ፈልግ

የዓለም የምግብ ፕሮግራም  በአፍሪካ እና በላቲን አሜሪካ የሚከናውናቸው የዕርዳታ አቅርቦት የዓለም የምግብ ፕሮግራም በአፍሪካ እና በላቲን አሜሪካ የሚከናውናቸው የዕርዳታ አቅርቦት   (World Food Programme)

ረሃብ ባለበት ዓለም ውስጥ ሰላምን ማንገሥ እንደማይቻል ተገለጸ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ሰኞ ሰኔ 15/2018 ዓ. ም. በሮም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት የዓለም የምግብ ፕሮግራም ዋና መሥሪያ ቤት (WFP) ጎብኝተው ለዓለም የምግብ ፕሮግራም ሥራ አስፈፃሚ ቦርድ ንግግር ማድረጋቸው ይታወሳል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የስብሰባው ተካፋይ የነበሩት የአፍሪካ እና የላቲን አሜሪካ ዳይሬክተሮች ኪንዴይ ሻምባ እና ሊና ሳቬሊ የቅዱስነታቸው ጉብኝት ጠቀሜታን በማስመልከት ከቫቲካን ሚዲያ ጋር ቃለ ምልልስ አድርገዋል።ዳይሬክተሮቹ በቃለ ምልልሳቸው፥ የምግብ እጥረትን ምክንያት በማድረግ የሚታዩ አንዳንድ ጭፍን ጥላቻዎችን በማውገዝ፥ በየአገራቱ ምርት እንደማያቋርጥ ነገር ግን ተደራሽነትን ማረጋገጥ እና ሌሎች ቀውሶች ከችግሮች መካከል ጥቂቶቹ መሆናቸውን ገልጸው፥ የገንዘብ እጥረት እንዲከሰት የሚያደርጉ አሳዛኝ ምርጫዎች መኖራቸውን አስረድተዋል።

“በዓለም ውስጥ ምግብ አለ፤ ችግሩ ግን ማን ሊያገኘው፣ ማን ሊገዛው እና የአየር ንብረት ለውጥ ከሚያስከትለው አደጋ ሊተርፍ የሚችል ማን ነው?” የሚል እንደሆነ ገልጸው፥ ይህ ደግሞ ብዙውን ጊዜ ችላ የሚባልበት መሆኑን የምዕራብ እና መካከለኛው አፍሪካ እንዲሁም የላቲን አሜሪካ እና ካሪቢያን የዓለም የምግብ ፕሮግራም (WFP) ዳይሬክተሮች ኪንዴይ ሻምባ እና ሊና ሳቬሊ ለቫቲካን ሚዲያ አስረድተዋል።

ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት የተሰጠ እውቅና ዋጋ

ዳይሬክተሮቹ በሮም የፕሮግራሙ ዋና መሥሪያ ቤት የተገኙ ቢሆንም ሁለቱም በመንፈሳዊነታቸው ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ጋር ተገናኝተዋል። “ሙስሊም ብሆንም ነገር ግን እንደ ማንኛውም ክርስቲያን እጅግ ደስተኛ ነኝ” ያለችው ሻምባ፥ “ስብሰባው ለሥራችን እና በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ለሚገኙ የድርጅቱ ሠራተኞች እውቅናን የሚሰጥ በመሆኑ ደስተኛ ነኝ” ስትል ገልጻለች።

“የቅዱስነታቸው ጉብኝት ለክልላችን ትልቅ ክብር ነው” በማለት ስሜቷን የገለጸችው ሳቬሊ፥ የምትሠራበት አካባቢ በካቶሊክ እምነት የሚታወቅ እና “የሰው ልጅ ክብር፣ አንድነት እና የተጎዱትን መንከባከብ” የሚለው የቤተ ክርስቲያኗ ማኅበራዊ አስተምህሮ እሴቶች በመኖራቸው እና እነዚህም ከዓለም የምግብ ፕሮግራም (WFP) ተልዕኮ ጋር የሚጣጣሙ ናቸው” ስትል አስረድታለች።

ወደ ጦርነት የሚመራ ረሃብ

ሁለቱም ዳይሬክተሮች በዓለም ዙሪያ ረሃብን እንደ መሣሪያነት መጠቀምን በመቃወም የሚያሰሙትን ድምፅም ጨምሮ በአኅጉራቱ ለሚሰጧቸው አገልግሎቶች ምስጋና ተሰጥቶአቸዋል። እንደ ሳሄል ባሉ ውስብስብ አካባቢዎች ባላት ልምድ፣ ሰብዓዊ ዕርዳታ ካልተደረገላቸው ሰዎች እንዴት እንደሚደኸዩ እና የኑሮ መተዳደሪያቸውን እንደሚያጡ እንዲሁም በክልሉ ከሚንቀሳቀሱ የታጠቁ ቡድኖች ጋር የመቀላቀል ዕድላቸው ከፍተኛ መሆኑን ሻምባ አስረድታለች።

