ፈልግ

አባ ሉቺዮ ሩይዝ (በስተ ግራ( አባ ሉቺዮ ሩይዝ (በስተ ግራ( 

አባ ሉቺዮ ሩይዝ የበጎ አድራጎት አገልግሎት ጽሕፈት ቤት ዋና ጸሐፊ ሆነው ተሾሙ

እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከ2015 ጀምሮ የቅድስት መንበር መገናኛዎች ጽሕፈት ቤት ዋና ጸሐፊ ሆነው ያገለገሉት አርጄንቲናዊ ካኅን አባ ሩይዝ በተለምዶ ሐዋርያዊ የበጎ አድራጎት ማስተባበሪያ በመባል የሚታወቀው የበጎ አድራጎት አገልግሎት ጽሕፈት ቤት ጸሐፊ ሆነው በርዕሠ ሊቃነ ጳጳስት ሊዮ 14ኛ የተሾሙ ሲሆን፥ በሥራ ገበታቸው የሚገኙት ከነሐሴ 26/2018 ዓ. ም. ጀምሮ እንደሆነ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ የቅድስት መንበር መገናኛዎች ጽሕፈት ቤት ጸሐፊ የነበሩት አባ ሉቺዮ ሩይዝ በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት የበጎ አድራጎት ተነሳሽነቶች እና የሰብዓዊ ዕርዳታዎች አስተባባሪ ጽሕፈት ቤት ውስጥ የበጎ አድራጎት አገልግሎት ጸሐፊ አድርገው ሾመዋል።

ሰኞ ሰኔ 22/2018 ዓ. ም. የተገለጸው ሹመቱ ከቅርብ ወራት ወዲህ በቅድስት መንበር ከፍተኛ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤቶች ውስጥ ከተደረጉ ለውጦች መካከል አንዱ እንደሆነ ታውቋል። ሁለቱ ጽሕፈት ቤቶች ማለትም የቅድስት መንበር መገናኛዎች እና የበጎ አድራጎት አገልግሎት ጽሕፈት ቤት በቅርቡ አዳዲስ መሪዎችን ማግኘታቸው ታውቋል።

በላቲን አሜሪካ እና በሮም ያካበቷቸው ልምዶች

አባ ሩይዝ ከአቡነ ማሪን ደ ሳን ማርቲን ጋር በቅድስት መንበር በጎ አድራጎት አገልግሎት ጽሕፈት ቤት ውስጥ ከነሐሴ 26/2018 ዓ. ም. ጀምሮ አብረው እንደሚገለግሉ ታውቋል። አባ ሩይዝ የቅድስት መንበር መገናኛዎች እንደ አዲስ ከተዋቀረበት ጊዜ ጀምሮ ዋና ጸሐፊ ሆነው ማገልገላቸው ይታወሳል።

የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በተለይም በላቲን አሜሪካ ውስጥ በመገናኛ እና ሚዲያ ዘርፎች የብዙ ዓመታት ልምድ ያላቸውን አባ ሩይዝን እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከሰኔ 27/2015 ዓ. ም. ጀምሮ የቅድስት መንበር መገናኛዎች ዋና ጸሐፊ አድርገው መሾማቸው ይታወሳል። አባ ሩይዝ በላቲን አሜሪካ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን የመረጃ መረብ አማካሪ እና የላቲን አሜሪካ ጓዳሉፔ እመቤታችን ማርያም የልማት ማዕከል ፕሬዝዳንት ሆነው አገልግለዋል።

አባ ሩይዝ በሮም በሚገኝ የቅዱስ መስቀል ጳጳሳዊ ዩኒቨርሲቲ መገናኛ ፋኩልቲ ውስጥ በመምህርነት  እንዲሁም በግሪጎሪያን ጳጳሳዊ ዩኒቨርሲቲ ተጋባዥ መምህር ሆነው በማስተማር ላይ እንደሚገኙ ታውቋል። እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በጥር ወር 2025 ዓ. ም. ዓለም አቀፍ የመገናኛ ኢዮቤልዩን እና በሐምሌ ወር የዲጂታል ሚስዮናውያን እና የካቶሊክ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ኢዮቤልዩ እንዲዘጋጅ አስተዋጽኦ አድርገዋል።

አዲሱ ተልዕኳቸው

አባ ሩይዝ ሹመታቸው ከተነገራቸው በኋላ ብዙም ሳይቆዩ ለቅድስት መንበር መገናኛዎች ጽሕፈት ቤት ሠራተኞች ባደረጉት ንግግር፥ “ጌታ በጠራኝ ጊዜ ሁሉ ልከተለው ደስተኛ ነኝ” ብለው፥ ከሌሎች ጋር ሆነው ለሠሩባቸው ዓመታት ምስጋናቸውን በማቅረብ በተለይም በጽሕፈት ቤቱ ምሥረታ የመጀመሪያ ደረጃዎች ላይ ላጋጠሟቸው ማናቸውም ችግሮች ይቅርታን ጠይቀዋል።

እንዲሁም በተጀመረው እና በተገነባው ፕሮጀክት ላይ ስለሚሰማቸው የኃላፊነት ስሜት እና ቁርኝት ተናግረው፥ እንዲህ ዓይነቱ ትስስር በፍፁም የማያልቅ መሆኑ አስረድተዋል።

አዲስ ምክትል ፀሐፊ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በአሁኑ ወቅት የበጎ አድራጎት አገልግሎት ጽሕፈት ቤት ባለስልጣን የሆኑትን ማሲሞ ራሊን በተመሳሳይ ጽሕፈት ቤት ምክትል ፀሐፊ አድርገው የሾሟቸው ሲሆን፥ አዲሱን ሚናቸውን የሚጀምሩት በነሐሴ 26/2018 ዓ. ም. እንደሚሆን ታውቋል።

 

01 Jul 2026, 16:27