ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ አዲስ የተሾሙት ሊቃነ ጳጳሳት መልካም እረኞች እንዲሆኑ አሳሰቡ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የሮም ደጋፊዎች የሆኑት የቅዱሳን ጴጥሮስ እና ጳውሎስ ዓመታዊ ክብረ በዓል ምክንያት በማድረግ ሰኞ ሰኔ 22/2018 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ መስዋዕተ ቅዳሴን መርተዋል። በሥነ-ሥርዓቱ ላይ ባሰሙት ቃለ-ምዕዳን፥ “ዛሬ እኛም በተራችን አንድነትን ለማበረታታት እና እውነተኛ ለጋስ አገልጋዮች ለመሆን ቅዱስ ጴጥሮስን እና ቅዱስ ጳውሎስን መመልከት ያስፈልጋል” ሲሉ አሳስበዋል።
ሁለት የቤተ ክርስቲያን "ምሰሶዎች"
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የሮም ሀገረ ስብከት ባልደረባ በሆኑት ቅዱሳን ሕይወት ላይ በማስተንተን ባሰሙት ቃለ-ምዕዳን፥ ሐዋርያው ጴጥሮስ የመንጋው እረኛ ሆኖ እንዲሁም ሐዋርያው ጳውሎስ የአሕዛብ ሐዋርያ ሆኖ በኢየሱስ ክርስቶስ መመረጡን አስታውሰው፥ “በመሆኑም የቤተ ክርስቲያን ምሰሶዎች የሆኑ የሁለት ሐዋርያት በዓልን ዛሬ እናከብራለን” ብለዋል።
የቤተ ክርስቲያን የመጀመሪያው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሐዋርያው ጴጥሮስ በልዩነት እና በሁከት መካከል አንድነትን እና ኅብረትን ያበረታታ እንደ ነበር አስታውሰዋል።
ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ፍጹም አልነበረም
ቅዱስነታቸው ቃለ-ምዕዳናቸውን በመቀጠል፥ “ይሁን እንጂ ይህ ማለት ሐዋርያው ጴጥሮስ ፍጹም ነው ማለት አይደለም” ብለው፥ በሕማማቱ ወቅት ኢየሱስ ክርስቶስን ከካደ በኋላ ከልብ በማልቀስ የንስሐ እንባዎቹን ማፍሰሱን አስታውሰው፥ በተሳሳቱ ድርጊቶቹ በተለያዩ ጊዜያት ሐዋርያው ጳውሎስ እንደ ገሰጸው አስታውሰዋል።
“ጴጥሮስም ስህተቶቹን አምኖ ንስሐ መግባቱን፥ ተስፋ ሳይቆርጥ ወንጌልን ለማወጅ እና የክርስቶስን መንጋ የመሰብሰብ ተልዕኮውን ሳያቋርጥ ከተሰበሰብንበት ቦታ ብዙም ሳይርቅ ሮም ውስጥ በሰማዕትነት ተሰቃይቷል” ብለዋል።
“ሐዋርያው ጴጥሮስ በኢየሱስ ክርስቶስ በተሰጠው ተልዕኮ በመታገዝ የእያንዳንዱን ሰው ድምፅ ማዳመጥ፤ ተነሳሽነቶችን መለየት፣ መምራት፣ ስህተቶችን ማረም፣ ወንድሞችን እና እህቶችን ማስተማር፣ ማበረታታት እና አብረው መጓዝ እንዲችሉ፣ በዚሁ መንፈስ እርስ በርስም ሆነ ለሰው ልጆች ሁሉ በሚያበረክቱት ሥራ በገርነት እንዲተባበሩ መርዳቱን አስታውሰዋል።
የሐዋርያው ጴጥሮስ ምሳሌ እያንዳንዱ ክርስቲያን አንድነትን እንዲገነባ፣ እግዚአብሔርን የሕይወቱ ማዕከል እንዲያደርግ እና ከወንድሞች እና እህቶች ጋር እንዲቀራረብ፥ ለሁኔታዎቻቸው እና ፍላጎቶቻቸው ትኩረት እንዲሰጥ የቀረበ ግብዣ ነው” ብለው፥ “መልዕክቱ ለሌሎች በሙላት እንዲታወጅ እርስ በርሳችን በፍቅር መኖርን እንማራለን” ብለዋል።
