ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ ከካርዲናሎች ጋር የሚያደርጉት ስብሰባ ግልጽነት እና ታማኝነት እንዲኖረው አሳሰቡ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
“ቅን ምክር ዘወትር በኅብረት የሚገለጽ ተግባር ነው” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ “ነፃነታችሁ፣ ግልጽነታችሁ እና ታማኝነታችሁ ያስፈልገኛል” ሲሉ በማከልል ልዩ የካርዲናሎች ስብሰባን ዓርብ ሰኔ 19/2018 ዓ. ም. በይፋ ከፍተዋል።
ከዓለም ዙሪያ የመጡ ካርዲናሎች የሚሳተፉበት ይህ ልዩ ስብሰባ በጳውሎስ 6ኛ አዳራሽ ውስጥ እስከ ቅዳሜ ሰኔ 20 ምሽት ድረስ የሚቆይ እና ካርዲናሎቹ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ጋር ሆነው ለማስተንተን ዕድል እንደሚሰጣቸው ተገልጿል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ እነዚህ ስብሰባዎች የቤተ ክርስቲያንን አገልግሎት ከካርዲናሎች ጋር በጋራ በኅብረት ለመፈጸም እና በተልዕኮ መካከል ሊረዱ የሚችሉ ውይይቶችን ለመቀጠል ያላቸውን ፍላጎት አድሰዋል።
ኅብረት ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ የሚገኝ ሳይሆን ነገር ግን ዕለታዊ መለወጥን፣ ጸሎትን፣ መተማመንን፣ ግንኙነትን እና እርስ በርስ መደማመጥን እንደሚጠይቅ ቅዱስነታቸው አስረድተዋል።
ካርዲናሎች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በሲኖዶሳዊነት ኅብረትን እንዲገነቡ በማለት በቅርብ ወራት ውስጥ ያቀረቡትን ግብዣ አስታውሰው፥ እያንዳንዱ የስብሰባው አባል በግል የቸርነት እና የአገልግሎት ተልዕኮ መሠረት የሚተባበር መሆኑን ተናግረው፥ ካርዲናሎቹ በሁለቱ የስብሰባ ቀናት ውስጥ ትኩረት በሚሰጡባቸው አራት ጭብጦች ላይ አሰላስለዋል።
የመጀመሪያው ክፍለ ጊዜ፥ ቤተ ክርስቲያን ወንጌልን ለማወጅ በተጠራችበት ዓለም ላይ የሚያሰላስል ሲሆን፥ ይህ ዘመኑን ማዕከል ያደረገ ግንዛቤ በዓለም ላይ እና በታሪክ ውስጥ የሚጓዘውን ኢየሱስ ክርስቶስን ለማወቅ የሚረዳቸው መሆኑን ተነግረዋል።
ሁለተኛው ክፍለ ጊዜ፥ ካርዲናሎች የኃይል ባሕል እና የፍቅር ሥልጣኔ አንድምታዎችን የሚመረምሩበት ሲሆን፥ ብዙዎቹ ከጦርነት ቀጣና አገራት የመጡት ቢሆንም ከመካከላቸው ኅብረተሰቦችን በሚያስጨንቁ ግጭቶች፣ የአምባ ገነን ሥርዓቶች እና መከፋፈሎች ያልተጎ አለመኖሩን አስታውሰዋል።
ካርዲናሎች ቤተ ክርስቲያኖቻቸውን ለመረዳት ያግዛቸው ዘንድ፥ “የስዎች አስደናቂነት” የሚለውን ሐዋርያዊ መልዕክት በድጋሚ እንዲመለከቱት ጠይቀዋል።
በሦስተኛው ክፍለ ጊዜ፥ ቤተ ክርስቲያን ለሰው ልጆ የጋራ ጥቅም ምን ዓይነት አስተዋጽኦ ማድረግ እንደምትችል የሚያተኩሩበት እንደሆነ ገልጸዋል።
“የቤተ ክርስቲያን ማኅበራዊ አስተምህሮ በበኩሉ፥ የጋራ ጥቅም በድንገት የሚመጣ ሳይሆን ነገር ግን የጋራ ኃላፊነትን የሚፈልግ መሆኑን ያስታውሰናል” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ “ለቤተ ክርስቲያን ትክክለኛ ቅርፅ የሚሰጥ እና የመንግሥቱን ተልዕኮ ለማገልገል የሚረዳ የሲኖዶሳዊነት ዘይቤን የተከተለ ነው” ሲሉ ገልጸዋል።
በአራተኛው ክፍለ ጊዜ ካርዲናሎች ሲኖዶሳዊነት በቀጣይነት እንዲተገበር በኅብረት የሚያስተነትኑበት ጊዜ እንደሆነ ገልጸዋል።
ቅዱስነታቸው ይህ የመጨረሻ ክፍለ ጊዜ በሲኖዳዊነት ሥር ሆነው የተወያዩባቸውን ሦስት አስተንትኖዎች ማለትም፥ አመለካከትን፣ ግልጽነትን እና ለመረዳት ፈቃደኛ መሆንን ያካተተ መሆኑን ተናግረዋል።
ካርዲናሎች በቤተ ክርስቲያን ውስጣዊ ሕይወት ላይ ከማተኮር ይልቅ መላውን ዓለም እንዲመለከቱ ጋብዘው፥ “ዛሬ ቤተ ክርስቲያኖቻችን ወንጌልን በታላቅ ታማኝነት፣ በነፃነት እና በተዓማኒነት እንዲያውጁ እንዴት መርዳት እንችላለን?” ሲሉ ጠይቀዋል።
የወንጌል ተልዕኮ ለቤተ ክርስቲያን ከብዙ ተግባሮቿ መካከል አንዱ ሳይሆን ህልውናዋ እንደሆነ ጠቁመው፥ በመሆኑም ካርዲናሎች እንዲያዳምጡ፣ ኃላፊነቶቻቸውን እንዲሸከሙ እና በመንፈስ ቅዱስ ሥራዎች ላይ እንዲያሰላስሉበት የሚጠይቅ መሆኑን አስረድተዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በንግግራቸው ማጠቃለያ ላይ ካርዲናሎችን አመስግነው፥ ካርዲናሎቹ መንፈስ ቅዱስ ለቤተ ክርስቲያን በሚናገረው ላይ ለማስተነተን እንደሚያግዙ ያላቸውን እምነት ገልጸው፥ “ጠንካራ እና ግልጽ የወንድማማችነት ድጋፋችሁን እፈልጋለሁ” በማለት ንግግራቸውን ደምድመዋል።