አንድ ድንጋጤ በሌላው ሌላ ድንጋጤ

የዓለም የምግብ ፕሮግራም (WFP) በአህጉሪቱ ላይ ያለውን ፈጣን ሰብዓዊ እርዳታን ከረጅም ጊዜ የመልሶ ግንባታ ጥረቶች ጋር የሚጣምር ሲሆን፥ ፕሮጀክቶቹ በማሊ፣ በቡርኪናፋሶ፣ በኒጀር፣ በቻድ ሐይቅ ተፋሰስ አገራት፣ በሰሜናዊ ናይጄሪያ፣ በካሜሩን እና በቻድ ውስጥ ጠንካራ መሆናቸው ታውቋል። ሰዎች እንዲሸሹ ከሚያስገድዷቸው ግጭቶች በተጨማሪ ከአየር ንብረት ጋር የተያያዙ ጉዳዮች በአንዳንድ የሳህል ክፍሎች በረሃማነት መሬቱን እያደረቀው እና ዝናብ እንዲጠፋ እያደረገው እንደሚገኝ ታውቋል። ስለዚህ ከአካባቢው ማኅበረሰቦች ጋር በመተባበር ያሉትን ሃብቶች በአግባቡ ለመጠቀም፣ ሰብሎችን ለማመቻቸት እና የሚገኘውን ውስን የዝናብ ውሃ ለመጠበቅ ድርጅቱ እየሠራ እንደሚገኝ ተገልጿል።

የችግር እና የዕድል አገራት

በአፍሪካ ውስጥ የዓለም የምግብ ፕሮግራም (WFP) ዘላቂ የሆነ የረሃብ እና የጸጥታ ችግሮች የሚያጋጥመው ሲሆን፥ እነዚህ ችግሮች በምዕራባውያን ሚዲያዎች ውስጥ ብዙውን ጊዜ ዓለም አቀፍ ትኩረት እንደማያገኙ ተገልጿል።

ሻምባ የመካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክን ምሳሌ በመጥቀስ፥ ለብዙ ዓመታት በአካባቢው ከባድ የሚባል ጦርነት አለመኖሩን ተናግራ፣ ከፍተኛ የምግብ ዋስትና ማጣት እና በችግር ውስጥ የሚኖሩ ስደተኞች መኖራቸውን ገልጻለች። በሌላ በኩል በፔሩ ውስጥም ችግሮች መኖራቸውን የምትገልጸው ሳቬሊ፥  በአካባቢው የሚገኙ የሥራ ባልደረቦቻቸው በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ጉብኝት እጅግ መነካታቸውን ገልጻ፥ እንደ ቬንዙዌላ እና ሄይቲ ያሉ የዓለም የምግብ ፕሮግራም (WFP) የሚገኝባቸው አገራት ከሌሎች በርካታ አገራት ውስጥ ጥቂቶቹ እንደሆኑ ጠቅሳለች።

ደህንነትን አደጋ ላይ መጣል

ሳቬሊ ወደ ግማሽ የሚጠጋ ሕዝብ በረሃብ በሚሰቃይበት የመጨረሻው አገር ቀውስ ላይ በማትኮር፥ በቀን አንድ ጊዜ ብቻ መመገብ ወይም የአመጋገብ ፍላጎቶችን በማያሟሉ ርካሽ ምግቦች ላይ እንደሚመኩ ገልጻ፥ ይህ ማለት በዓመፅ ምክንያት ምግብ ፍለጋ ገበያ መሄድ አለመቻል ወይም ምግብ የማምረት አቅም አለመኖር ማለት እንደሆነ ተናግራ፥ ለምግብ ፍለጋ ሲባል ደህንነትን አደጋ ላይ መጣል ወይም ያለ ምግብ የመኖር ምርጫ እንደሆነ አስረድታለች።

