ፈልግ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ለሐዋርያዊ ጉብኝት ወደ ላምፔዱሳ ሲደርሱ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ለሐዋርያዊ ጉብኝት ወደ ላምፔዱሳ ሲደርሱ   (@Vatican Media)

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ለሐዋርያዊ ጉብኝት ወደ ላምፔዱሳ መድረሳቸው ተገለጸ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ቅዳሜ ሰኔ 27/2018 ዓ. ም. ጠዋት ደቡባዊ የጣሊያን ደሴት ወደ ሆነች ላምፔዱሳ ደርሰዋል። የጣሊያን ደሴት ላምፔዱሳ ከአፍሪካ ወደ አውሮፓ በባሕር ለሚጓዙ ስደተኞች ዋና መዳረሻ ስትሆን፥ ቅዱስነታቸውም በዚህች ደሴት የሚያደርጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን ጀምረዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ቅዳሜ ሰኔ 27/2018 ዓ. ም. ከጠዋቱ 2:54 ደቂቃ ወደ ላምፔዱሳ ደርሰው ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን የጀመሩ ሲሆን፥ ይህች የደቡብ ጣሊያን ደሴት በተለይም ከሰሜን አፍሪካ ወደ አውሮፓ አደገኛ የባሕር ላይ ጉዞ ለሚያደርጉት ስደተኞች መዳረሻ እንደሆነች ይታወቃል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በጉብኝታቸው መጀመሪያ፥ በደሴቲቱ የሚገኘውን እና በባሕር ላይ ጉዞ ሕይወታቸውን ያጡ በርካታ ስደተኞች የተቀበሩበትን ሥፍራ እንደሚጎበኙ፥ ከዚያም “ወደ አውሮፓ መሄጃ በር” በመባል የሚታወቀውን ሐውልት ለመጎብኘት እና ወደ አውሮፓ ለመድረስ ሲሞክሩ ሕይወታቸውን ያጡ ስደተኞች መታሰቢያን እንደሚጎበኙ የጉብኝታቸው መርሃ ግብር አመልክቷል።

ቅዱስነታቸው በመቀጠልም “ፋቫሎሮ ፒየር” በተባለ ሥፍራ ከስደተኞች ጋር ከተገናኙ በኋላ ለቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስችስኮስ መታሰቢያነት የተሠራውን ሐውልት እንደሚባርኩ ታውቋል።

የቅዱስነታቸው የላምፔዱሳ ጉብኝት፥ የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እንደ ጎርጎሮሳውያን ሐምሌ 8/2013 ዓ. ም. ከሮም ውጭ ለመጀመሪያ ጊዜ ያደረጉትን የላምፔዱሳ ሐዋርያዊ ጉብኝት እንደሚያስታውስ ተገልጿል።

በመጨረሻም ቅዱስነታቸው ወደ ሮም ከመመለሳቸው በፊት መስዋዕተ ቅዳሴን ካቀረቡ በኋላ ከአካባቢው ባለስልጣናት፣ ከሕጻናት እና ከበጎ ፈቃደኞች ጋር ሰላምታ ከተለዋወጡ በኋላ ማታ አሥራ ሁለት ሰዓት ተኩል ላይ ከላምፔዱሳ ተነስተው ከምሽቱ አንድ ሰዓት ከአርባ አምስት ደቂቃ ላይ ወደ ሮም እንደሚደርሱ ይጠበቃል።

 

04 Jul 2026, 10:46