉባኤው አባቶች የተሃድሶ ፕሮግራም ዓላማን በሚገባ በመመልከት፥ ባለፈው እና ወደፊት በሚመጣው ታላቅ የአምልኮ ሥርዓት መካከል ሚዛናዊነት መኖሩን ተረድተዋል። “ወግ እና ዕድገት ብዙውን ጊዜ በማይመች ሁኔታ እርስ በርስ ይጻረራሉ” ሲሉ ተናግረው፥ “በእርግጥ ሁለቱ ፅንሰ-ሃሳቦች ይዋሃዳሉ። ወግ ሕያው እውነታ በመሆኑ በውስጡ የዕድገት መርህን ያካትታል። የወግ ‘ወንዝም’ መነሻውን በውስጡ ይዞ ወደ መውጫው ይፈሳል ማለት ነው’ (በቅዱስ አንሴልሞ ጳጳሳዊ ኮሌጅ 50ኛ ዓመት መታሰቢያ ንግግር፥ ግንቦት 6 ቀን 2011፥ እ.አ.አ)።
ጉባኤው የዚህን ዕድገት ሕጋዊነት ያረጋግጣል። ይህም በእውነተኛ ወግ ላይ የተመሠረተ ነው። በአምልኮ ሥርዓት ውስጥ በመለኮት የተቋቋሙ የማይለወጡ አካላት ሊለወጡ ከሚችሉ የአምልኮ ሥርዓት ውስጣዊ ተፈጥሮ ጋር የማይጣጣሙ ወይም ለአምልኮ የማይስማሙ ከሆነ በጊዜ ሂደት ሊለወጡ የሚችሉ ብቻ ሳይሆን ሊለወጡ የሚገቡ ናቸው’ (ቅዱስ ጉባኤ ደንብ ‘SC’ ቁ. 21)። ምእመናን የክርስትና እምነት መሠረት በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ ፋሲካ ምስጢር በአምልኮ ተግባራት ፍሬያማ በሆነ መንገድ እንዲሳተፉ ለማስቻል የዚህ ዓይነት ለውጦች ባለፉት መቶ ዓመታት ውስጥ ያለማቋረጥ ሲከናወኑ ቆይተዋል። በዚህም ምክንያት የቤተ ክርስቲያን አምልኮ በእያንዳንዱ ዘመን ባሕላዊ ቅርጾችን ተላብሶ ቆይቷል። በእነርሱ ላይ ተጽዕኖ ማሳደር እና እንዲያውም መለወጥ ተችሏል። ስለዚህ ሥነ-ሥርዓቱ ለዘመናት ያህል ለወንጌል አገልግሎት ኃይል ሆኖ ቆይቷል። ዛሬ ይህ ኃይል ከእውነተኛው እና ሕያው ከሆነው የካቶሊክ ባህል ጋር ቀጣይነት ባለው መልኩ ምዕመናንን ወደ እውነት ሙላት ለማድረስ በታለመው መሠረት መታደስ አለበት።
ስለዚህ የጉባኤው አባቶች የቤተ ክርስቲያኒቱ ጥቅም በእውነት እና በእርግጠኝነት የሚያስፈልጋቸው በሚሆንበት ጊዜ በአምልኮ ሥርዓት ላይ ማሻሻያ ማድረግ እንደሚገባ የመከሩት ለምን እንደሆነ መረዳት ይቻላል። “ማንኛውም አዲስ ይዘት በአንድ መንገድ ከነባር ይዘት ጋር እንዲያድግ ለማድረግ በጥንቃቄ መከናወን አለበት (ቅዱስ ጉባኤ ደንብ ‘SC’ ቁ. 23)። ለመላው ቤተ ክርስቲያን ጥቅም ሲባል እያንዳንዱ ማሻሻያ ዘወትር ጥንቃቄ በተሞላበት ሥነ-መለኮታዊ፣ ታሪካዊ እና ሐዋርያዊ ምርምር ሊደረግበት ይገባል። ጉባኤው በምእመናን መካከል ሊከሰት የሚችለው ግራ መጋባት በዚህ መንገድ እንዲወገድ ይጠይቃል። ይህ አካሄድ ማንም ሰው በራስ ተነሳሽነት በአምልኮ ጉዳዮች ላይ ማንኛውንም ነገር እንዳይጨምር፣ እንዳያስወግድ ወይም እንዳይቀይር ያደርጋል (ቅዱስ ጉባኤ ደንብ ‘SC’ ቁ. 22)። የጉባኤው አባቶች ባዘጋጁት ደንብ ውስጥ የተገለጸው ዕድገት የቤተ ክርስቲያንን አንድነት በምንም መንገድ አያጎድፍም፤ ይልቁንም ለማረጋገጥ እና ለማሳደግ ይፈልጋል።
ስለዚህ የመለኮታዊ ምስጢራት በዓልን ለማክበር የተጠሩ ሁሉ በተለይም የአምልኮ ሥርዓትን የሚያከናውኑ ካህናት፥ ከውስጣዊ ግልጽነት እና በእግዚአብሔር ላይ ከመታመን የሚመነጨውን የአምልኮ ሥርዓት ጽሑፎችን እና ደንቦችን ሁልጊዜ እንዲያከብሩ፣ የእግዚአብሔርን ታላቅነት በትሕትና ተገንዝበው ለቤተ ክርስቲያን አንድነት ልባዊ ታማኝነታቸውን እንዲያሳዩ አሳስባለሁ።”
