ፈልግ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በካስቴል ጋንዶልፎ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በካስቴል ጋንዶልፎ   (ANSA)

የካስቴል ጋንዶልፎ ከተማ ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ክብር ኮንሴርት ማዘጋጀቱ ተገለጸ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የበጋ ወቅት የዕረፍት ጊዜያቸውን የሚያሳልፉበት የአልባኖ ሀገረ ስብከት ለቅዱስነታቸው ክብር ኮንሴርት ማዘጋጀቱን አስታውቋል። ሀገረ ስብከቱ ኮንሴርቱን የሚያቀርበው በካስቴል ጋንዶልፉ በሚገኘው ሐዋርያዊ ሕንጻ ውስጥ ቅዳሜ ሐምሌ 11/2018 ዓ. ም እንደሆነ ገልጿል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የአልባኖ ሀገረ ስብከት በካስቴል ጋንዶልፎ በሚገኘው ሐዋርያዊ ሕንጻ ውስጥ ቅዳሜ ሐምሌ 11/2018 ዓ. ም. ከምሽቱ ሦስት ሰዓት ጀምሮ በሚቀርበው ኮንሴርት ላይ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የሚገኙ ሲሆን፥ የኮንሴርቱ ዋና ዓላማ ሀገረ ስብከቱ ከቅዱስነታቸው ጋር ያለውን የፍቅር እና የኅብረት ምልክት ለመግለጽ መሆኑን ታውቋል።

መርሃ ግብሩ የሚጀምረው ታዋቂዋ የፒያኖ ተጫዋች ሮሳና ቶማሲ በምትጫወተው እና የኦስካር አሸናፊው አቀናባሪ ሉዊስ ባካሎቭ በጻፈው አዲስ ሥራ እንደሚሆን ታውቋል።

የሶሎ ዘማሪያኑ የሚታጀቡት እንደ ጎርጎርሳውያኑ ከ2006 ዓ. ም. ጀምሮ የብሬሻ እና የቤርጋሞ ዓለም አቀፍ የፒያኖ ፌስቲቫል ጥበባዊ ዳይሬክተር በነበረው ፒየር ካርሎ ኦሪዚዮ እና በብሬሻ ኮንሰርቫቶሪ የኦርኬስትራ ዳይሬክተር በሆነው ፕሮፌሰር ሉካ ማሬንዚዮ የሚመሩት 55 አባላት በኅብረት በሚያቀርቡት ዝማሬ እንደሚሆን ታውቋል።

በቤሊኒ ተነሳሽነት የተዘጋጀው ቅንብሩ የኦፔራውን ድራማ ቁልፍ ጊዜያትን በሚያጎላ ዝግጅት የሚታጀብ ሲሆን፥ ኮንሴርቱ ከፋብሪኒ ስብስቦች መካከል የቤችስቴይን ግራንድ የፒያኖ ጨዋታን እንደሚያቀርብ ታውቋል።

“ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በሀገረ ስብከታችን ውስጥ መገኘት የአካባቢያችንን ቤተ ክርስቲያን እና ምዕመናኖቿን በደስታ ሞልቷቸዋል” ሲሉ የአልባኖ ሀገረ ስብከት ጳጳስ አቡነ ቪንቼንሶ ቪቫ ተናግረዋል።

ብጹዕ አቡነ ቪንቼንሶ በማከልም ለተነሳሽነቱ አስተዋጽኦ የደረጉትን፥ “ባንካ ዲ ክሬዲቶ ኮኦፔራቲቮ ዴይ ካስቴሊ ሮማኒ” እና “ዴል ቱስኮሎ” ን ጨምሮ ሌሎች በርካታ የአካባቢው ንግድ ማኅበረሰብን፣ ለጋሾችን እና ደጋፊዎችን አመስግነዋል።

በተጨማሪም ዝግጅቶቻቸውን በቁርጠኝነት ለማቅረብ የተዘጋጁ አርቲስቶችን፣ የሀገረ ስብከቱ መንፈሳዊ ዜማ አስተባባሪ ጽሕፈት ቤትን፣ በካስቴል ጋንዶልፎ የሚገኘውን የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ማረፊያ አስተዳደር አባላትን አመስግነዋል።

 

18 Jul 2026, 10:23