ፈልግ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ መንፈስ ቅዱስ አእምሮን የሚያበራ እና የሚጠብቀን መሆኑን ገለጹ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ የላቲን ሥርዓት በምትከተል ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ዘንድ እሑድ ግንቦት 16/2018 ዓ. ም የተከበረውን በዓለ ኃምሳ ወይም ጴንጤቆስጤ በዓልን ምክንያት በማድረግ ባቀረቡት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ባሰሙት ቃለ ምዕዳን፥ መንፈስ ቅዱስ በሕይወታችን ውስጥ ድንቅ ነገሮችን እንደሚሠራ በማስታወስ፥ አእምሮን በማብራት እና በልባችን ውስጥ አዲስ ኃይልን በመጨመር እና ታሪክን በመለወጥ፥ እግዚአብሔር ለእያንዳንዱ ሰው ያዘጋጀውን የመዳን ስጦታ ይሰጣል” ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“በመንፈስ ቅዱስ ኃይል የወንጌል ምስክርነታችን በደስታ እና በተስፋ በመሙላት እኛ ራሳችን በአዲስ ዓለም የምድር ብርሃን እና ጨው ነን” ሲሉ አስገንዝበዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ይህንን የመጽናኛ ቃለ-ምዕዳን ያሰሙት፥ የላቲን ሥርዓትን በምትከተል ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን እሑድ ግንቦት 16/2018 ዓ. ም በዓለ ኃምሳን ምክንያት በማድረግ በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ ባቀረቡት የመስዋዕት ቅዳሴ ጸሎት ላይ ሲሆን፥ የብርሃነ ትንሳኤው ወቅትም በዚህ በዓል መፈጸሙን አስታውሰዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ከዮሐ. 20: 19-23 ተወስዶ የተነበበው የዕለቱ ቅዱስ ወንጌል ክፍል፥ ሐዋርያት በፍርሃት ተሸንፈው በሮችን መዝጋታቸውን እንደሚያስታውስ ተናግረው፥ በሮች ቢዘጉም ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ እነርሱ መጥቶ በመካከላቸው ቆሞ በደስታ እንደሞላቸው እና “ሰላም ለእናንተ ይሁን” በሚሉት ቃላት ወዲያውኑ በደቀ መዛሙርቱ ላይ መንፈስ ቅዱስን እፍ እንዳለባቸው ተናግረዋል።

መንፈስ ቅዱስ በሐዋርያት ሕይወት ውስጥ ያልተለመደ ነገር እንዳከናወነ አፅንዖት ሰጥተው፥ መንፈስ ቅዱስ ዛሬም ሥራውን እንደቀጠለ አመልክተዋል። የብርሃነ ትንሳኤው በዓል ጴንጤቆስጤ በጸጋው ሁላችንም የምንገኝበት የክርስቶስ አካል በዓል መሆኑን አፅንዖት ሰጥተዋል

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ይህንን ምስጢር ሲያከብሩ በመንፈስ ቅዱስ ሦስት ገጽታዎች ላይ በማትኮር፥ እነርሱም የሰላም መንፈስ፣ የተልዕኮ መንፈስ እና የእውነት መንፈስ መሆናቸውን አስገንዝበዋል።

በልባችን ውስጥ ሰላምን ማፍሰስ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ በመጀመሪያ የሰላም መንፈስ ላይ በማተኮር እንደተናገሩት፥ በክርስቶስ የፋሲካ ምስጢር አማካኝነት በእግዚአብሔር እና በሰው ልጆች መካከል ያለውን ሰላም ገልጸው፥ ይህንን ሰላም በልባችን ውስጥ አፍስሶ በዓለም ዙሪያ ያሰራጨው መንፈስ ቅዱስ መሆኑን አስረድተዋል።

ይህ ሰላም ከይቅርታ የመነጨ እና ወደ ይቅርታ የሚመራን መሆኑን አፅንዖት ሰጥተው፥ ምክንያቱም “እግዚአብሔር ማንንም ሳይለይ ሁሉንም ከሞት ያዳነ በመሆኑ የሰላምን መንፈስ ከአንድ ጫፍ ወደ ሌላው ጫፍ ያፈስሳል” ሲሉ ገልጸዋል።

ሁላችንም እንድንመሰክር ተጋብዘናል

ወደ መንፈስ ቅዱስ የሚስዮናዊነት ገጽታ ተመልሰው ባሰሙት ቃለ-ምዕዳን፥ መንፈስ ቅዱስ በኢየሱስ ክርስቶስ ሕያው ፍቅር የሚሞላን፣ የሚያበረታታን እና በተልዕኳችን የሚደግፈን መሆኑን አስታውሰዋል።

በጴንጤቆስጤ ዕለት ሐዋርያት በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ተሞልተው ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ማወጅ መጀመራቸውን ገልጸው፥ “የመንፈስ ቅዱስ የመጀመሪያ ሥራ በእኛ ውስጥ ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ መሆኑን እንድናውጅ እምነትን መስጠት ነው” ሲሉ አስረድተዋል።

ይህ እምነት በእያንዳንዱ መልካም ተግባር እና በጎነት እንደሚገልጽ ተናግረው፥ ስለዚህም እያንዳንዳችን ወደ ጌታ ማዕድ የተጋበዝን፣ ቃሉን ለማዳመጥ የተሰበሰብን እና በየቦታው ለመመስከር የተጠራን የእግዚአብሔር ሥራ ውጤቶች ነው” ብለዋል።