እግዚአብሔር የወጣቱን ሳኦል ልብ አሸነፈ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በመቀጠልም፥ “ይህ ትምህርት ዛሬ የምናከብረው የሌላኛው ታላቅ ሐዋርያ እና ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይል የምሥራች ቃል ሰባኪ የነበረ የጳውሎስም ጭምር ነው” ብለው፥ “እግዚአብሔር በወጣቱ ሳኦል ልብ ውስጥ ድንቅ ነገር ፈጽሟል፣ አሸንፎታል፣ በመጀመሪያ በወንጌል ተለውጦ አዲስ ስም እንዲሰጠው ካደረገ በኋላ ወንጌልን በዓለም ዙሪያ እንዲያውጅ ልኮታል” ብለዋል።
“እንደ ሐዋርያው ጴጥሮስ ሐዋርያው ጳውሎስም በሮም ሕይወቱን እስኪሰጥ ድረስ ወንጌልን መስክሯል” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ “የአሕዛብ ሐዋርያ ቅዱስ ጳውሎስ በእግዚአብሔር ቃል ራሱን ለመለወጥ መፍቀዱ ከዓመፅ መንገድ ይልቅ ወደ ፍቅር መንገድ መርቶታል” ብለዋል።
ቅዱስ አጎስጢኖስ ስለ ጳውሎስ መለወጥ እና ተልዕኮው የተናገረውን ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ቤተ ክርስቲያንን ሲያሳድድ የነበረውን እግዚአብሔር የሰላም መልእክተኛ አድርጎታል፤ ኃጢአቱን በሙሉ ይቅር ብሎለት የሌሎችን ኃጢአት ይቅር በሚልበት አገልግሎት ላይ ማስቀመጡን አስታውሰዋል።
የመንጋውን እንዲጠብቁ አደራ የተሰጣቸው አዳዲስ ሊቃነ ጳጳሳት
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ እነዚህን ቅዱሳን መመልከት አንድነትን ማራመድ እና እውነትን በበጎ አድራጎት ማገልገልን ሊያስተምረን እንደሚችል ጠቁመው፥ መንጋውን እንዲጠብቁ አደራ የተሰጣቸው አዳዲስ ሊቃነ ጳጳሳት በዚህ መንፈስ የሊቃነ ጵጵስና ሹመታቸውን ለማክበር መዘጋጀታቸውን አስታውሰዋል።
“በመስቀል ያጌጡ እነዚህ ነጭ አልባሳት በአደራ የተሰጣቸውን እያንዳንዱን የእግዚአብሔር መንጋ በሃላፊነት በመሸከም ጉልበታቸውን፣ ጊዜያቸውን እና ሕይወታቸውንም ጭምር በመስዋዕትነት የመስጠትን ቁርጠኝነትን ያሳያሉ” ብለው፥ “ከራስ ወዳድነት ነጻ የሆነው አገልግሎት ወንጌል ለሁሉም ሰው እንዲደርስ እና መላው ዓለምም ተስማምቶ እንዲኖር የሚል መልዕክት አለው” ሲሉ አስረድተዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በዚህ መንፈስ ከቆስጠንጢንያ ፓትርያርክ ጽሕፈት ቤት ለመጡት የክርስቲያኖች አንድነት እንቅስቃሴ ልዑካን ልባዊ ሰላምታቸውን አቅርበው፥ በመጨረሻም “በጉዟችን ውስጥ የአዳኛችን የኢየሱስ ክርስቶስ ፈለግ ለመከተል የቅዱሳን ጴጥሮስ እና ጳውሎስ ድጋፍ በጸሎት እንጠይቅ” ሲሉ አሳስበዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ይህም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያዘጋጀልን መንገድ እና በመጨረሻው እራት ወደ አባቱ ዘንድ የጸለየው፣ በተስፋ እንድንመኘው ያስተማረን ግብ ነው” ሲሉ ቃለ-ምዕዳናቸውን ደምድመዋል።
