ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ የስፔኑን ጠቅላይ ሚኒስትር በቫቲካን ተቀበሉ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ በስፔን ሐዋርያዊ ጉብኝት ከማድረጋቸው ከሁለት ሳምንታት ባነሰ ጊዜ ውስጥ የስፔኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ፔድሮ ሳንቼዝ ፔሬዝ-ካስቴጆን በቫቲካን ተቀብለዋል።
የቅድስት መንበር መግለጫ እንዳስታወቀው፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ረቡዕ ግንቦት 19/2018 ዓ. ም. ከሳምንታዊው የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ በፊት ከጠቅላይ ሚኒስትር ፔድሮ ሳንቼዝ ፔሬዝ-ካስቴጆ ጋር መገናኘታቸውን እና ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኋላም ከቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን እና በቫቲካን የመንግሥታት እና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ግንኙነት ክፍል ዋና ጸሐፊ ከሆንት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ፖል ሪቻርድ ጋላገር ጋርም መገናኘታቸውን ገልጿል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በቅርቡ ወደ ስፔን የሚያደርጉት ጉዞ በማስመልከት ጠቅላይ ሚኒስትር ፔድሮ ሳንቼዝ ፔሬዝ-ካስቴጆ ከቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን ጋር ያደረጓቸው ውይይቶች እርካታን የሰጡ መሆናቸውን በመግለጽ፥ በቅድስት መንበር እና በስፔን መካከል መልካም ግንኙነት መኖሩን የሚያሳይ ምልክት ነው” ሲሉ መግለጫው ገልጿል።
የቅድስት መንበር መግለጫ በተጨማሪም፥ በርካታ ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ትኩረት እንደተሰጠባቸው ገልጹ ከእነዚህም መካከል በዓለም ዙሪያ የሚፈጠሩ ግጭቶች የሚያስከትሉት መዘዝ፣ ስደት፣ የብዙ አገራት ትብብር አስፈላጊነት፣ ዓለም አቀፍ ሕግ ማክበር እና እንዲሁም ለሰላም ለሚሰጥ ድጋፍ የማያቋርጥ ቁርጠኝነት” የሚሉ ይገኙበታል።
ከዚህም በላይ ሁለቱም ወገኖች በስፔን በምትገኝ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን እና በመንግሥት ባለስልጣናት መካከል እንዲሁም በተለያዩ የሲቪል ማኅበረሰብ ክፍሎች መካከል በጋራ መከባበር ላይ የተመሠረተ እና የጋራ ጥቅምን ለማስተዋወቅ የታለመ ፍሬያማ ውይይት የማሳደግ አስፈላጊነት በመሳሰሉ የጋራ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል።