ከፍተኛ ምርት እና ደካማ ተደራሽነት

በዓለም ላይ ትልቁ የምግብ ላኪ የላቲን አሜሪካ ክልል፥ ሕዝቡን በቀን ሁለት ጊዜ ለመመገብ የሚያስችል በቂ የማምረት አቅም ያለው ቢሆንም ነገር ግን ቀጣይነት ባለው ረሃብ እንደሚቸገር ተገልጿል። ችግሩ ከኤኮኖሚ አቅርቦት ጋር የተያያዘ አለመመጣጠን ሲሆን የዓለምን ሁሉንም ክልሎች ብንመለከት አንድ ሰው ጤናማ አመጋገብን ለመከተል ከፍተኛ ወጪ በማድረጉ ምክንያት ሁሉም ሰው ገንቢ ምግብ መግዛት እንደማይችል ተገልጿል።

የአካባቢ ሁኔታ በረሃብ ላይ የሚያስከትለው ተጽእኖ

በላቲን አሜርካ አገራት ውስጥ ያለው የአካባቢ ተጽዕኖ፥ ባለፈው ዓመት በተከሰተው ሜሊሳ የአውሎ ነፋስ አደጋ እና የዛሬው የኤልኒኞ የአየር ሁኔታ፣ ድርቅ እና ጎርፍ በመካከለኛው አሜሪካ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እያሳደረ እንደሚገኝ ተገልጾ፥ ይህ በአካባቢው አገራት ውስጥ ሌሎች 16 ሚሊዮን ሰዎችን የምግብ ዋስትና እጦት ውስጥ ሊያስገባ እንደሚችል ተገምቷል። ከዚህ በተጨማሪ እንደ ሄይቲ ባሉ አገራት ውስጥ ከሚከሰቱ ዓመጾች ጋር የተያያዘው ረሃብ ብዙውን ጊዜ የቤተሰብን መደበኛ ኑሮ ለማረጋገጥ የመጨረሻ አማራጭ ተደርጎ የሚታሰበው የስደት ጉዳይ መኖሩም ተገልጿል።

አስገራሚው የገንዘብ ድጋፍ ማሽቆልቆል

እነዚህን ምክንያቶች ዝቅ አድርጎ መመልከት ወደ ከፍተኛ የገንዘብ እጥረት እንደሚያመራ የተገለጸ ሲሆን፥ ይህም በዓለም ላይ ትልቁ የሰብዓዊነት ድርጅት እና እንደ ጎርጎሮሳውያኑ የ2020 የኖቤል የሰላም ሽልማት አሸናፊ የሆነውን የዓለም የምግብ ፕሮግራም፥ ግቦቹን እንደገና መመልከት አስፈላጊ እንደሚያደርገው ተገልጿል። ባለፈው ዓመት በላቲን አሜሪካ ከሚገኙ 33 ሚሊዮን የምግብ ዋስትና እጦት ካጋጠማቸው ሰዎች መካከል 8.6 ሚሊዮን ሰዎች ብቻ ዕርዳታ ማግኘታቸውን የክልሉ ዳይሬክተር ሳቬሊ ገልጻ፥ በእነዚህ ሁኔታዎች ውስጥ እጅግ አስቸጋሪ ውሳኔዎች እንደሚደረጉ፥ ብዙ ሰዎችን ለመርዳት የሚቀርብ የምግብ መጠን መቀነስ ወይም ሙሉ በሙሉ እንዲቆይ ወይም ጥቂቶችን ብቻ እንዲደርስ ማድረግ፣ እንደ ሕፃናት፣ እርጉዝ ሴቶች ወይም ስደተኞች የመሳሰሉ ተጋላጭ ቡድኖች መካከል ምርጫ ማድረግ እና በአደጋ ጊዜ ምላሾች እና በማኅበረሰብ የመቋቋም አቅም ላይ የረጅም ጊዜ የገንዘብ ወጭ መካከል ያለው ሚዛን ሁለቱም አስፈላጊ መሆናቸውን አስረድተዋል።

የአፍሪካ ፕሮግራሞችንም ተመሳሳይ ችግር እንደሚያጋጥማቸው እና ማግኘት ከሚያስፈልገው ገንዘብ በጣም ያነሰ እንደሆነ በዚህም ምክንያት በአንዳንድ አገሮች ከ10-20% የሚሆነውን ፍላጎት ብቻ እያሟሉ እንደሆነ ሳምባ አስረድቷል። ይህ ማለት የምናገለግላቸውን ሰዎች ቁጥር መቀነስ እና አንዳንድ ጊዜ ሠራተኞችን መቀነስ እንደሚኖርባቸው ተናግረው፥ ይህ በሰዎች ሕይወት እና ከእኛ ጋር በሚሠሩ ሰዎች ኑሮ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ የሚያሳድር መሆኑን ተናግሯል።

 

24 Jun 2026, 16:29