ፈልግ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ከአህጉራዊ የሲኖዶስ መሪዎች ጋር ሲወያዩ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ከአህጉራዊ የሲኖዶስ መሪዎች ጋር ሲወያዩ   (@VaticanMedia)

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ለአህጉራዊ የሲኖዶስ መሪዎች የማበረታቻ መልዕክት አስተላለፉ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በሲኖዶሳዊነት አተገባበር እና እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 2028 ዓ. ም. ሊካሄድ በታቀደው ጠቅላላ የቤተ ክርስቲያን ጉባኤ ላይ ከተወያዩ መሪዎች ጋር ተገናኝተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በሲኖዶሳዊነት አተገባበር ላይ ለሦስት ቀናት ከተሰበሰቡት አህጉራዊ የሲኖዶስ መሪዎች ጋር ሐሙስ ሰኔ 18/2018 ዓ. ም. በግል ተገናኝተዋል።

ከሰኔ 16-18/2018 ዓ. ም. ​​በተካሄደው ስብሰባ ላይ ከላቲን አሜሪካ፣ ከአፍሪካ፣ ከእስያ፣ ከአውሮፓ፣ ከኦሽንያ፣ ከመካከለኛው ምሥራቅ እና ከሰሜን አሜሪካ የተውጣጡ አህጉራዊ የሲኖዶስ ቡድኖች አስተባባሪዎች ጋር ተገኝተዋል።

የሲኖዶሱ ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ማርዮ ግሬች፥ “ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ጋር የተደረገው ውይይት ለቤተ ክርስቲያኒቱ ሲኖዶሳዊ ለውጥ ጠንካራ የድጋፍ እና የማበረታቻ ምልክት ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

ካርዲናል ማርዮ ግሬች ማክሰኞ ዕለት ስብሰባውን ሲከፍቱ ባደረጉት ንግግር፥ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 2028 ዓ. ም. ወደሚካሄደው የቤተ ክርስቲያን ጠቅላላ ጉባኤ የሚደረገውን ጉዞ አጭር ግምገማ በማቅረብ የሂደቱን ልዩ ባህሪ አስታውሰዋል።

ብጹዕነታቸው በመግለጫው ላይ፥ ምእመናንን በአገራቱ ቤተ ክርስቲያናት ሲኖዶሳዊነ ላይ ለማሳተፍ ቀደም ሲል የተወሰዱት በርካታ ተነሳሽነቶች መኖራቸውን አስታውሰው፥ ከእነዚህም መካከል የሲኖዶሳዊነት ትምህርት ቤቶች፣ የስልጠና ፕሮግራሞች፣ ሲምፖዚየሞች፣ ጉባኤዎች፣ የማዳመጥ እና የማስተዋል ሂደቶች እንደሆኑ አስረድተዋል።

ከካርዲናል ማርዮ ግሬች የሰላምታ ንግግር ቀደም ብሎ የጠቅላይ ሲኖዶሱ ምክትል ጸሐፊ እህት ናታሊ ቤክኳርት የስብሰባውን ተካፋዮች በጸሎት መርተዋል።

የማዳመጥ እና የማስተዋል ሂደቶች

ተካፋዮቹ በቀጣዮቹ ቀናት ውስጥ አዲስ የሲኖዶሳዊነት ጊዜ ማዳመጥ እና ማስተዋል መንገዶችን መሠረት በማድረግ ተወያይተዋል።

ብጹዕ ካርዲናል ማርዮ ግሬች “በ16ኛው የጳጳሳት ሲኖዶስ ጠቅላላ ጉባኤ መጨረሻ ሠነድ ላይ ያተኮረው የአፈጻጸም ምዕራፍ የቅድመ ስብሰባው ሂደት ድግግሞሽ ሳይሆን የአካባቢው ማኅበረሰቦች የሲኖዶሱን ሠነድ ምክረ ሃሳቦችን ወደራሳቸው አውድ እንዲተረጉሙት የተጠሩበት አዲስ ሂደት ነው” ሲሉ አስረድተዋል።

የስብሰባው ተሳታፊዎች በአህጉራት ውስጥ የመጨረሻውን ሠነድ ተግባራዊ ለማድረግ በታዩ ዋና ዋና ዕድገቶች ላይ የተወያዩ ሲሆን፥ ከእነዚህም ውስጥ ጉልህ ተሞክሮዎች፣ ያጋጠሙ ችግሮች፣ የቀረቡ ጥያቄዎች እና ሐዋርያዊ አገልግሎትን የሚመለከቱ ጉዳዮች እንደሚገኙበት ታውቋል።

በ 2028 ዓ. ም. ሊካሄድ የታቀደ ጠቅላላ ጉባኤ

በስብሰባው መካከል የሲኖዶሱ አማካሪ የሆኑት አባ ጃኮሞ ኮስታ ባቀረቡት ሠነድ ላይ ውይይት የተደረገበት ሲሆን፥ ሠነዱ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በጥቅምት ወር 2028 ዓ. ም. ወደ ሚካሄደ ጠቅላላ የቤተ ክርስቲያን ጉባኤ የሚወስዱ አራት ደረጃዎችን ይዘረዝራል።

የመጀመሪያው “ማስታወስ” የሚል ሲሆን እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2027 ዓ. ም. የመጀመሪያ አጋማሽ ላይ በሀገረ ስብከቶች እና በኤፓርኪዎች ውስጥ የግምገማ ስብሰባዎች የሚካሄዱበት ደረጃ እንደሆነ ታውቋል።

ሁለተኛው ደረጃ “በተግባር መተርጎም” የሚል ሲሆን ይህም እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2027 ዓ. ም. ሁለተኛ አጋማሽ ላይ በብሔራዊም ሆነ በክልል የጳጳሳት ጉባኤዎች አማካኝነት የሚደረግ ስብሰባ እንደሆነ ተገልጿል።

ሦስተኛው ደረጃ “ማተኮር” የሚል ሲሆን፥ ይህም በ2028 ዓ. ም. የመጀመሪያዎቹ አራት ወራት ውስጥ የሚካሄድ ሲሆን፥ ይህም የአመለካከት ሪፖርቶችን የሚያቀርቡ አህጉራዊ ጉባኤዎች እንደሚሆኑ ታውቋል።

የመጨረሻው ደረጃ “በደስታ ማክበር” የሚል ሲሆን ይህም እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በጥቅምት ወር 2028 ዓ. ም. መላዋ ቤተ ክርስቲያን በቫቲካን ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ጋር የምታካሂደው ጉባኤ ማጠናቀቂያ እንደሆነ ተገልጿል።

የስብሰባው ተሳታፊዎች፥ የአህጉራዊ አካላት እና ቡድኖቻቸው ሚና ከሁሉም በላይ ድጋፍ መስጠት እንጂ ክትትል ማድረግ እንዳልሆነ አፅንዖት ሰጥተው፥ ተግባራቸው በእውነተኛ መንፈስ በአገራቱ ቤተ ክርስቲያናት መካከል የስጦታ ልውውጥን ማስተዋወቅ እንደሆነ ተገልጿል።

እንደ ጎርጎሮሳውያኑ እስከ 2028 ዓ. ም. ድረስ ያሉት ጉባኤዎች የቤተ ክርስቲያኒቱ ሲኖዶሳዊ የለውጥ ጉዞ የመጨረሻ ደረጃ ሳይሆኑ ነገር ግን እንዴት መቀጠል እንደሚቻል ለመረዳት የሚያግዙ የማስተዋል ጊዜያት መሆናቸውን አፅንዖት ሰጥተዋል።

 

27 Jun 2026, 16:47