የወንጌል ተባባሪ መስካሪዎች

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ሁሉም ምዕመናን በእውነት የወንጌል ተባባሪዎች መሆናቸውን አፅንዖት ሰጥተው፥ “ቤተ ክርስቲያንም የዚህ ተልዕኮ ዋና ተዋናይ እንጂ የምዕመናን ጠባቂ ብቻ አይደለችም” ሲሉ ገልጸው፣ “በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ድጋፍ የወንጌል ምስክርነታችን በደስታ እና በተስፋ የተሞላ ነው” ሲሉ አስረድተዋል።

እኛ ራሳችን አዲስ ፍጥረት፣ የምድር ብርሃን እና ጨው እንደሆንን አፅንዖት ሰጥተው፥ “እንዲህ የሆንነው በመብታችን ሳይሆን፥ ኃጢአተኛውን በሚቀድስ፣ ለምጻሙን በሚፈውስ እና የከዳውን ወደ ሐዋርያነት በሚለውጠው በኢየሱስ ክርስቶስ ቃል ምክንያት ነው” ብለዋል።

ለዓለማችን አዲስ ሕይወት የማያመጡ ለውጦች መኖራቸውን የተናገሩት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ነገር ግን ዓለም በስህተት እና በዓመፅ እንዲያረጅ አስተዋጽዖ እንደሚያደርጉ ገልጸው፥ ያም ሆኖ መንፈስ ቅዱስ ግን አእምሮን እንደሚያበራ እና በልባችን ውስጥ አዲስ ሕይወትን የሚፈጥር መሆኑን አስረድተዋል።

እውነትን በመናገር አንድነትን ማበረታታት

መንፈስ ቅዱስ ታሪክን በመለወጥ ለድነት እንደሚያዘጋጅ ገልጸው፥ ይህም እግዚአብሔር ለሁሉ ሰው የሚሰጠው ስጦታ እንደሆነ አስረድተው፥ “የቤተ ክርስቲያን ተልዕኮ ለዚህ ​​ስጦታ ምስክርነት መስጠት ነው” ሲሉ አክለው፥ በዚህም የዓለምን ግራ መጋባት በእግዚአብሔር እና በእኛ መካከል ወዳለው ኅብረት እንደሚለውጠው አስረድተዋል።

በነቢያት አፍ የተነገረው መንፈስ ቅዱስ ዘወትር ኅብረትን በእውቀት፣ በስምምነት እና በሕይወት ውስጥ በማካተት አንድነትን የሚያበረታታ መሆኑን አስታውሰዋል።

ጰራቅሊጦስ ዘወትር የሚጠብቀን የቅድስና ምንጭ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በመጨረሻም፥ ጰራቅሊጦስ ይህንን ግንዛቤ ከሚያደናቅፉ ነገሮች ሁሉ ማለትም የወንጌልን ብርሃን ከሚደብቁ የወገናዊነት እና የግብዝነት አዝማሚያዎች እንደሚጠብቀን አስረድተዋል።

“እግዚአብሔር የሚሰጠን እውነት ሕዝቦችን ነፃ የሚያወጣ ቃል እና እያንዳንዱን ባህል ከውስጥ የሚቀይር መልዕክት ያለው ነው” ብለው፥ መንፈስ ቅዱስ ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ የሚሰጥ ሳይሆን ሳያቋርጥ የሚፈስ ጸጋ እንደሆነ አፅንዖት ሰጥተዋል።

“ሳያቋርጥ የሚመግበን ቅዱስ ቁርባን የኢየሱስ ክርስቶስ ሕያው ሥጋ እንደሆነ ሁሉ እንዲሁም መንፈስ ቅዱስ በጥምቀት የእርሱን ባሕርይ በእኛ ላይ በማሳረፍ ክርስቲያኖች ያደርገናል” ብለው፥ በተመሳሳይም “መንፈስ ቅዱስ በምስጢረ ሜሮን በኩል እኛን ምስክሮቹ በማድረግ በሌሎች ቅዱሳት ምስጢራት ውስጥ የእግዚአብሔር ሕዝብ አገልጋዮች እና እረኞች ያደርገናል” ብለው፥ “መንፈስ ቅዱስ የጸጋ ጦታን በጸሎት፣ በምሕረት ሥራ እና በእግዚአብሔር ቃል በማሳደግ በእያንዳንዱ ቅዱሳት ምስጢራት ውስጥ የቅድስና ምንጭ ነው” ሲሉ አስረድተዋል።

ሐዋርያው ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች በጻፈው የመጀመሪያ መልዕክቱ ምዕ. 12:7 ላይ፥ “ለእያንዳንዱ የመንፈስን መገለጥ የሚሰጠው ለጋራ ጥቅም ነው” ያለውን በማስታወስ፥ “እኛ ቤተ ክርስቲያን የሆንነው በዚህ ምክንያት ነው” ብለው፥ “ለመንፈስ ቅዱስ ምስጋና ይግባውና፥ እንደ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሁሉም ሰው እውነተኛ ሰላም እና መዳን የሚሆን እውነት ማምጣት እንችላለን” ሲሉ ምዕመናንን ጋብዘዋል።

“መንፈስ ቅዱስ ሆይ፥ ከጦርነት ክፋት አድነን!”

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በማጠቃለያ፥ መንፈስ ቅዱስ በሁሉን ቻይ ፍቅሩ የሰውን ልጆች ከመከራ ነፃ እንዲያወጣን እና በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ለሕዝቦች በሙሉ በተሰበከው የመዳን ቃል ከኃጢአት መቅሰፍት እንዲፈውሳቸው ምእመናን እንዲጸልዩ ጋብዘው፥ ዛሬም ሆነ ዘወትር በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት፥ ለሐዋርያት ድፍረት የሰጠው ጸጋ በውስጣችን እንዲያሳድግ መንፈስ ቅዱስን በጸሎት በመጠየቅ ቃለ-ምዕዳናቸውን ደምድመዋል።

25 May 2026, 16:41